በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጣም አስፈላጊ የሆነ ቀጠሮ

በጣም አስፈላጊ የሆነ ቀጠሮ

 በጣም አስፈላጊ የሆነ ቀጠሮ

በጣም አስፈላጊ የሆነ ቀጠሮ አለኝ። በወጣትነት ዕድሜ ላይ የምገኝ ስፔናዊት የልጆች እናት ነኝ፤ ይህን በጣም አስፈላጊ የሆነ ቀጠሮ የያዝኩት እንዴት እንደሆነ እስቲ ልንገራችሁ።

በወላጆቼ ቤት ውስጥ ሰላምና ስምምነት አልነበረም። ታናሽ ወንድሜ በአሳዛኝ አደጋ በአራት ዓመቱ ሲሞት ቤተሰባችን ከፍተኛ ሐዘን ላይ ወደቀ። ከዚህም በላይ የአባቴ መጥፎ ባሕርይ እናቴ በትዳሯ ብዙም ደስተኛ እንዳትሆን አድርጓት ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ እናቴ፣ እኔንም ሆነ ታላቅ ወንድሜን በሥነ ምግባር ኮትኩታ እንዳታሳድገን አላገዳትም።

ከጊዜ በኋላ እኔም ሆንኩ ወንድሜ ትዳር መሠረትን። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ እናቴ ካንሰር እንዳለባት የታወቀ ሲሆን ውሎ አድሮም ሕይወቷ አለፈ። እናቴ ከመሞቷ በፊት ግን ውድ ሀብት አውርሳናለች።

እናቴን የምታውቃት አንዲት ሴት፣ በቅዱስ ጽሑፉ ላይ የሚገኘውን የትንሣኤ ተስፋ የነገረቻት ሲሆን እናቴም መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣ ተቀበለች። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለው ተስፋ፣ እናቴ ልትሞት በተቃረበችበት ወቅት ሕይወቷ ትርጉም ያለው እንዲሆን ያደረገላት ከመሆኑም በላይ ደስተኛ እንድትሆን ረድቷታል።

እኔና ወንድሜ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በእናቴ ላይ ያሳደረውን በጎ ተጽዕኖ ስንመለከት የአምላክን ቃል ማጥናት ጀመርን። ሁለተኛዋን ልጄን ከመውለዴ ከአንድ ወር በፊት ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ፤ ይህችን ቆንጆ ልጅ ሉሲያ ብለን ስም አወጣንላት።

የተጠመቅኩበትን ዕለት ትልቅ ቦታ እሰጠዋለሁ። ይህን የምልበት አንደኛው ምክንያት ለዘላለም ይሖዋን ለማገልገል ራሴን ወስኜ የእሱ ንብረት በመሆኔ ነው። ሌላው ምክንያት ደግሞ ለምወዳቸው ወንድና ሴት ልጆቼ እምነቴን ማካፈል መቻሌ ነው።

ይሁን እንጂ እንድደሰት ያደረገኝ ሁለተኛው ምክንያት ብዙም አልዘለቀም። ሉሲያ አራት ዓመት ሲሆናት ከባድ የሆድ ሕመም ያሠቃያት ጀመር። ከብዙ ምርመራ በኋላ የራዲዮሎጂ ባለሞያው፣ ከጉበቷ ጋር የተጣበቀ የብርቱካን መጠን ያለው ዕጢ እንዳለ ነገረን። ሉሲያ፣ ኒውሮብላስቶማ የተባለ በከፍተኛ ፍጥነት የሚያድግ ወደ ካንሰርነት የተለወጠ ዕጢ እንዳላት ሐኪሙ ገለጸልን። ሉሲያ፣ ለሰባት ዓመታት ከካንሰር ጋር ያደረገችው ትግል በዚህ መንገድ ጀመረ፤ በእነዚህ ጊዜያት ለበርካታ ቀናት ሆስፒታል መተኛት አስፈልጓት ነበር።

የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ

ሉሲያ በእነዚህ አስቸጋሪ ዓመታት እቅፍ አድርጋ በመሳም ታበረታታኝ ነበር። ሉሲያ የነበረባትን ሕመም በተረጋጋ መንፈስ ለመቋቋም የምታደርገው ጥረት የሆስፒታሉን ሠራተኞች ጭምር አስገርሟል። ሉሲያ፣ በሆስፒታሉ ለሚገኙ ልጆች እርጎ፣ ጭማቂና ሌሎች ነገሮችን በመስጠቱ ሥራ ነርሶቹን ለመርዳት ትፈልግ ነበር። ነርሶቹም ከላይ የሚደርቡትን ነጭ ልብስና “ረዳት ነርስ” የሚል ደረት ላይ የሚለጠፍ ካርድ ሳይቀር ለሉሲያ ሰጥተዋት ነበር።

አንዲት የሆስፒታሉ ሠራተኛ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “የሉሲያ ሁኔታ ልቤን ነክቶታል። ፈጣን አእምሮ የነበራት ንቁ ልጅ ስትሆን ሥዕል መሳል ትወድ ነበር። ስሜቷን የምትገልጽ እንዲሁም አዋቂና በጣም የበሰለች ልጅ ነበረች።”

የአምላክ ቃል ለሉሲያ ጥንካሬ የሰጣት ሲሆን እንድትረጋጋም አስችሏታል። (ዕብ. 4:12) በአዲስ ዓለም ውስጥ ስለሚኖረው ሁኔታ የአምላክ ቃል እንደሚከተለው በማለት በሰጠው ተስፋ ላይ ጠንካራ እምነት ነበራት:- “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም።” (ራእይ 21:4) ሉሲያ ለሌሎች ሰዎች አሳቢ ስለነበረች የምታገኘውን አጋጣሚ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመናገር ትጠቀምበት ነበር። ምንም እንኳ ከሕመሟ ለመዳን የነበራት ተስፋ የመነመነ ቢሆንም በትንሣኤ ተስፋ ላይ የነበራት ጠንካራ እምነት ስሜቷን መቆጣጠር እንድትችልና ደስታዋን እንዳታጣ ረድቷታል።  (ኢሳ. 25:8) ሉሲያ በካንሰር ምክንያት እስከሞተችበት ዕለት ድረስ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ነበራት።

በጣም አስፈላጊ የሆነውን ቀጠሮ የያዝኩት በዚህ ዕለት ነበር። በዚያ ቀን ሉሲያ ዓይኗን እንኳ መግለጥ አቅቷት ነበር። እኔ አንድ እጇን አባቷ ደግሞ ሌላውን እጇን ይዘናት ነበር። ጠጋ ብዬ በቀስታ እንዲህ አልኳት:- “አይዞሽ፣ አልተውሽም። ቀስ እያልሽ ተንፍሺ። በትንሣኤ ስትነሺ ጤነኛ ትሆኛለሽ። ከዚያ በኋላ በሕመም አትሠቃዪም፤ እኔም ከአንቺ ጋር እሆናለሁ።”

ያን ጊዜ የያዝኩትን ቀጠሮ ጠብቄ መገኘት አለብኝ። እርግጥ ነው፣ እሷ የምትነሳበትን ጊዜ መጠበቅ ቀላል እንዳልሆነ አውቃለሁ። ሆኖም ይሖዋን ተማምኜ በትዕግሥት ከጠበቅኩትና ለእሱ ታማኝ ሆኜ ከተገኘሁ ሉሲያ በትንሣኤ ስትነሳ አጠገቧ እንደምሆን አውቃለሁ።

ሉሲያ የተወችልን ቅርስ

ሉሲያ የተወችው የድፍረት ምሳሌና የጉባኤው አባላት ያደረጉልን ግሩም ድጋፍ የይሖዋ ምሥክር ያልነበረውን ባለቤቴን በእጅጉ ነክቶታል። ሉሲያ በሞተችበት ዕለት፣ ባለቤቴ ነገሮችን እንደገና መመርመር እንደሚፈልግ ነገረኝ። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በጉባኤያችን ለሚገኝ አንድ ሽማግሌ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እንደሚፈልግ ነገረው። ብዙም ሳይቆይ ባለቤቴ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ። ከዚህ በፊት ሲጋራ ማቆም ፈልጎ ያቃተው ቢሆንም በዚህ ጊዜ ግን በይሖዋ እርዳታ ማጨሱን አቁሟል።

