በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ምክንያታዊ በመሆን ደስታ ማግኘት

ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ምክንያታዊ በመሆን ደስታ ማግኘት

 ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ምክንያታዊ በመሆን ደስታ ማግኘት

“አሁንም አልተሳካልኝም!” ለማድረግ ያቀድከውን ነገር ማከናወን ባለመቻልህ እንደዚህ ያልክበት ጊዜ አለ? ወጣት የሆነች አንዲት ክርስቲያን እናት፣ አራስ ልጇን የመንከባከቡ ኃላፊነት ፋታ ስለማይሰጣትና ለመንፈሳዊ ነገሮች የበለጠ ትኩረት መስጠት አለመቻሏ ስለሚያበሳጫት ከላይ እንደተገለጸው በማለት ትናገር ይሆናል። አንድ ሌላ ክርስቲያን ደግሞ በአስተዳደጉ ምክንያት ብቃት እንደሌለው ስለሚሰማው በጉባኤ ውስጥ የሚያከናውነው ነገር ምንጊዜም ቢሆን በቂ እንዳልሆነ ያስብ ይሆናል። አንዲት አረጋዊት እህት የበለጠ ጉልበት በነበራቸውና እንደ ልብ መንቀሳቀስ በሚችሉበት ጊዜ ያደርጉት እንደነበረው በሚወዷቸው ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች የሚፈልጉትን ያህል ተሳትፎ ማድረግ ባለመቻላቸው ያዝኑ ይሆናል። የቤተሰቧ ሁኔታ በይሖዋ አገልግሎት የምትፈልገውን ያህል እንዳትካፈል የሚያግዳት ክርስቲያን የተባለች እህት “አቅኚ መሆንን የሚያበረታታ ንግግር እንኳ አንዳንድ ጊዜ ያስለቅሰኛል” ብላለች።

እንዲህ ዓይነት ስሜት ሲሰማን ምን ማድረግ እንችላለን? አንዳንድ ክርስቲያኖች ስላሉበት ሁኔታ ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት ማዳበር የቻሉት እንዴት ነው? እንደዚህ ዓይነት አመለካከት መያዝ ምን ጥቅሞች አሉት?

ምክንያታዊ ሁን

ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት በተናገረበት ወቅት ደስታችንን እንዳናጣ የሚረዳንን ነጥብ ጠቁሞናል:- “ምንጊዜም በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ። ገርነታችሁ [“ምክንያታዊነታችሁ፣ NW”] በሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን።” (ፊልጵ. 4:4, 5) ለአምላክ በምናቀርበው አገልግሎት ደስታና እርካታ ለማግኘት፣ ችሎታችንንና ሁኔታችንን ግምት ውስጥ በማስገባት ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ምክንያታዊ መሆን አለብን። የሚጠይቁብን መሥዋዕትነት ምንም ይሁን ምን ምክንያታዊነት እንደጎደለን የሚያሳዩ ግቦች የምናወጣ ከሆነ ራሳችንን አላስፈላጊ ውጥረት ውስጥ እንጨምራለን። በሌላ በኩል ደግሞ አቅማችንን እንደሚገድቡብን የምናስባቸውን ነገሮች ሰበብ በማድረግ በክርስቲያናዊው አገልግሎት የምናደርገውን ተሳትፎ ከሚገባው በላይ እንዳንቀንስ መጠንቀቅ አለብን።

ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ ይሖዋ ምርጣችንን እንድንሰጠው ማለትም በሙሉ ነፍሳችንና በሙሉ ልባችን እንድናገለግለው ይጠብቅብናል። (ቈላ. 3:23, 24) ለይሖዋ ምርጣችንን የማንሰጠው ከሆነ ራሳችንን ለእሱ ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን እየኖርን አይደለንም። (ሮሜ 12:1) ከዚህም በተጨማሪ በሙሉ ነፍስ ማገልገል የሚያስገኘውን ጥልቅ እርካታና እውነተኛ ደስታ እናጣለን፤ በሙሉ ነፍስ በማገልገል ልናገኛቸው የምንችላቸውን ሌሎች በረከቶችም ይቀሩብናል።—ምሳሌ 10:22

