በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋን ዘወትር በፊትህ አድርግ

ይሖዋን ዘወትር በፊትህ አድርግ

 ይሖዋን ዘወትር በፊትህ አድርግ

“እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] ሁልጊዜ በፊቴ አድርጌአለሁ።” —መዝ. 16:8

1. የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን ማንበባችን ምን በጎ ተጽዕኖ ያሳድርብናል?

በጽሑፍ የሰፈረው የይሖዋ ቃል አምላክ ከሰው ልጆች ጋር ስለነበረው ግንኙነት የሚገልጹ አስደናቂ ዘገባዎችን ይዟል። በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ውስጥ ሚና ስለተጫወቱ በርካታ ሰዎች ያወሳል። እርግጥ ነው፣ እነዚህ ሰዎች የተናገሯቸው ቃላትም ሆኑ ያከናወኗቸው ድርጊቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩት እንዲያው በታሪክነት እንድናውቃቸው ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ዘገባዎቹ ወደ አምላክ ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዱናል።—ያዕ. 4:8

2, 3. በመዝሙር 16:8 ላይ ያሉት ቃላት ምን ትርጉም አላቸው?

2 ሁላችንም እንደ አብርሃም፣ ሣራ፣ ሙሴ፣ ሩት፣ ዳዊት፣ አስቴርና ሐዋርያው ጳውሎስ ያሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ታዋቂ ሰዎች ካሳለፉት የሕይወት ተሞክሮ ብዙ ትምህርት እናገኛለን። እምብዛም ታዋቂ ያልነበሩ ግለሰቦችን ታሪክ ማንበባችንም ቢሆን ጥቅም ያስገኝልናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ላይ ማሰላሰላችን መዝሙራዊው “እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] ሁልጊዜ በፊቴ አድርጌአለሁ፤ እርሱ በቀኜ ስላለ አልናወጥም” ሲል ከገለጸው ሐሳብ ጋር ተስማምተን እንድንኖር ይረዳናል። (መዝ. 16:8) እነዚህ ቃላት ምን ትርጉም አላቸው?

3 በውጊያ ላይ ያለ አንድ ወታደር በአብዛኛው ሰይፍ የሚይዘው በቀኝ እጁ ስለሆነ፣ በግራ እጁ የሚይዘው ጋሻ በቀኝ በኩል ያለውን የሰውነቱን ክፍል አይሸፍንለትም። ሆኖም ከእሱ በስተቀኝ ሆኖ የሚዋጋ ጓደኛ ካለው ከለላ ይሆነዋል። ይሖዋን ሁልጊዜ የምናስብና ፈቃዱን የምናደርግ ከሆነ ከጥቃት ይጠብቀናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን መመርመራችን እምነታችንን የሚያጠናክርልን እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። እንዲህ ማድረጋችን ‘ይሖዋን ሁልጊዜ በፊታችን እንድናደርግ’ ይረዳናል።

ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ ይሰጣል

4. አምላክ ለጸሎቶቻችን መልስ እንደሚሰጥ የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ያሳያል?

4 ይሖዋን ሁልጊዜ በፊታችን የምናደርግ ከሆነ ለጸሎታችን መልስ ይሰጠናል። (መዝ. 65:2፤ 66:19) በዕድሜ አንጋፋ የነበረው የአብርሃም አገልጋይ (ኤሊዔዘር ሳይሆን አይቀርም) የገጠመው ሁኔታ ይህ እውነት መሆኑን ያረጋግጣል። አብርሃም፣ ኤሊዔዘርን ለልጁ ለይስሐቅ ፈሪሃ አምላክ ያላት ሚስት እንዲያመጣለት ወደ መስጴጦምያ ላከው። ኤሊዔዘር የአምላክን መመሪያ ለማግኘት የጸለየ ሲሆን ርብቃ ግመሎቹን ውኃ ስታጠጣ ሲመለከት በጉዳዩ ላይ የይሖዋ እጅ እንዳለበት ተገነዘበ። ኤሊዔዘር ከልብ የመነጨ ጸሎት በማቅረቡ ለይስሐቅ ጥሩ ሚስት ማግኘት ችሎ ነበር። (ዘፍ. 24:12-14, 67) እርግጥ ነው፣ የአብርሃም አገልጋይ የተሰጠው ተልእኮ ለየት ያለ ነበር። ይሁን እንጂ እኛስ ይሖዋ ጸሎታችንን በእርግጥ እንደሚሰማን ልንተማመን አይገባንም?

