በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ታማኞቹን አይጥልም

ይሖዋ ታማኞቹን አይጥልም

 ይሖዋ ታማኞቹን አይጥልም

‘ይሖዋ ታማኞቹን አይጥልም፤ ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል።’—መዝ. 37:28

1, 2. (ሀ) በአሥረኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የአምላክ አገልጋዮችን ታማኝነት የተፈታተኑ ምን ሁኔታዎች ተከስተው ነበር? (ለ) ይሖዋ ታማኞቹን የጠበቃቸው በየትኞቹ ሦስት ሁኔታዎች ሥር ነው?

ጊዜው አሥረኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ሲሆን የይሖዋ አገልጋዮች ውሳኔ የሚጠይቅ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል። ለውጥ ፈላጊ የሆኑት በስተ ሰሜን ያሉት የእስራኤል ነገዶች የራሳቸውን መንግሥት እንዲያቋቁሙ ባይፈቀድላቸው ኖሮ በእስራኤል የእርስ በርስ ጦርነት ይቀሰቀስ ነበር። በቅርቡ የተሾመው የአሥሩ ነገድ ንጉሥ ኢዮርብዓም ሥልጣኑን ለማጠናከር ሲል ወዲያውኑ አዲስ የመንግሥት ሃይማኖት አቋቋመ። ኢዮርብዓም ሕዝቡ ሙሉ በሙሉ ታማኝ እንዲሆኑለት ይጠብቅባቸው ነበር። ታዲያ በዚህ ወቅት የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ምን ያደርጉ ይሆን? ለአምላካቸው ታማኝ በመሆን ይጸኑ ይሆን? በሺዎች የሚቆጠሩ የአምላክ አገልጋዮች እንዲህ ያደረጉ ሲሆን ይሖዋም ታማኝ ስለሆኑ ጥበቃ አድርጎላቸዋል።—1 ነገ. 12:1-33፤ 2 ዜና 11:13, 14

2 በዛሬው ጊዜም ቢሆን የአምላክ አገልጋዮች ታማኝነታቸውን የሚፈትን ሁኔታ ያጋጥማቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ማሳሰቢያ ይሰጣል:- “ራሳችሁን የምትገዙ ሁኑ፤ ንቁም፤ ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ ወዲያ ወዲህ ይዞራል።” ታዲያ ዲያብሎስን ‘በእምነት ጸንተን በመቃወም’ ረገድ ሊሳካልን ይችላል? (1 ጴጥ. 5:8, 9) በ997 ከክርስቶስ ልደት በፊት ንጉሥ ኢዮርብዓም ሥልጣን ሲጨብጥ የተከናወኑትን ነገሮች በመመርመር ከእነዚህ ሁኔታዎች ምን ትምህርት እንደምናገኝ እስቲ እንመልከት። በእነዚያ አስጨናቂ ወቅቶች የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ጭቆና ይደርስባቸው እንዲሁም በከሃዲዎች ተጽዕኖ ይደረግባቸው ነበር፤ ከዚህም በተጨማሪ አስቸጋሪ የሆኑ ተልእኮዎችን መወጣት ነበረባቸው። በእነዚህ በሦስቱም ሁኔታዎች ሥር ይሖዋ በዚያን ጊዜ የነበሩ ታማኝ አገልጋዮቹን አልጣላቸውም፤ በዛሬው ጊዜም ቢሆን ታማኝ አገልጋዮቹን አይጥላቸውም።—መዝ. 37:28

ጭቆና ሲደርስባቸው

3. የንጉሥ ዳዊት አገዛዝ ጨቋኝ አልነበረም የምንለው ለምንድን ነው?

