በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአንዲስ ተራሮች ምሥራቹን መስበክ

በአንዲስ ተራሮች ምሥራቹን መስበክ

 በአንዲስ ተራሮች ምሥራቹን መስበክ

ሥራ ስምንታችንም መሬት ላይ ተኝተናል። ለመኝታ በተዘጋጁት ከረጢቶች ውስጥ ሆነን ከቅዝቃዜው የተነሳ እየተንዘፈዘፍን ደጅ የሚጥለው ኃይለኛ ዝናብ በቆርቆሮው ጣሪያ ላይ ሲወርድ ይሰማናል። የዚህን ደሳሳ ቤት ሁኔታ ስንመለከት ከእኛ በፊት ሰው የነበረበት መሆኑን ተጠራጠርን።

ወደዚህ አካባቢ የመጣነው ለምን ነበር? ኢየሱስ “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ” ምሥራቹን እንድንሰብክ የሰጠንን ትእዛዝ ለመፈጸም ስለፈለግን ነው። (ሥራ 1:8፤ ማቴ. 24:14) ከላይ የተጠቀሰው ሁኔታ ያጋጠመን በቦሊቪያ በሚገኙት የአንዲስ ተራሮች ላይ ባሉት ገለልተኛ አካባቢዎች ለመስበክ ሄደን በነበረበት ጊዜ ነው።

ወደ ተራራው መውጣት

የመጀመሪያው አስቸጋሪ ሁኔታ ወደምንፈልገው ቦታ መድረስ ነበር። ራቅ ብለው ወደሚገኙት ወደነዚህ አካባቢዎች የሚሄደው የሕዝብ መጓጓዣ ቋሚ ፕሮግራም እንደሌለው ተነገረን። የምንሄድበት አውቶቡስ ሲመጣ ደግሞ ከጠበቅነው ያነሰ በመሆኑ አንዳንዶቻችን ቆመን መጓዝ ነበረብን። ያም ሆኖ ግን በመጨረሻ ሁላችንም ወደምንፈልገው ቦታ ደረስን።

የጉዟችን ዓላማ በቦሊቪያ ባሉት የአንዲስ ተራሮች ላይ ወደሚገኙት መንደሮች ሄደን መስበክ ነበር። ስለዚህ ከአውቶቡሱ ከወረድን በኋላ ስንቃችንንና ሌሎች የሚያስፈልጉንን ነገሮች ተሸክመን በአቀበታማው መንገድ ላይ አንድ በአንድ እየሆንን በጥንቃቄ መጓዝ ጀመርን።

 መንደሮቹ ትንንሽ ቢመስሉም ቤቶቹ የተራራቁ ስለሆኑ ወደ እያንዳንዱ መንደር ለመድረስ ረጅም ሰዓት ወሰደብን። የቱንም ያህል ርቀን ብንሄድ ከሩቅ ሌላ ቤት ይታየን ነበር። ብዙውን ጊዜ ደግሞ ማሳውን አቋርጠን ግራ በሚያጋቡት መንገዶች ስንጓዝ እንጠፋ ነበር።

“ለምን ቀደም ብላችሁ አልመጣችሁም?”

አንዲት ሴት ምን ያህል ርቀት በእግራችን እንደተጓዝን ስታውቅ በጣም ስለተገረመች፣ እሷ ባዘጋጀችው የማገዶ እንጨት ተጠቅመን ኩሽናዋ ውስጥ ምሳችንን እንድናበስል ፈቀደችልን። አንድ ሌላ ሰው ደግሞ የሞቱ ሰዎች ስላሉበት ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ሲያውቅ “ለምን ቀደም ብላችሁ አልመጣችሁም?” ብሎ ጠየቀን። ሰውየው የተማረው ነገር ትኩረቱን በጣም ስለሳበው መንደሩን ለቀን ስንሄድ አብሮን እየተጓዘ ተጨማሪ ጥያቄዎችን ይጠይቀን ነበር። ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ምንም ሰምቶ የማያውቅ አንድ ሌላ ሰው ደግሞ ጽሑፎቻችንን በጣም ወዷቸው ነበር። እሱ ያለበት ቦታ ድረስ በመሄዳችን ደጋግሞ ካመሰገነን በኋላ ሌሊቱን አንዲት አነስተኛ ቤት ውስጥ ማደር እንድንችል ቁልፍ ሰጠን።