5. በልብ የቀረበ አጭር ጸሎት እንኳ ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል የምንለው ለምንድን ነው?

5 አንዳንድ ጊዜ የአምላክን እርዳታ ለማግኘት ወዲያውኑ መጸለይ ይኖርብን ይሆናል። በአንድ ወቅት፣ የፋርሱ ንጉሥ አርጤክስስ ነህምያ የተባለ የወይን ጠጅ አሳላፊው በሐዘን ፊቱ ጠቁሮ ተመለከተ። በመሆኑም ንጉሡ ነህምያን “ምን ትፈልጋለህ?” ሲል ጠየቀው። ነህምያም ወዲያውኑ ‘ወደ ሰማይ አምላክ ጸለየ።’ ነህምያ በልቡ ያቀረበው ጸሎት አጭር እንደነበር መገመት እንችላለን። ይሁንና አምላክ ለጸሎቱ መልስ ሰጥቶታል። የኢየሩሳሌምን ቅጥር ዳግም ለመገንባት የሚያስችል ድጋፍ ከንጉሡ አግኝቷል። (ነህምያ 2:1-8ን አንብብ።) አዎን፣ በልብ የቀረበ አጭር ጸሎት እንኳ ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል።

6, 7. (ሀ) ኤጳፍራ በጸሎት ረገድ ምን ምሳሌ ትቶልናል? (ለ) ስለ ሌሎች መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?

6 ጸሎታችን መልስ እንዳገኘ የሚያሳይ ማስረጃ ወዲያውኑ የማንመለከትባቸው ጊዜያት ሊኖሩ ቢችሉም ‘አንዳችን ለሌላው እንድንጸልይ’ ተመክረናል። (ያዕ. 5:16) “የክርስቶስ ታማኝ አገልጋይ የሆነው” ኤጳፍራ ለእምነት አጋሮቹ አጥብቆ ይጸልይ ነበር። ጳውሎስ ሮም ሆኖ በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሏል:- “ከእናንተ [ከቈላስይስ] ወገን የሆነው የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ ኤጳፍራ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ እርሱም ፍጹም ጠንክራችሁና  ሙሉ በሙሉ ተረጋግታችሁ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉ ጸንታችሁ እንድትቆሙ ዘወትር ስለ እናንተ በጸሎት እየተጋደለ ነው። ደግሞም ስለ እናንተ እንዲሁም በሎዶቅያና በኢያራ ከተሞች ስላሉት ተግቶ እንደሚሠራ እኔ እመሰክርለታለሁ።”—ቈላ. 1:7፤ 4:12, 13