3 እስቲ በመጀመሪያ፣ ኢዮርብዓም ወደ ንግሥና እንዲመጣ ያደረጉትን ሁኔታዎች እንመልከት። ምሳሌ 29:2 “ክፉዎች ሲገዙ . . . ሕዝብ ያቃስታል” ይላል። የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ በነበረው በዳዊት የግዛት ዘመን ሕዝቡ አላቃሰተም ወይም አልተማረረም። ዳዊት ፍጹም ባይሆንም ለአምላክ ታማኝ ነበር፤ እንዲሁም በእሱ ላይ እምነት ነበረው። በመሆኑም የዳዊት አገዛዝ ጨቋኝ አልነበረም። ይሖዋ “ቤትህና መንግሥትህ በፊቴ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤ ዙፋንህም እንደዚሁ ለዘላለም የጸና ይሆናል” በማለት ከዳዊት ጋር ቃል ኪዳን ገብቶ ነበር።—2 ሳሙ. 7:16

4. በሰሎሞን የግዛት ዘመን ሕዝቡ ያገኘው በረከት ቀጣይ መሆኑ በምን ላይ የተመካ ነበር?

4 የዳዊት ልጅ የነበረው የሰሎሞን አገዛዝ መጀመሪያ ላይ ሰላም የሰፈነበት ከመሆኑም በላይ ብሔሩ በልጽጎ ስለነበር ወደፊት ለሚመጣው የክርስቶስ ኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት ተስማሚ ጥላ ሊሆን ይችላል። (መዝ. 72:1, 17) በዚያን ጊዜ ከ12ቱ የእስራኤል ነገዶች መካከል አንዱም ቢሆን እንዲያምፅ የሚያደርገው ምክንያት አልነበረም። ይሁን እንጂ ሰሎሞንም ሆነ ተገዢዎቹ ያገኙት በረከት ቀጣይ እንዲሆን ማሟላት የሚገባቸው ነገር ነበር። ይሖዋ፣ ሰሎሞንን እንዲህ ብሎት ነበር:- “ሥርዐቴን ብትከተል፣ ፍርዴን በተግባር ብትገልጸው፣ ትእዛዛቴን ብትጠብቅና ብትመላለስባቸው ለአባትህ ለዳዊት የሰጠሁትን ተስፋ በአንተ እፈጽመዋለሁ፤ በእስራኤላውያን መካከል እኖራለሁ፤ ሕዝቤን እስራኤልንም አልተወውም።”—1 ነገ. 6:11-13

5, 6. ሰሎሞን ለአምላክ ታማኝ አለመሆኑ ምን አስከተለ?

5  ሰሎሞን በሸመገለ ጊዜ ግን ለይሖዋ የነበረውን ታማኝነት በማጉደል በሐሰት አምልኮ መካፈል ጀመረ። (1 ነገ. 11:4-6) ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ሰሎሞን የይሖዋን ሕግጋት መታዘዝ የተወ ሲሆን ሕዝቡንም ይበልጥ ይጨቁናቸው ጀመር። የሰሎሞን አገዛዝ በጣም ጨቋኝ ስለነበር እሱ ከሞተም በኋላ እንኳ ሕዝቡ ሰሎሞንን ተክቶ ለነገሠው ለልጁ ለሮብዓም ቅሬታቸውን ገልጸው ነበር፤ እንዲሁም ሮብዓም እረፍት እንዲሰጣቸው ጠይቀውታል። (1 ነገ. 12:4) ሰሎሞን ታማኝነቱን ሲያጓድል ይሖዋ ምን እርምጃ ወሰደ?

6 “ሰሎሞን ሁለት ጊዜ ከተገለጠለት ከእስራኤል አምላክ . . . ልቡ ስለ ሸፈተ፣ እግዚአብሔር ተቈጣው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ይሖዋ፣ ሰሎሞንን እንዲህ አለው:- “ያዘዝሁህን ኪዳኔንና ሥርዐቴንም ባለመጠበቅህ፣ መንግሥትህን ከአንተ ወስጄ ከአገልጋዮችህ ለአንዱ እሰጠዋለሁ።”—1 ነገ. 11:9-11

7. ይሖዋ፣ ሰሎሞንን ቢተወውም ለታማኞቹ ጥበቃ ያደረገላቸው እንዴት ነበር?