አንድ ምሽት በጣም ጨልሞ ስለነበር ትላልቅ ጥቁር ጉንዳኖች ባሉበት ቦታ ላይ ሳናውቅ ድንኳናችንን ተከልን። የተቆጡት ጉንዳኖች ወዲያውኑ ይነክሱን ጀመር። እኛ ግን በጣም ደክሞን ስለነበር ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ አልፈለግንም፤ ጥሩነቱ ብዙም ሳይቆይ ጉንዳኖቹ ተዉን።

መሬት ላይ ስለተኛን መጀመሪያ አካባቢ ቢጎረብጠንም ምሽቱ እየገፋ ሲሄድ ግን ለመድነው። ጠዋት ተነስተን ሸለቆዎቹንና በላያቸው በዝግታ የሚጓዘውን ደመና እንዲሁም በበረዶ የተሸፈኑትን የሚያምሩ ተራሮች ስንመለከት ሕመሙን ሁሉ ረሳነው። በአካባቢው  የሚሰማው የወንዝ ድምፅና የአእዋፍ ዝማሬ ብቻ ነው።

በወንዙ ውስጥ ከታጠብን በኋላ በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ተወያየን፤ ከዚያም ቁርሳችንን በልተን ርቀው ወደሚገኙ ሌሎች መንደሮች ለመድረስ አቀበቱን ተያያዝነው። ተራራውን በመውጣታችን ተክሰናል። በአካባቢው ያገኘናቸው አንዲት አረጋዊት፣ ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዳለ ሲያውቁ አለቀሱ። እኚህ ሴት በጣም ተደስተው ነበር፤ ከአሁን በኋላ አምላክን በስሙ እየጠሩ መጸለይ ይችላሉ!

አንድ አረጋዊ ሰው፣ አምላክ እንዳስታወሳቸው ከተናገሩ በኋላ እኛን የላኩን መላእክት እንደሆኑ የሚገልጽ መዝሙር መዘመር ጀመሩ። በጠና በመታመሙ የተነሳ ከቤት መውጣት የማይችል ሌላ ሰው፣ ከመንደሩ ነዋሪዎች መካከል ማንም እንዳልጠየቀው ነገረን። ላ ፓዝ ከተባለችው ከተማ መምጣታችንን ሲያውቅ ተገረመ። አንድ ሌላ ሰው ደግሞ ሌሎች ሃይማኖቶች፣ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመጡ ለመጥራት ደወል ሲደውሉ የይሖዋ ምሥክሮች ግን ወደ ሰዎች ቤት መሄዳቸው በጣም አስገርሞት ነበር። 

በዚያ አካባቢ ያሉ ቤቶች ሁሉ መብራት ስላልነበራቸው ሰዎች የሚተኙት ቀኑ ሲጨልም ሲሆን ጠዋት ጎህ ሲቀድ ይነሳሉ። በመሆኑም ሰዎችን ቤታቸው ለማግኘት ማለዳ አሥራ ሁለት ሰዓት ላይ መስበክ መጀመር ነበረብን። እንዲህ ካላደረግን ግን አብዛኞቹ ሰዎች ወደ እርሻቸው ይሄዳሉ። ረፈድ ሲል ደግሞ በሥራ ላይ ለተሠማሩት ሰዎች የምንሰብክ ሲሆን አንዳንዶቹ ሥራቸውን አቋርጠው ከአምላክ ቃል የምንነግራቸውን መልእክት ለማዳመጥ ፈቃደኞች ነበሩ፤ በዚህ ጊዜ በሬው ማረሻውን ከመጎተት አረፍ ይላል። በቤታቸው ያገኘናቸው አብዛኞቹ ሰዎች አጎዛ አንጥፈው እንድንቀመጥ ከጋበዙን በኋላ መላውን ቤተሰብ ሰብስበው መልእክታችንን ያዳምጡ ነበር። አንዳንድ ገበሬዎች ለሰጠናቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አድናቆታቸውን ለመግለጽ በትልልቅ ከረጢቶች በቆሎ ሰጥተውናል።