7 ቈላስይስ፣ ሎዶቅያና ኢያራ በትንሿ እስያ በአንድ አካባቢ የሚገኙ ከተሞች ነበሩ። በኢያራ የነበሩት ክርስቲያኖች ሲብል የተባለችውን ጣዖት በሚያመልኩ ሰዎች መካከል ይኖሩ የነበረ ሲሆን በሎዶቅያ ያሉት ደግሞ ፍቅረ ንዋይ በተጠናወታቸው ሰዎች የተከበቡ ነበሩ። ከዚህም በተጨማሪ በቈላስይስ ተስፋፍቶ የሚታየው ሰብዓዊ ፍልስፍና በዚያ ለሚኖሩት የአምላክ አገልጋዮች ተፈታታኝ ሁኔታ ፈጥሮባቸዋል። (ቈላ. 2:8) በመሆኑም ከቈላስይስ ወገን የሆነው ኤጳፍራ በከተማዋ ለሚኖሩት የእምነት ባልደረቦቹ ‘አዘውትሮ ይጸልይ’ የነበረ መሆኑ ምንም አያስገርምም። መጽሐፍ ቅዱስ የኤጳፍራ ጸሎት ምላሽ ያገኘው እንዴት እንደነበር የሚገልጸው ነገር የለም። ይሁንና ኤጳፍራ ስለ እምነት አጋሮቹ መጸለዩን አላቆመም። እኛም ብንሆን ስለ ወንድሞቻችን መጸለያችንን ማቆም የለብንም። ‘በሰው ነገር ጣልቃ የምንገባ’ ባንሆንም፣ አንድ የቤተሰባችን አባል ወይም ወዳጃችን የእምነት ፈተና እየደረሰበት እንዳለ እናውቅ ይሆናል። (1 ጴጥ. 4:15) በመሆኑም ስለ እሱ መጸለያችን ምንኛ የተገባ ነው! ጳውሎስ ሌሎች ስለ እሱ ባቀረቡት ጸሎት ተጠቅሟል። በተመሳሳይም፣ እኛም የምናቀርበው ጸሎት ብዙ ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል።—2 ቆሮ. 1:10, 11

8. (ሀ) በኤፌሶን ይኖሩ የነበሩት ሽማግሌዎች የጸሎትን ጥቅም ከፍ አድርገው ይመለከቱ እንደነበር እንዴት ማወቅ እንችላለን? (ለ) ወደ አምላክ የመጸለይ መብታችንን እንዴት ልንመለከተው ይገባል?

8 ሌሎች የጸሎት ሰው እንደሆንን አድርገው ይመለከቱናል? ጳውሎስ በኤፌሶን ይኖሩ ከነበሩት ሽማግሌዎች ጋር ከተገናኘ በኋላ “ተንበርክኮ ከሁሉም ጋር ጸለየ።” ከዚያም “ሁሉም እጅግ አለቀሱ፤ ጳውሎስንም አንገቱን ዐቅፈው ሳሙት፤ ከሁሉም በላይ ልባቸውን የነካው፣ ከእንግዲህ ወዲህ ፊቱን እንደማያዩ የተናገራቸው ቃል ነበር።” (ሥራ 20:36-38) በወቅቱ የነበሩትን የሁሉንም ሽማግሌዎች ስም ባናውቅም የጸሎትን ጥቅም ከፍ አድርገው ይመለከቱ እንደነበር ከሁኔታቸው በግልጽ መረዳት ይቻላል። ወደ አምላክ የመጸለይ መብታችንን ከፍ አድርገን ልንመለከተው የሚገባን ሲሆን በሰማይ የሚኖረው አባታችን መልስ እንደሚሰጠን በማመን ‘የተቀደሱ እጆቻችንን ወደ ላይ አንስተን መጸለይ’ ይኖርብናል።—1 ጢሞ. 2:8

አምላክን በፍጹም ልብ ታዘዝ

9, 10 (ሀ) የሰለጰዓድ ሴት ልጆች ምን ምሳሌ ትተዋል? (ለ) የሰለጰዓድ ሴት ልጆች ያሳዩት ታዛዥነት፣ ያላገቡ ክርስቲያኖች ስለ ጋብቻ ያላቸውን አመለካከት የሚነካው እንዴት ነው?

9 ይሖዋን ዘወትር ማሰባችን እሱን እንድንታዘዘው የሚረዳን ሲሆን ይህም በረከት ያስገኝልናል። (ዘዳ. 28:13፤ 1 ሳሙ. 15:22) ይህ የታዛዥነት መንፈስ ማሳየትን ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል፣ በሙሴ ዘመን ይኖሩ የነበሩት የሰለጰዓድ አምስት ሴት ልጆች የነበራቸውን ዝንባሌ ተመልከት። በእስራኤላውያን ልማድ መሠረት ርስት የመውረስ መብት ያላቸው ወንዶች ልጆች ብቻ ነበሩ። ይሁንና ሰለጰዓድ ወንድ ልጅ ሳይወልድ በመሞቱ ይሖዋ ሴቶች ልጆቹ የአባታቸውን ርስት በሙሉ እንዲወርሱ ትእዛዝ ሰጠ። ይሁን እንጂ ውርሱን ለማግኘት አንድ ነገር ማሟላት ይጠበቅባቸው ነበር። ይኸውም ርስቱ በአባታቸው ነገድ ይዞታ ሥር እንዲቆይ ከምናሴ ነገድ ብቻ ማግባት ነበረባቸው።—ዘኍ. 27:1-8፤ 36:6-8