7 ከዚያም ይሖዋ፣ ሕዝቡን ከጭቆና ቀንበር ነፃ የሚያወጣ ሰው እንዲቀባ ነቢዩን አኪያን ላከው። ይህ ነፃ አውጪ በሰሎሞን መንግሥት ሥር ያገለግል የነበረ ኢዮርብዓም የተባለ ብቃት ያለው ሰው ነበር። ይሖዋ ከዳዊት ጋር ለገባው የመንግሥት ቃል ኪዳን ታማኝ ቢሆንም 12ቱን ነገዶች ያቀፈው መንግሥት ለሁለት እንዲከፈል ፈቅዷል። በዳዊት የዘር ሐረግ ለመጣው ለንጉሥ ሮብዓም ሁለቱ ነገዶች ብቻ ሲቀሩለት አሥሩ ነገዶች ለኢዮርብዓም ተሰጡ። (1 ነገ. 11:29-37፤ 12:16, 17, 21) ይሖዋ ኢዮርብዓምን እንዲህ ብሎት ነበር:- “ባሪያዬ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ አንተም ያዘዝሁህን ሁሉ ብትፈጽም፣ በመንገዴ ብትሄድ፣ ሥርዐቴንና ትእዛዜን በመጠበቅ ትክክል የሆነውን ነገር በፊቴ ብታደርግ፣ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ የዳዊትን ሥርወ መንግሥት እንዳጸናሁ፣ ለአንተም እንዲሁ እስከ ዘላለም የሚኖር ሥርወ መንግሥት አጸናለሁ፤ እስራኤልንም ለአንተ እሰጣለሁ።” (1 ነገ. 11:38) ይሖዋ፣ ሕዝቡ ከጭቆና የሚገላገልበት መንገድ አዘጋጅቶ ነበር።

8. በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ ሕዝቦች ምን ዓይነት ፈታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል?

8 በዛሬው ጊዜም ቢሆን ጭቆናና የፍትሕ መጓደል ተስፋፍቷል። መክብብ 8:9 “ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዥ የሚሆንበት ጊዜ አለ” በማለት ይናገራል። ስግብግብ የሆነው የንግድ ሥርዓትና ምግባረ ብልሹነት የሚታይበት አገዛዝ የኢኮኖሚ ድቀት እንዲኖር ሊያደርግ ይችላል። የመንግሥት ባለ ሥልጣናት እንዲሁም በንግዱ ዓለም ትልቅ ቦታ ያላቸው ሰዎችና የሃይማኖት መሪዎች አብዛኛውን ጊዜ በሥነ ምግባር ረገድ መጥፎ ምሳሌ ናቸው። በዚህም የተነሳ በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች እንደ ጻድቁ ሎጥ ‘በዐመፀኞች ሴሰኛ ድርጊት እየተሣቀቁ’ ይኖራሉ። (2 ጴጥ. 2:7) ከዚህም በተጨማሪ ማንንም ሳይነኩ በአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እየተመሩ ለመኖር ቢጥሩም ብዙውን ጊዜ እብሪተኛ የሆኑ ገዢዎች የጥቃት ዒላማ ይሆናሉ።—2 ጢሞ. 3:1-5, 12

9. (ሀ) ይሖዋ፣ ሕዝቦቹን ከጭቆና ነፃ ለማውጣት የሚያስችል ምን እርምጃ ወስዷል? (ለ) ኢየሱስ ምንጊዜም ቢሆን ለአምላክ ታማኝ እንደሚሆን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

9 ያም ቢሆን እርግጠኛ መሆን የምንችልበት አንድ መሠረታዊ እውነት አለ:- ይሖዋ ታማኞቹን አይጥልም! ምግባረ ብልሹ በሆኑት የዓለም የፖለቲካ መሪዎች ምትክ ሌላ አገዛዝ ለማቋቋም የወሰዳቸውን እርምጃዎች ብቻ እንኳ ለማሰብ ሞክር። በክርስቶስ ኢየሱስ የሚመራው የአምላክ መሲሐዊ መንግሥት ተቋቁሟል። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ መቶ ለሚጠጉ ዓመታት በሰማይ ሲገዛ ቆይቷል። በቅርቡ ደግሞ የአምላክን ስም ለሚፈሩ ሁሉ የተሟላ እፎይታ ያመጣላቸዋል። (ራእይ 11:15-18ን አንብብ።) ኢየሱስ እስከ ሞት ድረስ ለአምላክ ታማኝ መሆኑን አስመስክሯል። ሰሎሞን ካደረገው በተቃራኒ ኢየሱስ ተገዢዎቹን በፍጹም አያሳዝናቸውም።—ዕብ. 7:26፤ 1 ጴጥ. 2:6