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ምክንያታዊነት” ተብሎ የተተረጎመው ቃል አሳቢነት ማሳየት የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ይህ ቃል በቀጥታ ሲተረጎም “እሺ ባይ” የሚል ፍቺ አለው። ከዚህም በተጨማሪ ቃሉ፣ ከመጠን በላይ ጥብቅ አለመሆን የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ስለዚህ ምክንያታዊ ከሆንን ሁኔታችንን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መገምገም እንችላለን። እንዲህ ማድረግ ከባድ ነው? አንዳንዶች ለሌሎች አሳቢነት የሚያሳዩ ቢሆንም ለራሳቸው እንዲህ ማድረግ ይከብዳቸዋል። ለአብነት ያህል፣ አንድ የቅርብ ጓደኛችን በጣም ብዙ ነገሮችን ስለሚሠራ የድካም ስሜት ቢታይበት በሕይወቱ ውስጥ አንዳንድ ማስተካከያዎች  የማድረግን አስፈላጊነት እንዲገነዘብ ልንረዳው አንሞክርም? በተመሳሳይ እኛም ከአቅማችን በላይ እየሠራን መሆኑን የሚጠቁሙ ምልክቶችን ማስተዋል መቻል አለብን።—ምሳሌ 11:17

ወላጆቻችን ሲያሳድጉን ከእኛ ብዙ ይጠብቁብን ከነበረ የአቅማችንን ውስንነት በመረዳት ረገድ ምክንያታዊ አመለካከት ማዳበር ፈታኝ ሊሆንብን ይችላል። አንዳንዶች ልጆች በነበሩበት ወቅት፣ ወላጆቻቸው እንዲወዷቸው ሁልጊዜ የበለጠ መሥራት ወይም የተሻሉ ሆነው መገኘት እንዳለባቸው ይሰማቸው ነበር። ያደግነው በእንደዚህ ዓይነት ቤተሰብ ውስጥ ከሆነ ይሖዋ ስለ እኛ ባለው አመለካከት ረገድ የተሳሳተ ግንዛቤ ይኖረን ይሆናል። ይሖዋ በሙሉ ልባችን የምናገለግለው ከሆነ ይወደናል። የአምላክ ቃል ይሖዋ “አፈጣጠራችንን ያውቃልና፤ ትቢያ መሆናችንንም ያስባል” የሚል የሚያበረታታ ሐሳብ ይዟል። (መዝ. 103:14) ይሖዋ ያሉብንን የአቅም ገደቦች የሚያውቅ ከመሆኑም በተጨማሪ እነዚህ የአቅም ገደቦች እያሉብንም እንኳ በቅንዓት የምናገለግለው ከሆነ ይወደናል። አምላካችን ጥብቅ የሆነ አሠሪ እንዳልሆነ ማስታወሳችን የአቅም ገደብ እንዳለብን በመገንዘብ ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ትሑት ወይም ሚዛናዊ እንድንሆን ይረዳናል።—ሚክ. 6:8