10 የሰለጰዓድ ሴት ልጆች አምላክን እስከታዘዙ ድረስ አስደሳች ውጤት እንደሚያገኙ እምነት ነበራቸው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “የሰለጰዓድ ሴት ልጆች እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ። የሰለጰዓድ ሴት ልጆች፤ ማህለህ፣ ቲርጻ፣ ዔግላ፣ ሚልካ፣ ኑዓ ከአባታቸው ወንድሞች ልጆች ጋር ተጋቡ።  ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ዝርያ ጐሣዎች ጋር በመጋባታቸው፣ ርስታቸው በዚያው በአባታቸው ጐሣና ነገድ እጅ እንዳለ ቀረ።” (ዘኍ. 36:10-12) እነዚህ ታዛዥ ሴቶች ይሖዋ ያዘዘውን ፈጽመዋል። (ኢያሱ 17:3, 4) በዛሬው ጊዜ የሚገኙ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ያላገቡ ክርስቲያኖችም እንዲሁ ዓይነት እምነት ስላላቸው “በጌታ” ብቻ በማግባት አምላክን እንደሚታዘዙ ያሳያሉ።—1 ቆሮ. 7:39

11, 12. ካሌብ በአምላክ ላይ እምነት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?

11 ካሌብ የተባለው እስራኤላዊ እንዳደረገው ሁሉ ይሖዋን በፍጹም ልብ መታዘዝ ይኖርብናል። (ዘዳ. 1:36) በ16ኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ነፃ ከወጡ በኋላ ሙሴ የከነዓንን ምድር እንዲሰልሉ 12 ሰዎችን ልኮ ነበር። ይሁንና ከእነዚህ ሰላዮች መካከል፣ ሕዝቡ በአምላክ ላይ ሙሉ በሙሉ በመታመን ወደ ምድሪቱ እንዲገባ ሐሳብ ያቀረቡት ካሌብና ኢያሱ ብቻ ነበሩ። (ዘኍ. 14:6-9) ይህ ከሆነ ከአርባ ዓመት በኋላም ቢሆን ኢያሱና ካሌብ በሕይወት የነበሩ ሲሆን ይሖዋን በፍጹም ልብ ተከትለዋል። እንዲሁም አምላክ እስራኤላውያንን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለማስገባት በኢያሱ ተጠቅሟል። ይሁን እንጂ አሥሩ እምነት የለሽ ሰላዮች እስራኤላውያን በምድረ በዳ በተንከራተቱባቸው 40 ዓመታት ሞተዋል።—ዘኍ. 14:31-34

12 በምድረ በዳ ከመሞት የተረፈው በዕድሜ የገፋው ካሌብ ወደ ኢያሱ ቀርቦ ‘አምላኬን ይሖዋን በፍጹም ልቤ ተከተልሁት’ ለማለት ችሏል። (ኢያሱ 14:6-9ን አንብብ።) የሰማንያ አምስት ዓመቱ ካሌብ፣ አምላክ እንደሚሰጠው ቃል በገባለት ኮረብታማ አገር ውስጥ የሚኖሩት ጠላቶቻቸው ጠንካራ የተመሸጉ ከተሞች ያሏቸው ቢሆኑም እንኳ ይህ ስፍራ ርስት ተደርጎ እንዲሰጠው ከመጠየቅ ወደኋላ አላለም።—ኢያሱ 14:10-15

13. ማንኛውም ዓይነት ፈተና ይድረስብን፣ የአምላክን በረከት ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