10. (ሀ) ለአምላክ መንግሥት ትልቅ ቦታ እንደምንሰጠው እንዴት ማሳየት እንችላለን? (ለ) ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

10 የአምላክ መንግሥት ሁሉንም ዓይነት ጭቆና የሚያስወግድ እውን መስተዳድር ነው። እኛም ለይሖዋም ሆነ ለመንግሥቱ ታማኝ መሆን ይኖርብናል። በአምላክ መንግሥት ላይ ሙሉ እምነት በመጣል በዓለም ላይ የሚታየውን በኃጢአት የመኖር ዝንባሌ ክደን መልካም ለማድረግ እንተጋለን። (ቲቶ 2:12-14) የዚህ ዓለም ነውር እንዳይኖርብን እንጠነቀቃለን። (2 ጴጥ. 3:14) በአሁኑ ጊዜ ምንም ዓይነት ፈተናዎች ቢያጋጥሙንም ይሖዋ ከመንፈሳዊ ጉዳት እንደሚጠብቀን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (መዝሙር 97:10ን አንብብ።) ከዚህም በተጨማሪ  መዝሙር 116:15 “የቅዱሳኑ ሞት፣ በእግዚአብሔር ፊት የተከበረ” እንደሆነ ማረጋገጫ ይሰጠናል። ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ ለእሱ በጣም ውድ በመሆናቸው በቡድን ደረጃ እንዲጠፉ አይፈቅድም።

ከሃዲዎች ተጽዕኖ ሲያደርጉባቸው

11. ኢዮርብዓም ታማኝነቱን ያጎደለው እንዴት ነበር?

11 የንጉሥ ኢዮርብዓም አገዛዝ ለአምላክ ሕዝቦች በተወሰነ መጠን እፎይታ ሊያመጣላቸው ይችል ነበር። ከዚህ በተቃራኒ ግን ኢዮርብዓም የወሰደው እርምጃ ለአምላክ ያላቸውን ታማኝነት ይበልጥ የሚፈትን ነበር። ኢዮርብዓም ባገኘው ክብርና የንግሥና መብት ከመርካት ይልቅ ሥልጣኑን የሚያጠናክርበት መንገድ መፈለግ ጀመረ። ንጉሡ እንዲህ ሲል አሰበ:- “ይህ ሕዝብ መሥዋዕት ለማቅረብ ኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚወጣ ከሆነ፣ እንደ ገና ልቡን ወደ ጌታው ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሮብዓም ሊያዞር ነው። ከዚያም እኔን ይገድለኛል፤ ወደ ንጉሡም ወደ ሮብዓም ይመለሳል።” ስለዚህ ኢዮርብዓም ሁለት የወርቅ ጥጃዎች ካሠራ በኋላ እነዚህ ጥጃዎች የሚመለኩበት አዲስ ሃይማኖት አቋቋመ። “አንዱን በቤቴል ሌላውንም በዳን አቆመው። ይህም አድራጎት ኀጢአት ሆነ፤ ሕዝቡም በዚያ ላለው ለመስገድ እስከ ዳን ድረስ ርቆ ሄደ። ኢዮርብዓም በማምለኪያ ኰረብቶች ላይ አብያተ ጣዖታትን ሠራ፤ ከሕዝቡ የተለያዩ ክፍሎች ሁሉ፣ ሌዋውያን ካልሆኑት ካህናትን ሾመ።” ሌላው ቀርቶ ኢዮርብዓም ራሱ በመረጠው ቀን ‘ለእስራኤላውያን በዓል የወሰነላቸው’ ከመሆኑም በላይ ‘ዕጣን ለማቅረብ ወደ መሠዊያው ወጥቷል።’—1 ነገ. 12:26-33

12. ኢዮርብዓም በእስራኤል የጥጃ አምልኮ ሲያቋቁም በሰሜናዊው መንግሥት ሥር የሚኖሩ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ምን አደረጉ?