አንዳንድ ክርስቲያኖች አምላክ ከአቅማቸው በላይ እንደማይጠብቅባቸው ቢያውቁም ከላይ እንደተገለጸው ዓይነት ሚዛናዊ አመለካከት ማዳበር ያስቸግራቸዋል። አንተም በዚህ ረገድ የምትቸገር ከሆነ ስለ አንተ በደንብ የሚያውቅ ተሞክሮ ያለው አንድ ክርስቲያን እንዲረዳህ ለምን አትጠይቀውም? (ምሳሌ 27:9) ለምሳሌ ያህል፣ የዘወትር አቅኚ ሆነህ ማገልገል ትፈልጋለህ? ይህ በጣም ግሩም ግብ ነው! ሆኖም እዚህ ግብ ላይ መድረስ ከባድ ሆኖብሃል? ከሆነ ኑሮህን ቀላል በማድረግ ረገድ እርዳታ ያስፈልግህ ይሆናል። ወይም ደግሞ ካሉብህ በርካታ የቤተሰብ ኃላፊነቶች አንጻር የዘወትር አቅኚነት በዚህ ወቅት ልትደርስበት የምትችል ግብ መሆን አለመሆኑን መመርመር እንድትችል አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ጓደኛህ ይረዳህ ይሆናል። ይህ ጓደኛህ አቅኚነት የሚያስከትላቸውን ተጨማሪ ሥራዎች ማከናወን ትችል እንደሆነና እንዳልሆነ ወይም የትኞቹን ማስተካከያዎች ማድረግ በአገልግሎትህ የበለጠ ለመካፈል እንደሚያስችልህ እንድታስተውል ሊረዳህ ይችላል። አንዲት ሚስት የምትወስዳቸው እርምጃዎች አቅሟን ያገናዘቡ እንዲሆኑ ባሏ ከማንም በተሻለ ሊረዳት ይችላል። ለአብነት ያህል፣ ከወትሮው የበለጠ እንቅስቃሴ የሚኖርበት ወር ከመጀመሩ በፊት እረፍት እንድታደርግ ሐሳብ ሊያቀርብላት ይችላል። እንዲህ ማድረጓ ኃይሏ እንዲታደስና በአገልግሎቷም ደስተኛ ሆና እንድትቀጥል ይረዳታል።

ልታከናውናቸው በምትችላቸው ነገሮች ላይ ትኩረት አድርግ

የዕድሜ መግፋት ወይም የጤና እክል በይሖዋ አገልግሎት የምናደርገውን ተሳትፎ ሊገድብብን ይችላል። ወላጅ ከሆንክ፣ አብዛኛውን ጊዜህንና ኃይልህን ትንንሽ ልጆችህን ለመንከባከብ ስለምታውለው የግል ጥናት ማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነብህ ወይም ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ብዙም ጥቅም እንደማታገኝ ይሰማህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ባሉብህ የአቅም ገደቦች ላይ ትኩረት ማድረግህ ልታከናውናቸው የምትችላቸውን ነገሮች እንዳታስተውል አድርጎህ ይሆን?

በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የኖረ አንድ ሌዋዊ ሊያገኘው የማይችለውን ነገር ተመኝቶ ነበር። ይህ ሌዋዊ በየዓመቱ ለሁለት ሳምንታት በቤተ መቅደሱ ውስጥ የማገልገል  መብት ነበረው። ይሁንና ሁልጊዜ በመሠዊያው አጠገብ ለመኖር እንደሚፈልግ ገልጾ ነበር፤ እንዲህ ዓይነት ነገር መመኘቱ የሚደነቅ ነው። (መዝ. 84:1-3) ታዲያ ይህ ታማኝ ሰው ባለው መብት እንዲረካ የረዳው ምን ነበር? ይህ ሌዋዊ በቤተ መቅደሱ አደባባይ አንዲት ቀን እንኳ መዋል ልዩ መብት እንደሆነ ተገንዝቧል። (መዝ. 84:4, 5, 10) እኛም በተመሳሳይ ከአቅማችን በላይ የሆኑትን ነገሮች በማሰብ ከመብሰልሰል ይልቅ ልናከናውናቸው የምንችላቸውን ነገሮች ማስተዋልና እነዚህንም ማድረግ በመቻላችን አመስጋኞች መሆን ይገባናል።