13 እኛም፣ ታማኝና ታዛዥ እንደነበረው እንደ ካሌብ ይሖዋን ‘በፍጹም ልብ የምንከተል’ ከሆነ አምላክ ይባርከናል። ይሖዋን ‘በፍጹም ልብ ከተከተልነው’ ከባድ ችግሮች ሲያጋጥሙን እርዳታ እናገኛለን። ይሁንና ካሌብ እንዳደረገው ሕይወታችንን በሙሉ ይሖዋን መከተል ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል። ንጉሥ ሰሎሞን ሥልጣን በያዘበት ወቅት ይሖዋን በፍጹም ልቡ የታዘዘ ቢሆንም እንኳ በሸመገለ ጊዜ ሚስቶቹ ወደ ሐሰት አማልክት እንዲያዘነብል አድርገውታል። በመሆኑም ልክ ‘እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ይሖዋን እስከ መጨረሻው አልተከተለም።’ (1 ነገ. 11:4-6) ማንኛውም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን ምንጊዜም አምላክን በፍጹም ልብ እንታዘዝ፤ እንዲሁም ይሖዋን ዘወትር በፊታችን እናድርግ።

ምንጊዜም በይሖዋ ታመን

14, 15. በአምላክ የመታመንን አስፈላጊነት በተመለከተ ከኑኃሚን ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

14 በተለይ የወደፊቱ ጊዜ የጨለመብን ሲመስለንና በጭንቀት ስንዋጥ በይሖዋ መታመን ያስፈልገናል። የትዳር ጓደኛዋንና ሁለት ወንዶች ልጆቿን፣ የሰው ልጆች ጠላት በሆነው በሞት የተነጠቀችው አረጋዊቷ ኑኃሚን የነበረችበትን ሁኔታ ተመልከት። ኑኃሚን ከሞአብ ወደ ይሁዳ በተመለሰችበት ወቅት እንዲህ ስትል በምሬት ተናግራለች:- “ሁሉን የሚችል አምላክ ሕይወቴን እጅግ መራራ አድርጎታልና ማራ [“መራራ፣” የግርጌ ማስታወሻ] በሉኝ እንጂ፣ ኑኃሚን [“ደስተኛ፣” የግርጌ ማስታወሻ] ብላችሁ አትጥሩኝ። በሙላት ወጣሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ባዶዬን መለሰኝ፤ እግዚአብሔር አስጨንቆኝ፣ ሁሉን  የሚችል አምላክ መከራ አምጥቶብኝ ሳለ እንዴት ኑኃሚን ብላችሁ ትጠሩኛላችሁ?”—ሩት 1:20, 21

15 ኑኃሚን ተጨንቃ የነበረ ቢሆንም የሩት መጽሐፍን በጥንቃቄ ካነበብነው በይሖዋ ትታመን እንደነበር ለማስተዋል እንችላለን። ኑኃሚን የነበረችበት ሁኔታ በድንገት ተለወጠ! የልጇ ሚስት የሆነችው መበለቷ ሩት ቦዔዝን አግብታ ወንድ ልጅ ወለደች። ኑኃሚንም የልጁ ሞግዚት ሆነች። መጽሐፍ ቅዱስ ሁኔታውን ሲገልጽ “ጎረቤቶቿ የሆኑ ሴቶችም፣ ‘ለኑኃሚን ወንድ ልጅ ተወለደላት’ አሉ። ስሙንም ኢዮቤድ ብለው ጠሩት፤ እርሱም የዳዊት አባት የሆነው የእሴይ አባት ነበር” ይላል። (ሩት 4:14-17) ኑኃሚንና ሩት ወደፊት ትንሣኤ በሚያገኙበት ወቅት ኑኃሚን፣ ሩት የመሲሑ ቅድመ አያት መሆኗን ማወቋ አይቀርም። (ማቴ. 1:5, 6, 16) ልክ እንደ ኑኃሚን እኛም ያጋጠመን ችግር በምን መንገድ መፍትሔ እንደሚያገኝ አናውቅም። በመሆኑም፣ በምሳሌ 3:5, 6 ላይ እንደተመከርነው ምንጊዜም በአምላክ እንታመን። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” NW] ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።”

በመንፈስ ቅዱስ ታመን

16. የአምላክ መንፈስ በጥንቷ እስራኤል ይኖሩ የነበሩትን አንዳንድ ሽማግሌዎች የረዳቸው እንዴት ነበር?

