በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የበላይ አካሉ አደረጃጀት

የበላይ አካሉ አደረጃጀት

 የበላይ አካሉ አደረጃጀት

የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል፣ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ቅቡዓን ወንዶችን ያቀፈ ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች ታማኝና ልባም ባሪያን ወክለው ይሠራሉ፤ ይህ ባሪያ መንፈሳዊ ምግብ የማቅረብ እንዲሁም በመላው ምድር የሚካሄደውን ስለ አምላክ መንግሥት የመስበክ ሥራ የመምራትና ይህ ሥራ ቅድሚያ እንዲሰጠው የማድረግ ኃላፊነት አለበት።—ማቴ. 24:14, 45-47

የበላይ አካሉ አባላት በየሳምንቱ ስብሰባ የሚያደርጉ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ስብሰባው የሚያካሄደው ረቡዕ ነው። እነዚህ ወንድሞች እንዲህ ማድረጋቸው በአንድነት መሥራት እንዲችሉ ይረዳቸዋል። (መዝ. 133:1) የበላይ አካሉ አባላት በተለያዩ ኮሚቴዎች ውስጥም ያገለግላሉ። ከዚህ በታች አጠር ባለ መንገድ እንደተገለጸው እያንዳንዱ ኮሚቴ ከአምላክ መንግሥት የስብከት ሥራ ጋር በተያያዘ በበላይነት የሚከታተለው የራሱ ምድብ አለው።

የአስተባባሪዎች ኮሚቴ:- ይህ ኮሚቴ፣ በእያንዳንዱ የበላይ አካል ኮሚቴ ውስጥ አስተባባሪ ሆነው የሚያገለግሉትን ወንድሞች እንዲሁም የበላይ አካሉ አባል የሆነውን ጸሐፊ ያቀፈ ነው። የአስተባባሪው ኮሚቴ ሁሉም ኮሚቴዎች ሥራቸውን ያለምንም ችግር በተቀላጠፈ ሁኔታ ማከናወን እንዲችሉ ይረዳቸዋል። በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ድንገተኛ ሁኔታዎች፣ ስደት፣ አደጋዎች እንዲሁም ሌሎች አጣዳፊ ነገሮች ሲያጋጥሟቸው እርዳታ መስጠት የሚቻልባቸውን መንገዶች ያመቻቻል።

የፐርሶኔል ኮሚቴ:- በዚህ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግሉት ወንድሞች፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የቤቴል ቤተሰብ አባላትን አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ደኅንነት የመከታተል እንዲሁም በሌሎች መንገዶች የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች የማሟላት ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። ይህ ኮሚቴ አዳዲስ የቤቴል ቤተሰብ አባላትን የመምረጡንና ወደ ቤቴል የመጥራቱን ሥራ በበላይነት ይከታተላል፤ እንዲሁም ቤቴላውያን ከሚያከናውኑት አገልግሎት ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

የኅትመት ኮሚቴ:- ይህ ኮሚቴ በዓለም ዙሪያ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን የማተሙንና የማሠራጨቱን ሂደት በበላይነት ይከታተላል። ኮሚቴው የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ ኮርፖሬሽኖች ንብረት የሆኑትንና እነዚህ ኮርፖሬሽኖች የሚያንቀሳቅሷቸውን የኅትመት መሣሪያዎች እንዲሁም ሌሎች ነገሮች ይቆጣጠራል። ለዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ የሚደረጉት መዋጮዎች በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉም ያደርጋል።

የአገልግሎት ኮሚቴ:- በዚህ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግሉት ወንድሞች የስብከቱን ሥራ እንዲሁም ከጉባኤዎች፣ ከአቅኚዎች፣ ከሽማግሌዎችና ከተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በበላይነት ይከታተላሉ። ኮሚቴው የመንግሥት አገልግሎታችን እንዲዘጋጅ ያደርጋል፤ በተጨማሪም በጊልያድና በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የሚካፈሉ ተማሪዎችን ይጋብዛል እንዲሁም ወደ ተለያዩ ቦታዎች ይመድባል።

የትምህርት ኮሚቴ:- ይህ ኮሚቴ በልዩ፣ በወረዳ፣ በአውራጃና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡትን ትምህርቶች ይከታተላል። ለቤቴል ቤተሰብ አባላት መንፈሳዊ ምግብ የሚያዘጋጅ ከመሆኑም ሌላ እንደ ጊልያድና የአቅኚዎች የአገልግሎት ትምህርት ቤት የመሳሰሉ ትምህርት ቤቶችን በበላይነት ይቆጣጠራል። ከዚህም በላይ በድምፅ ብቻና በቪዲዮ የተቀረጹ ፕሮግራሞችን ያዘጋጃል።

የጽሑፍ ዝግጅት ኮሚቴ:- የዚህ ኮሚቴ ኃላፊነት መንፈሳዊ ምግብ በጽሑፍ መልክ ማዘጋጀትና ለይሖዋ ምሥክሮችም ሆነ ለሌሎች ሰዎች እንዲደርስ ማድረግ ነው። ኮሚቴው ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ ከመሆኑም ሌላ እንደ ድራማ ጽሑፍና የንግግር አስተዋጽኦ የመሳሰሉ ነገሮች ያጸድቃል። ከዚህም በተጨማሪ በዓለም ዙሪያ የሚካሄደውን የትርጉም ሥራ ይከታተላል።

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የቅቡዓን ክርስቲያኖችን ጉባኤ ከሰው አካል ጋር ያመሳሰለው ሲሆን ሁሉም ክፍሎች አምላክ የሰጣቸውን ሥራ በማከናወን ረገድ የሚጫወቱትን ጠቃሚ ሚና እንዲሁም እያንዳንዳቸው አስፈላጊ እንደሆኑ፣ እርስ በርስ እንደሚዋደዱና እንደሚተባበሩ ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ሮሜ 12:4, 5፤ 1 ቆሮ. 12:12-31) ራስ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የአካሉ አባላት እርስ በርስ እንዲተባበሩ የሚረዳቸው ከመሆኑም በላይ መንፈሳዊ ምግብ ያቀርብላቸዋል። (ኤፌ. 4:15, 16፤ ቈላ. 2:19) በዚህ መንገድ የተደራጀው የበላይ አካል በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ እየተመራ ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በግንባር ቀደምትነት ያከናውናል።