“አልረሳችሁኝም”

እርግጥ ነው፣ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀታቸው እያደገ እንዲሄድ አንድ ጊዜ ብቻ መሄዳችን በቂ አይደለም። በርካታ ሰዎች ተመልሰን ተጨማሪ ነገር እንድናስተምራቸው ይለምኑን ነበር። በዚህም ምክንያት ወደዚህ የቦሊቪያ ክፍል በተደጋጋሚ ጊዜያት መጥተናል።

ወደዚህ ቦታ በሌላ ጊዜ በሄድንበት ወቅት፣ አንዲት አረጋዊት ተመልሰን በመሄዳችን ተደስተው “እናንተ ለእኔ እንደ ልጆቼ ናችሁ፤ አልረሳችሁኝም” ብለውናል። አንድ ሰውዬ ለምናከናውነው ሥራ ያመሰገነን ከመሆኑም በላይ በሚቀጥለው ጊዜ ስንመጣ ቤቱ እንድናርፍ ጋበዘን። ላደረግነው ጥረት ካገኘናቸው በረከቶች ሁሉ የላቀው ግን ቀደም ሲል ያነጋገርናት ሴት ወደ ከተማ ተዛውራ በአሁኑ ወቅት ምሥራቹን እንደምትሰብክ መስማታችን ነው።

የመጀመሪያ ጉዟችንን ባጠናቀቅንበት ዕለት ለምድጃችን የምንጠቀምበት ጋዝ ያለቀብን ሲሆን የያዝነውን ምግብም ልንጨርሰው ተቃርበን ነበር። በመሆኑም እንጨት ለቅመን እሳት ካያያዝን በኋላ የቀረንን ምግብ አብስለን ተመገብንና ወደ ቤት ለመመለስ በእግራችን መጓዝ ጀመርን። አውቶቡስ ማግኘት የምንችልበት ከተማ ለመድረስ ብዙ ኪሎ ሜትሮች ይቀሩን ነበር። በመጨረሻም ምሽት ላይ ወደ ከተማው ደረስን።

ወደ ቤት መመለስ

ስንመለስ የተሳፈርንበት አውቶቡስ በመበላሸቱ ጉዞው አስቸጋሪ ነበር። በኋላ ላይ ግን በሰዎች በተጨናነቀ የጭነት መኪና ላይ ተሳፈርን።

ወደ ቤታችን ስንመለስ አብረውን ለሚጓዙ ሰዎች ለመመስከር አጋጣሚ አገኘን፤ እነዚህ ሰዎች ወደዚያ ቦታ ለምን እንደሄድን ለማወቅ ፈልገው ነበር። ሰዎቹ በተፈጥሯቸው ቁጥብ ቢሆኑም አብዛኞቹ ወዳጃዊና ሞቅ ያለ መንፈስ አሳይተውናል።

በጭነት መኪናው ላይ ከኋላ ተሳፍረን ለዘጠኝ ሰዓታት ከተጓዝን በኋላ ልብሳችን በስብሶና በብርድ ተቆራምደን ቤታችን ደረስን። ያም ሆኖ ግን ያደረግነው ጉዞ ከንቱ አልነበረም። በጉዟችን ላይ፣ ከተማ ውስጥ ከምትኖር አንዲት ሴት ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ቀጠሮ መያዝ ችለን ነበር።

በእርግጥም እንደዚህ ባሉ ራቅ ያሉ አካባቢዎች ለሚኖሩ ሰዎች ምሥራቹን መስበክ ታላቅ መብት ነበር። በጉዟችን ወቅት በአራት ትላልቅ መንደሮችና በበርካታ ትናንሽ መንደሮች ውስጥ መስበክ ችለናል። “በተራሮች ላይ የቆሙ፣ የምሥራች ይዘው የሚመጡ እግሮች፣ ሰላምን የሚናገሩ፣ መልካም ዜና የሚያበስሩ፣ ድነትን የሚያውጁ፣ . . . እንዴት ያማሩ ናቸው” የሚለውን ጥቅስ አስታወስን።—ኢሳ. 52:7፤ ሮሜ 10:15

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ምሥራቹን ለመስበክ ተዘጋጅተው እያለ