16 ምንጊዜም ይሖዋን በፊታችን የምናደርግ ከሆነ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ይመራናል። (ገላ. 5:16-18) የእስራኤልን ‘ሕዝብ ሸክም በመሸከም’ ሙሴን እንዲያግዙ የተመረጡት 70 ሰዎች የአምላክ መንፈስ ተሰጥቷቸው ነበር። ከእነዚህ መካከል በስም የተጠቀሱት ኤልዳድና ሞዳድ ቢሆኑም መንፈስ ቅዱስ ሁሉንም ሽማግሌዎች የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አስችሏቸዋል። (ዘኍ. 11:13-29) እነዚህ ሽማግሌዎች ከዚህ በፊት እንደተመረጡት ሰዎች ብቃት ያላቸው፣ አምላክን የሚፈሩ፣ እምነት የሚጣልባቸውና ሐቀኞች እንደሆኑ ጥርጥር የለውም። (ዘፀ. 18:21) በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎችም እነዚህ ባሕርያት አሏቸው።

17. የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ የመገናኛው ድንኳን በተሠራበት ወቅት ምን ሚና ተጫውቷል?

17 የመገናኛው ድንኳን በምድረ በዳ በተሠራበት ወቅት የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ይሖዋ፣ ባስልኤል ‘በሁሉም ዐይነት የእጅ ጥበብ ሥራ፣ ብልሃት፣ ችሎታና ዕውቀት እንዲኖረው መንፈሱን እንደሚሞላበት’ በመግለጽ በመገናኛው ድንኳን ሥራ ዋና የእጅ ባለሙያ አድርጎ ሾሞት ነበር። (ዘፀ. 31:3-5) ባስልኤል የተጣለበትን አስደሳች ኃላፊነት እንዲወጣ “በልባቸው ጥበበኞች” የሆኑ ሌሎች ሰዎችና ረዳቱ ኤልያብ እገዛ አድርገውለታል። ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ መንፈስ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን በለጋስነት እንዲሰጡ አነሳስቷቸዋል። (ዘፀ. 31:6 የ1954 ትርጉም፤ 35:5, 30-34) በዛሬው ጊዜም ይኸው መንፈስ የአምላክ አገልጋዮች በሕይወታቸው ውስጥ መንግሥቱን እንዲያስቀድሙ ይገፋፋቸዋል። (ማቴ. 6:33) አንድ ዓይነት ችሎታ ሊኖረን ቢችልም፣ ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ለሚኖሩት ሕዝቦቹ የሰጣቸውን ሥራ መፈጸም እንድንችል መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት መጸለይና መንፈሱ እንዲመራን መፍቀድ ይኖርብናል።—ሉቃስ 11:13

የሠራዊት ጌታ ለሆነው ለይሖዋ ምንጊዜም አክብሮታዊ ፍርሃት ይኑርህ

18, 19. (ሀ) የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ምን ዓይነት ዝንባሌ እንዲኖረን ይረዳናል? (ለ) ስምዖንና ሐና ከተዉት ምሳሌ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