12 በሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት ሥር የሚኖሩ ታማኝ የአምላክ ሕዝቦች በዚህ ወቅት ምን ያደርጉ ይሆን? በሰሜናዊው መንግሥት ግዛት ሥር በተሰጣቸው ከተሞች ውስጥ ይኖሩ የነበሩት ሌዋውያን፣ ታማኝ የነበሩትን የቅድመ አያቶቻቸውን ምሳሌ በመከተል ወዲያውኑ እርምጃ ወሰዱ። (ዘፀ. 32:26-28፤ ዘኍ. 35:6-8፤ ዘዳ. 33:8, 9) እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች ርስታቸውን በመተው፣ ቤተሰባቸውን ይዘው ያለምንም ችግር ይሖዋን ማምለክ ወደሚችሉባት በስተ ደቡብ ወደምትገኘው ወደ ይሁዳ ሄዱ። (2 ዜና 11:13, 14) ለጊዜው በይሁዳ ይኖሩ የነበሩ ሌሎች እስራኤላውያንም በሰሜናዊው መንግሥት ሥር ወደሚገኘው ቤታቸው ከመመለስ ይልቅ በቋሚነት በዚያው ለመኖር ወሰኑ። (2 ዜና 10:17) ይሖዋ፣ ከዚያ በኋላ ባሉት ትውልዶችም በሰሜናዊው መንግሥት ሥር የሚኖሩ ሰዎች የጥጃ አምልኮን ትተው ወደ ይሁዳ በመመለስ እውነተኛውን አምልኮ መከተል ቢፈልጉ መንገዱ ክፍት እንዲሆንላቸው አድርጓል።—2 ዜና 15:9-15

13. በዘመናችን ከሃዲዎች የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ለአምላክ ሕዝቦች ፈተና የሆነባቸው እንዴት ነው?

13 በዘመናችንም ቢሆን ከሃዲዎችና እነሱ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ስጋት ይፈጥራሉ። አንዳንድ ገዢዎች የራሳቸውን የመንግሥት ሃይማኖት የሚያቋቁሙ  ሲሆን ተገዢዎቻቸውም ይህንን ሃይማኖት እንዲቀበሉ ተጽዕኖ ያደርጉባቸዋል። የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስትና ሌሎች ትዕቢተኛ ሰዎች የመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ካህናት እንደሆኑ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ “የንጉሥ ካህናት” የሚሆኑት ትክክለኛዎቹ ቅቡዓን የሚገኙት በእውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል ብቻ ነው።—1 ጴጥ. 2:9፤ ራእይ 14:1-5

14. ከሃዲዎች የሚያፈልቋቸውን ሐሳቦች በተመለከተ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

14 በአሥረኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደነበሩት ታማኝ ሌዋውያን ሁሉ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮችም ከሃዲዎች በሚያፈልቋቸው ሐሳቦች አይታለሉም። ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆኑ የእምነት ባልንጀሮቻቸው ከሃዲዎች ከሚያፈልቋቸው ሐሳቦች ለመራቅ እንዲሁም ሐሳባቸውን ላለመቀበል ፈጣን እርምጃ ይወስዳሉ። (ሮሜ 16:17ን አንብብ።) ከአምልኮ ጋር ባልተያያዙ ጉዳዮች ረገድ ለመንግሥት ባለ ሥልጣናት በፈቃደኝነት የምንገዛ ቢሆንም በዓለም ላይ በሚነሱ ግጭቶች ውስጥ አንካፈልም፤ እንዲሁም ለአምላክ መንግሥት ታማኝ እንሆናለን። (ዮሐ. 18:36፤ ሮሜ 13:1-8) አምላክን እንደሚያገለግሉ እየተናገሩ በተግባራቸው የሚያዋርዱት ሰዎች የሚያቀርቧቸውን ሐሰተኛ ሐሳቦች አንቀበልም።—ቲቶ 1:16

15. ‘ለታማኝና ልባም ባሪያ’ ታማኝ መሆን የሚገባን ለምንድን ነው?