በካናዳ የሚኖሩትን ኔርላንድ የተባሉ እህት እንደ ምሳሌ እንመልከት። ያለ ተሽከርካሪ ወንበር መንቀሳቀስ ስለማይችሉ በአገልግሎት የሚያደርጉት ተሳትፎ በጣም ውስን እንደሆነ ይሰማቸው ነበር። ሆኖም አመለካከታቸውን በማስተካከል በአቅራቢያቸው የሚገኘውን የገበያ ማዕከል የአገልግሎት ክልላቸው እንደሆነ አድርገው መመልከት ጀመሩ። እህት ኔርላንድ እንዲህ ብለዋል:- “በተሽከርካሪ ወንበሬ ላይ ሆኜ በገበያ ማዕከሉ ውስጥ በሚገኝ አግዳሚ ወንበር አጠገብ በመቀመጥ፣ አግዳሚ ወንበሩ ላይ አረፍ ለማለት ለሚመጡ ሰዎች መመሥከሬ ደስታ አስገኝቶልኛል።” እህት ኔርላንድ በዚህ ዓይነቱ ጠቃሚ የአገልግሎት ዘርፍ መካፈላቸው እርካታ አስገኝቶላቸዋል።

አስፈላጊ ከሆነ ማስተካከያ አድርግ

በነፋስ የሚንቀሳቀስ አንድ ጀልባ፣ ያለ ምንም ችግር እየነጎደ ነው እንበል። ይሁንና ኃይለኛ ማዕበል ሲመጣ መርከበኛው ሸራውን ለማስተካከል ይገደዳል። መርከበኛው ማዕበሉን መቆጣጠር ባይችልም አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማድረግ ጀልባው ከቁጥጥሩ ውጭ እንዳይሆን ማድረግ ይችላል። በተመሳሳይም ብዙውን ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን እንደ ማዕበል ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች መቆጣጠር አንችልም። ያም ቢሆን ከአካላችን፣ ከአእምሯችንና ከስሜታችን ጋር በተያያዘ ሁኔታዎቻችንን በማስተካከል በተወሰነ መጠን ሕይወታችንን መቆጣጠር እንችላለን። አሁን ያለንበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ ማስገባታችን በአምላክ አገልግሎት የምናገኘውን እርካታና ደስታ እንዳናጣ ያደርገናል።—ምሳሌ 11:2

እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት። ብዙም ኃይል እንደሌለን የሚሰማን ከሆነ፣ ምሽት ላይ በሚደረገው ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ ለመገኘት የሚያስችል አቅም እንዲኖረን በቀኑ ውስጥ ጉልበታችንን የሚያሟጥጡ ነገሮች አለማከናወናችን ጥሩ ይሆናል። እንዲህ ማድረጋችን ከስብሰባው ሙሉ በሙሉ መጠቀም እንድንችል ይረዳናል። ወይም ደግሞ አንዲት እናት ልጇ ስለታመመ ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ባትችል አንዲትን እህት ቤቷ በመጋበዝ ልጁ ሲተኛ በስልክ መመሥከር ይችሉ ይሆናል፤ አሊያም እህት ጥናቶቿን ይዛ ወደ ቤቷ እንድትመጣ በመጠየቅ አብረው ሊያስጠኑ ይችላሉ።

በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡትን ትምህርቶች በሙሉ ቀደም ብለህ ለመዘጋጀት ሁኔታህ የማይፈቅድልህ  ቢሆንስ? ካለህበት ሁኔታ አንጻር ምን ያህሉን ትምህርት መዘጋጀት እንደምትችል ካገናዘብክ በኋላ ያንን በተቻለህ መጠን በደንብ ተዘጋጀው። በአጭር ጊዜ ግቦቻችን ላይ ማስተካከያ በማድረግ በመንፈሳዊ ንቁና ደስተኞች ሆነን መቀጠል እንችላለን።

