በርካታ ቋንቋዎችን የያዘው የኮምፕሉቴንስ መጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ የትርጉም መሣሪያ
በርካታ ቋንቋዎችን የያዘው የኮምፕሉቴንስ መጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ የትርጉም መሣሪያ
በ1455 ገደማ በመጽሐፍ ቅዱስ ሕትመት ረገድ አንድ ታላቅ ለውጥ ተካሂዶ ነበር። ዮሐንስ ጉተንበርግ በተንቀሳቃሽ የማተሚያ መሣሪያ ለመታተም የመጀመሪያ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ አዘጋጅቶ አወጣ። መጽሐፍ ቅዱስ በእጅ እየተገለበጠ በአነስተኛ ቅጂዎች የሚሰራጭበት ዘመን አብቅቶ በአንጻራዊ ሁኔታ አነስተኛ በሆነ ወጪ በብዛት እየታተመ መሠራጨት ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስ በዓለማችን ላይ በስፋት ከተሠራጩት መጻሕፍት መካከል የአንደኛነቱን ቦታ ለመያዝ በቃ።
የጉተንበርግ መጽሐፍ ቅዱስ የታተመው በላቲንኛ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን የአውሮፓ ምሑራን ቅዱሳን ጽሑፎች በመጀመሪያ በተጻፉባቸው የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቋንቋዎች የተዘጋጀ አስተማማኝ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስፈልጋቸው ተገነዘቡ። በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ተቀባይነት የነበረው ብቸኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የላቲኑ ቩልጌት ቢሆንም ሁለት መሠረታዊ ችግሮች ነበሩት። በ16ኛው ክፍለ ዘመን የላቲን ቋንቋን መረዳት የሚችሉት ሰዎች ጥቂት የነበሩ ከመሆኑም በላይ ከአንድ ሺህ በሚበልጡ ዓመታት ውስጥ በላቲኑ ቩልጌት ላይ ገልባጮች በርካታ ስህተቶች ሠርተው ነበር።
ተርጓሚዎችም ሆኑ ምሑራን በጊዜው ከነበረው የተሻለ የላቲንኛ ትርጉምና ቅዱሳን ጽሑፎች መጀመሪያ በተጻፉባቸው ቋንቋዎች የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ ይፈልጉ ነበር። በ1502 የስፔይኗ ንግሥት ቀዳማዊ ኢዛቤላ የፖለቲካና የመንፈሳዊ ጉዳዮች አማካሪ የነበረው ካርዲናል ሂሜኔዝ ዜ ዚስኒሮስ በአንድ መጽሐፍ አማካኝነት ይህንን ፍላጎታቸውን ለማሟላት ወሰነ። ይህ ታሪካዊ የትርጉም መሣሪያ የኮምፕሉቴንስ ፖሊግሎት (በርካታ ቋንቋዎችን አጣምሮ የያዘ መጽሐፍ ቅዱስ) የሚል ስያሜ ተሰጠው። ዚስኒሮስ በበርካታ ቋንቋዎች ማለትም በአረማይክ የተዘጋጁ የተወሰኑ ክፍሎችን ጨምሮ በዕብራይስጥ፣ በግሪክና በላቲን የተተረጎሙ ቅዱሳን ጽሑፎችን አጣምሮ የያዘ የተሻለ መጽሐፍ ቅዱስ (polyglot) ለማዘጋጀት አስቦ ነበር። የሕትመት ሥራ ገና ስላላደገ የዚህ መጽሐፍ ቅዱስ መታተም በሕትመቱ ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ ከፋች እንደሚሆን ግልጽ ነበር።
ዚስኒሮስ ይህን ከባድ ሥራ ለማከናወን በስፔይን እንደልብ ይገኙ የነበሩትን ጥንታዊ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች መግዛት ጀመረ። በተጨማሪም ለማዘጋጀት ላሰበው መጽሐፍ ቅዱስ መሠረት እንዲሆኑ የተለያዩ የግሪክና የላቲን ጥንታዊ ጽሑፎችን አሰባሰበ። ዚስኒሮስ መጽሐፍ ቅዱሱን የማቀናበሩን ሥራ በስፔይን አዲስ በተቋቋመው አልካላ ዜ ኤናሬስ የተባለ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ላደራጀው አንድ የምሑራን ቡድን ሰጠ። የቡድኑ አባል እንዲሆኑ ከተጋበዙት ምሑራን መካከል የሮተርዳሙ ኢራስመስ ይገኝበት ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ታዋቂ የቋንቋ ሊቅ ግብዣውን አልተቀበለም።