15 ይሖዋ፣ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በምሳሌያዊ አነጋገር ከዚህ ክፉ ዓለም ወጥተው እሱ ወደፈጠረው መንፈሳዊ ገነት መግባት እንዲችሉ ለመርዳት ስላደረገው ዝግጅትም አስብ። (2 ቆሮ. 12:1-4) ለእነዚህ ዝግጅቶች አመስጋኝ መሆናችን ‘ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሾመውን ታማኝና ልባም ባሪያ’ እንድንከተል ያነሳሳናል። ክርስቶስ ይህንን ባሪያ “ባለው ሁሉ ላይ” ሾሞታል። (ማቴ. 24:45-47 የ1954 ትርጉም) በመሆኑም ታማኝና ልባም ባሪያ የሚወስደው አቋም በግለሰብ ደረጃ ሙሉ በሙሉ ባይገባንም እንኳ ይህ መሆኑ ባሪያው የወሰደውን አቋም እንዳንቀበል ወይም ወደ ሰይጣን ዓለም እንድንመለስ ምክንያት ሊሆነን አይገባም። ከዚህ በተቃራኒ ታማኝነት፣ ይሖዋ ነገሮችን ግልጽ እስኪያደርግልን ድረስ በትሕትና እሱን እንድንጠብቅ ይረዳናል።

አምላክ የሰጣቸውን ተልእኮ ሲወጡ

16. ከይሁዳ የመጣው ነቢይ ምን ተልእኮ ተሰጥቶት ነበር?

16 ኢዮርብዓም የክህደት ጎዳና በመከተሉ ይሖዋ አውግዞታል። ይሖዋ፣ አንድን ነቢይ ከይሁዳ ተነስቶ በስተ ሰሜን ወደምትገኘው ወደ ቤቴል በመሄድ ኢዮርብዓም በመሠዊያው ላይ የአምልኮ ሥነ ሥርዓት በሚያከናውንበት ጊዜ መልእክት እንዲነግረው አዝዞት ነበር። ነቢዩ ለኢዮርብዓም አስደንጋጭ የፍርድ መልእክት መናገር ነበረበት። ይህ ደግሞ ድፍረት የሚጠይቅ ተልእኮ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም።—1 ነገ. 13:1-3

17. ይሖዋ፣ መልእክተኛውን ከጉዳት የጠበቀው እንዴት ነበር?

17 ኢዮርብዓም፣ ይሖዋ እንዳወገዘው ሲሰማ ክፉኛ ተቆጣ። ከዚያም የይሖዋ ተወካይ ወደሆነው ሰው እጁን በመዘርጋት፣ “ያዙት!” በማለት ጮኸ! ይሁንና ማንም ሰው ነቢዩን ለመያዝ ከመሞከሩ በፊት “ያች የዘረጋት እጁ ደርቃ ቀረች፤ ሊመልሳትም አልቻለም። እንዲሁም . . . መሠዊያው ተሰነጠቀ፤ ዐመዱም ፈሰሰ።” በዚህ ወቅት ኢዮርብዓም የደረቀው እጁ ወደ ቦታው እንዲመለስ ይሖዋን እንዲለምንለት ነቢዩን መጠየቅ ግድ ሆነበት። ነቢዩ ወደ ይሖዋ የጸለየ ሲሆን የንጉሡም እጅ ወደ ቦታው ተመለሰ። በዚህ መንገድ ይሖዋ መልእክተኛውን ጉዳት እንዳይደርስበት ጠብቆታል።—1 ነገ. 13:4-6

18. ይሖዋ፣ ያለ ፍርሃት ለእሱ ቅዱስ አገልግሎት ስናቀርብ ጥበቃ የሚያደርግልን እንዴት ነው?