18 መንፈስ ቅዱስ፣ ይሖዋን ምንጊዜም ከፊታችን ለማድረግ የሚያስችለንን አክብሮታዊ ፍርሃት እንድናዳብር ይረዳናል። ጥንት የነበሩት የአምላክ ሕዝቦች ‘የሠራዊት ጌታ ይሖዋ አክብሮታዊ ፍርሃት የሚገባው ቅዱስ’ አምላክ እንደሆነ ተነግሯቸው ነበር። (ኢሳ. 8:13ባይንግተን) በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ ስምዖንና ሐና የተባሉ አረጋውያን ለአምላክ አክብሮታዊ ፍርሃት ነበራቸው። (ሉቃስ 2:25-38ን አንብብ።) ስምዖን ስለ መሲሑ በተነገሩት ትንቢቶች ላይ እምነት የነበረው ከመሆኑም ባሻገር “የእስራኤልን መጽናናት” ይጠባበቅ ነበር። አምላክ መንፈሱን በስምዖን ላይ በማውረድ መሲሑን  ሳያይ እንደማይሞት ቃል ገብቶለት ነበር። ይህም ፍጻሜውን አግኝቷል። በ2 ከክርስቶስ ልደት በፊት በዋለ አንድ ቀን እናቱ ማርያምና አሳዳጊ አባቱ ዮሴፍ ሕፃኑን ኢየሱስን ይዘው ወደ ቤተ መቅደስ መጡ። በዚህ ወቅት ስምዖን በመንፈስ ቅዱስ ተነሳስቶ ስለ መሲሑና ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ሲሰቀል ማርያም ስለሚሰማት ሐዘን ትንቢት ተናገረ። ይሁንና፣ ስምዖን “የጌታን መሲሕ” ባቀፈው ጊዜ ምን ያህል እንደተደሰተ ገምት! ስምዖን አክብሮታዊ ፍርሃትን በማሳየት ረገድ በዛሬው ጊዜ ለሚኖሩ የአምላክ አገልጋዮች ግሩም ምሳሌ ትቷል!

19 ለአምላክ አክብሮታዊ ፍርሃት የነበራት የ84 ዓመቷ መበለት ሐና ‘ከቤተ መቅደስ ተለይታ’ አታውቅም። ሐና “በጾምና በጸሎት” ሌት ተቀን ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት ታቀርብ ነበር። ሕፃኑን ኢየሱስን ወላጆቹ ወደ ቤተ መቅደስ ይዘውት በመጡበት ወቅት እሷም እዚያው ነበረች። ሐና የወደፊቱን መሲሕ የማየት አጋጣሚ በማግኘቷ ምንኛ አመስጋኝ ትሆን! በእርግጥም ሐና ‘አምላክን ያመሰገነች’ ሲሆን “የኢየሩሳሌምንም መቤዠት ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ ሕፃኑ ተናገረች።” ሐና ይህንን የምሥራች ለሌሎች መናገር እንዳለባት ተሰምቷታል! ልክ እንደ ስምዖንና እንደ ሐና በዛሬው ጊዜ የሚገኙ አረጋውያን ክርስቲያኖችም ዕድሜያቸው የቱንም ያህል ቢገፋ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው የማገልገል መብት ስላላቸው እጅግ ደስተኞች ናቸው።

20. በየትኛውም የዕድሜ ክልል ላይ እንገኝ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ለምንስ?

20 በየትኛውም የዕድሜ ክልል ላይ እንገኝ ይሖዋን ዘወትር በፊታችን ማድረግ ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን፣ ስለ መንግሥቱና ስለ ድንቅ ሥራዎቹ ለሌሎች ለመናገር የምናደርገውን ጥረት ይባርክልናል። (መዝ. 71:17, 18፤ 145:10-13) ይሁንና ይሖዋን ለማክበር ከፈለግን እሱን የሚያስደስቱትን ባሕርያት ማንጸባረቅ ይኖርብናል። ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን በመመርመር ስለ እነዚህ ባሕርያት መማር የምንችለው ነገር ይኖር ይሆን?

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ይሖዋ ጸሎትን እንደሚሰማ እንዴት እናውቃለን?

• አምላክን በፍጹም ልብ መታዘዝ ያለብን ለምንድን ነው?

• የሚያስጨንቅ ሁኔታ ቢገጥመንም እንኳ ምንጊዜም በይሖዋ መታመን ያለብን ለምንድን ነው?

• የአምላክ ቅዱስ መንፈስ የይሖዋ ሕዝቦችን የሚረዳቸው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ነህምያ ለይሖዋ ያቀረበው ጸሎት ጥሩ ውጤት አስገኝቷል

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኑኃሚን የነበረችበት ሁኔታ መለወጡን ማስታወሳችን በይሖዋ እንድንታመን ይረዳናል