ምሑራኑ ይህን ትልቅ ሥራ ለማቀናበር አሥር ዓመታት የፈጀባቸው ሲሆን የማተሙ ሂደት ደግሞ ተጨማሪ አራት ዓመታት ወስዷል። በስፔይን የነበሩት የማተሚያ መሣሪያዎች የዕብራይስጥ፣ የግሪክና የአረማይክ ፊደላት ስላልነበሯቸው በርካታ ቴክኒካዊ ችግሮች አጋጥመው ነበር። በመሆኑም ዚስኒሮስ፣ አርናልዶ ጊዬርሞ ብሮካር የተባለ በሙያው የተካነ አታሚ ለእነዚህ ቋንቋዎች የሚሆኑ የማተሚያ ፊደላት እንዲቀርጽለት አደረገ። ከዚያም ማተሚያዎቹ በ1514 ሥራ ጀመሩና ስድስቱም ጥራዞች ካርዲናሉ ከመሞቱ ከአራት ወራት በፊት በሐምሌ 10, 1517 ታትመው ተጠናቀቁ። ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ 600 ገደማ በሚሆኑ ቅጂዎች የታተመ ሲሆን ይህ የሆነው የስፓኒሽ ኢንኩዊዝሽን ከፍተኛው ደረጃ ላይ a
ደርሶ በነበረበት ጊዜ መሆኑ በእርግጥም የሚያስገርም ነው።የመጽሐፉ ቅንብር
በርካታ ቋንቋዎችን አጣምሮ የያዘው ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በእያንዳንዱ ገጽ ላይ ብዙ መረጃዎች ይዟል። የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን በያዙት አራት ጥራዞች ላይ በገጹ መሃል ለመሃል የሰፈረው የላቲኑ ቩልጌት ነው። በውጪኛው ዓምድ ላይ የዕብራይስጡ ጽሑፍ የሚገኝ ሲሆን የግሪኩ ጽሑፍ ደግሞ ከላቲንኛው የቃል በቃል (interlinear) ትርጉም ጋር በውስጠኛው አምድ ላይ ሰፍሯል። በሕዳጎቹ ላይ ለበርካታ የዕብራይስጥ ቃላት መነሻ ሆነው ያገለገሉ ቃላት ይገኛሉ። እንዲሁም አዘጋጆቹ በኦሪት መጽሐፎች ግርጌ ላይ ታርገም ኦቭ አንከላስ የተባለውን ጽሑፍ (የመጀመሪያዎቹን አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ሐሳብ ጨመቅ በማድረግ የተዘጋጀ የአረማይክ ትርጉም) ከላቲንኛ ትርጉሙ ጋር አስቀምጠውታል።
አምስተኛው የመጽሐፉ ጥራዝ የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን በሁለት አምድ ይዟል። በአንደኛው አምድ ላይ የግሪክኛው ጽሑፍ የሰፈረ ሲሆን በሌላኛው አምድ ላይ ደግሞ ከቩልጌት የተወሰደው ተጓዳኝ የላቲን ጽሑፍ ይገኛል። በሁለቱ ቋንቋዎች የቀረበውን ጽሑፍ ተመሳሳይነት ለመጠቆም ትናንሽ የላቲን ፊደላትን በመጠቀም የትኛው የግሪክኛ ቃል ከየትኛው የላቲን ቃል ጋር እንደሚዛመድ ለማሳየት ተሞክሯል። የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን ማለትም “የአዲስ ኪዳን” መጻሕፍትን በአንድ ላይ አጠቃልሎ ለመያዝ ይህ የመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በኢራስመስ የተዘጋጀው የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ታትሟል።