18 ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በታማኝነት ስንካፈል አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ጥሩ ምላሽ አይሰጡን ወይም ይቃወሙን ይሆናል። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) ያም ቢሆን ተቀባይነት አጣለሁ የሚለው ፍርሃት ለአገልግሎት ያለንን ቅንዓት እንዲያቀዘቅዝብን መፍቀድ የለብንም። በኢዮርብዓም ዘመን እንደነበረው ስሙ ያልተጠቀሰ ነቢይ እኛም ‘ያለ ፍርሀት በቅድስና [“በታማኝነት” NW]’ ይሖዋን የማገልገል  መብት አለን። * (ሉቃስ 1:74, 75) በዘመናችን ይሖዋ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ይጠብቀናል ብለን ባንጠብቅም ምሥክሮቹ እንደመሆናችን መጠን በቅዱስ መንፈሱ እንዲሁም በመላእክቱ አማካኝነት ጥበቃ እያደረገልንና እየደገፈን ነው። (ዮሐንስ 14:15-17ን እና ራእይ 14:6ን አንብብ።) አምላክ በድፍረት ቃሉን የሚያውጁ ሰዎችን ፈጽም አይተዋቸውም።—ፊልጵ. 1:14, 28

ይሖዋ ታማኞቹን ይጠብቃል

19, 20. (ሀ) ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይተወን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የትኞቹ ጥያቄዎች ይብራራሉ?

19 አምላካችን ይሖዋ ታማኝ አምላክ ነው። (መዝ. 18:25) “በሥራውም ሁሉ ቸር” ወይም ታማኝ ነው። (መዝ. 145:17) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ‘የታማኞቹንም አካሄድ እንደሚያጸና’ ወይም እንደሚጠብቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማረጋገጫ ተሰጥቶናል። (ምሳሌ 2:8) የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች፣ ፈተናዎች ሲያጋጥሟቸውም ሆነ ከሃዲዎች ተጽዕኖ ሲያደርጉባቸው አሊያም አስቸጋሪ የሆነ ተልእኮ ሲሰጣቸው የይሖዋ መመሪያና ድጋፍ እንደማይለያቸው መተማመን ይችላሉ።

20 እንግዲያው እያንዳንዳችን ልናስብበት የሚገባው ነጥብ ‘ምንም ዓይነት ተቃውሞ ወይም ፈተና ቢያጋጥመኝ ለይሖዋ ታማኝ ሆኜ እንድጸና ምን ሊረዳኝ ይችላል?’ የሚለው ነው። በሌላ አባባል፣ ‘ለአምላክ ታማኝ እንድሆን አቋሜን ማጠናከር የምችለው እንዴት ነው?’ ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.18 ይህ ነቢይ እስከ መጨረሻው ይሖዋን መታዘዝ አለመታዘዙን እንዲሁም ምን እንዳጋጠመው በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ እንመረምራለን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ይሖዋ፣ ታማኝ አገልጋዮቹ በጭቆና ሥር በሚሆኑበት ጊዜ እንደማይጥላቸው ያሳየው እንዴት ነው?

• ከሃዲዎችንና የሚያፈልቁትን ሐሳብ በተመለከተ ምን እርምጃ ልንወስድ ይገባል?

• ይሖዋ፣ ታማኝ አገልጋዮቹ በክርስቲያናዊው አገልግሎት በሚካፈሉበት ወቅት ጥበቃ የሚያደርግላቸው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሰሜናዊው መንግሥት (ኢዮርብዓም)

ዳን

ሴኬም

ቤቴል

ደቡባዊው መንግሥት (ሮብዓም)

ኢየሩሳሌም

[ሥዕሎች]

ኢዮርብዓም የጥጃ አምልኮ ባቋቋመበት ጊዜ ይሖዋ ታማኞቹን አልተዋቸውም

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰሎሞንም ሆነ ተገዢዎቹ ያገኙት በረከት ቀጣይ እንዲሆን ማሟላት የሚገባቸው ነገር ነበር