በሉሲያ ሞት የደረሰብኝ ሐዘን ሙሉ በሙሉ ከልቤ ባይጠፋም ሉሲያ ለተወችልን ቅርስ ይሖዋን በጣም አመሰግነዋለሁ። እኔና ባለቤቴ ግሩም በሆነው የትንሣኤ ተስፋ እርስ በርስ የምንጽናና ከመሆኑም በላይ ጎላ ብለው የሚታዩትን የሉሲያን ዓይኖችና ፈገግ ስትል ጉንጮቿ ላይ የሚታየውን ስርጉድ በማሰብ ሉሲያን እንደገና የምናገኝበትን ጊዜ በዓይነ ሕሊናችን እንስለዋለን።

በአካባቢያችን ትኖር የነበረች አንዲት የልጆች እናትም በልጄ ላይ በደረሰው መከራ የተለየ ሐዘን ተሰምቷት ነበር። አንድ ቅዳሜ ጠዋት ይህች ሴት ዝናብ እየዘነበ ቤታችን መጣች፤ ሴትየዋ ከሉሲያ ጋር አንድ ትምህርት ቤት የሚማር ልጅ ነበራት። እሷም 11 ዓመት የሆነውን ሌላ ወንድ ልጇን በዚሁ በሽታ አጥታለች። ይህች ሴት በሉሲያ ላይ የደረሰውን ስትሰማ የት እንደምንኖር አፈላልጋ ልትጠይቀን መጣች። በሉሲያ ሞት ከደረሰብኝ ሐዘን እየተጽናናሁ መሆኔን ጠየቀችኝ፤ እንዲሁም በዚህ ሁኔታ የሚገኙ ሌሎች እናቶችን ለማጽናናት እርስ በርስ የምንረዳዳበት ቡድን እንድናቋቁም ሐሳብ አቀረበችልኝ።

እኔም እውነተኛ መጽናኛ ያገኘሁት መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጠው ተስፋ እንደሆነና ይህ ደግሞ ማንኛውም ግለሰብ ሊሰጠው ከሚችለው በጣም የላቀ መሆኑን ገለጽኩላት። ኢየሱስ፣ በዮሐንስ 5:28, 29 ላይ የተናገረውን ሳነብላት ዓይኖቿ በደስታ አበሩ። መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የተስማማች ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ‘ከማስተዋል በላይ የሆነውን የእግዚአብሔርን ሰላም’ እያገኘች እንደሆነ ይሰማት ጀመር። (ፊልጵ. 4:7) መጽሐፍ ቅዱስን አንድ ላይ ስናጠና ብዙውን ጊዜ ቆም እንልና በአዲሱ ዓለም ውስጥ ልጆቻችንን በትንሣኤ ስንቀበል በዓይነ ሕሊናችን ለመመልከት እንሞክራለን።

አዎን፣ የሉሲያ አጭር ሕይወት ዘላለማዊ የሆነ ቅርስ ትቶልናል። የሉሲያ እምነት፣ ቤተሰባችን በአንድነት አምላክን እንዲያገለግል ያደረገ ከመሆኑም በላይ እኔም በእምነቴ ለመጽናት ያደረግኩትን ቁርጥ ውሳኔ ይበልጥ አጠናክሮልኛል። የሞቱ ዘመዶቻችን በትንሣኤ እንደሚነሱ ተስፋ የምናደርግ ሁሉ በጣም አስፈላጊ የሆነ ቀጠሮ እንዳለን ምንም ጥርጥር የለውም።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሉሲያ የሳለችው ገነትን የሚያሳይ ሥዕል