እርግጥ ነው፣ በግቦቻችን ላይ ማስተካከያ ለማድረግ ቆራጥ መሆንና ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። በፈረንሳይ የሚኖሩት ሰርዥ እና አንዬስ የተባሉ ባልና ሚስት በእቅዳቸው ላይ ትልቅ ማስተካከያ ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር። ሰርዥ እንደዚህ በማለት ተናግሯል:- “አንዬስ እርጉዝ መሆኗን ስናውቅ ሚስዮናውያን የመሆን ሕልማችን እንደማይሳካ ተገነዘብን።” በአሁኑ ጊዜ፣ ደስተኛ የሆኑ ሁለት ሴት ልጆች ያሉት ሰርዥ እሱና ባለቤቱ ስላወጡት አዲስ ግብ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ወደ ሌላ አገር ሄደን መስበክ ባንችልም በአገራችን ‘ሚስዮናውያን’ ሆነን ለማገልገል ወሰንን። በውጭ አገር ቋንቋ በሚመራ ቡድን ውስጥ ማገልገል ጀመርን።” እንደዚህ ዓይነት አዲስ ግብ በማውጣታቸው ተጠቅመዋል? ሰርዥ “ጠቃሚ አስተዋጽኦ እያበረከትን እንዳለን ይሰማናል” ብሏል።

በ70ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙት ኦዲል የተባሉ በፈረንሳይ የሚኖሩ እህት አርትራይትስ በተባለው በሽታ ምክንያት ጉልበታቸውን ስለሚያማቸው ብዙ መቆም አይችሉም። በሕመማቸው ምክንያት ከቤት ወደ ቤት ሄደው ማገልገል ባለመቻላቸው ያዝኑ ነበር። ሆኖም እኚህ እህት ፈጽሞ ተስፋ አልቆረጡም። ይልቁንም በመንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸው ላይ ማስተካከያ በማድረግ በስልክ መመስከር ጀመሩ። “ካሰብኩት በላይ ቀላልና አስደሳች ነው!” በማለት ተናግረዋል። እህት ኦዲል እንዲህ ማድረጋቸው እንደ ቀድሞው በአገልግሎታቸው እንዲደሰቱ አድርጓቸዋል።

ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ምክንያታዊ መሆን በረከት ያስገኛል

ማከናወን ስለምንችለው ነገር ምክንያታዊ አመለካከት ማዳበራችን ከሐዘን ይጠብቀናል። ሚዛናዊ የሆኑ ግቦችን ማውጣታችን የአቅም ገደቦች እያሉን እንኳ ስኬታማ እንደሆንን እንዲሰማን ያደርጋል። በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ የምናከናውነው ነገር አነስተኛ ቢሆንም ማድረግ በቻልነው ነገር መደሰት እንችላለን።—ገላ. 6:4

ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ሚዛናዊ በሆንን መጠን ለክርስቲያን ባልንጀሮቻችንም ይበልጥ አሳቢ እንሆናለን። የአቅም ገደቦች እንዳሉባቸው ስለምንገነዘብ ምንጊዜም ቢሆን ላደረጉልን ነገር አመስጋኝ እንሆናለን። ሌሎች የሚያደርጉትን ማንኛውንም እርዳታ ማድነቃችን በጉባኤ ውስጥ የትብብር መንፈስ እንዲኖርና ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር እርስ በርስ እንድንግባባ ያደርጋል። (1 ጴጥ. 3:8) ምንጊዜም ቢሆን አፍቃሪ አባታችን የሆነው ይሖዋ ልንሰጠው ከምንችለው በላይ እንደማይጠይቀን አስታውስ። እኛም ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ሚዛናዊ አመለካከት ካዳበርንና ልንደርስባቸው የምንችላቸው ግቦች ካወጣን የምናከናውናቸው መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የበለጠ እርካታና ደስታ ያስገኙልናል።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ለአምላክ በምናቀርበው አገልግሎት ደስታና እርካታ ለማግኘት፣ ችሎታችንንና ሁኔታችንን ግምት ውስጥ በማስገባት ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ምክንያታዊ መሆን አለብን

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እህት ኔርላንድ በአገልግሎታቸው ማከናወን የሚችሉትን ያህል በማድረጋቸው ደስታ አግኝተዋል

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ሸራውን ማስተካከል” ተማር

[ምንጭ]

© Wave Royalty Free/age fotostock

[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰርዥና አንዬስ አዲስ ግብ በማውጣታቸው ተጠቅመዋል