ምሑራኑ በአምስተኛው ጥራዝ የእርምት ንባብ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረጋቸው የተገኙበት ስህተቶች ከሃምሳ አይበልጡም ነበር። በዚህም የተነሳ የዘመናችን የመጽሐፍ ቅዱስ ሃያሲያን ይህ ጥራዝ በኢራስመስ ከተዘጋጀው የግሪክኛ ትርጉም የላቀ መሆኑን መስክረዋል። ዓይን የሚስቡት የግሪክኛ ሆሄያት የጥንቶቹ የብራና ጽሑፎች ከተጻፉበት የእጅ አጣጣል ጋር የሚወዳደር ውበት አላቸው። ሮበርት ፕራክተር ዘ ፕሪንቲንግ ኦቭ ግሪክ ኢን ዘ ፊፍቲንዝ ሴንቸሪ (የግሪክኛ ሕትመት በአሥራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “እስከ ዛሬ ከተዘጋጁት የግሪክኛ የፊደል አጣጣሎች ሁሉ በጣም ውብ የሆነውን የፊደል አጣጣል በመቅረጿ መመስገን የሚገባት ስፔይን ናት።”
ስድስተኛው ጥራዝ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚረዱ በርካታ መሣሪያዎችን የያዘ ሲሆን እነዚህም የዕብራይስጥና የአረማይክ መዝገበ ቃላት፣ የግሪክና የዕብራይስጥ እንዲሁም የአረማይክ ስሞች ፍቺ፣ የዕብራይስጥ ሰዋስውና ለመዝገበ ቃላቱ የሚሆን የላቲንኛ ማውጫ ናቸው። በእርግጥም ይህ መጽሐፍ ቅዱስ “ለሕትመት ጥበብና ለቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት የቆመ ሐውልት” መባሉ የሚያስገርም አይደለም።
ዚስኒሮስ ይህን መጽሐፍ ቅዱስ ለማዘጋጀት የተነሳው “ለዘመናት ተዳፍኖ በቆየው የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት ላይ ዳግመኛ ሕይወት ለመዝራት” ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ለሰፊው ሕዝብ በገፍ እንዲዳረስ የማድረግ ፍላጎት ግን አልነበረውም። “የአምላክ ቃል ተራው ሕዝብ ሊረዳው በማይችለው ሁኔታ ምስጢራዊ ሆኖ መቀመጥ ይኖርበታል” የሚል አስተሳሰብ ነበረው። እንዲሁም “ቅዱሳን ጽሑፎች አምላክ ልጁ በተሰቀለ ጊዜ ከበላዩ የነበረው ጽሑፍ እንዲጻፍ በፈቀደባቸው ሦስት ጥንታዊ ቋንቋዎች ተወስነው መቆየት አለባቸው” ብሎ ያምን ነበር። b በዚህም የተነሳ በኮምፕሉቴንስ ፖሊግሎት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የስፓንኛ ትርጉም አልተካተተም።
ቩልጌት መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ ከተጻፈባቸው ቋንቋዎች ጋር ሲወዳደር
የመጽሐፍ ቅዱሱ ይዘት በራሱ በሥራው በተካፈሉት ምሑራን መካከል አንዳንድ አለመግባባቶችን አስነስቶ c በርካታ ቋንቋዎችን አጣምሮ በያዘው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚካተተውን የላቲኑን ቩልጌት የማሻሻል ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር። ምንም እንኳን በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ሕጋዊ እውቅና የነበረው በጄሮም የተዘጋጀው የቩልጌት ትርጉም ብቻ ቢሆንም ኔብሪሃ ይህን ትርጉም ከዕብራይስጥ፣ ከአረማይክና ከግሪክ ቅጂዎች ጋር ማመሳከር አስፈላጊ መሆኑን ተገንዘቦ ነበር። በጊዜው በነበሩት የቩልጌት ቅጂዎች ውስጥ የነበሩትን ግልጽ ስህተቶች ለማረም ፈልጎ ነበር።
ነበር። ስመ ገናናው ስፔይናዊ ምሑር አንቶኒዮ ዴ ኔብሪሃኔብሪሃ በቩልጌትና ቅዱሳን ጽሑፎች በተጻፉባቸው የመጀመሪያ ቋንቋዎች መካከል ያለውን ልዩነት ለማስተካከል ለዚስኒሮስ እንዲህ በማለት ጽፎለት ነበር:- “ጠፍተው የነበሩትን የሃይማኖታችንን ፋናዎች ማለትም የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቋንቋዎች ዳግመኛ አብራቸው። ራሳቸውን ለዚህ ሥራ ያቀረቡትን ሰዎች ካሳቸው።” የሚከተለውን ሐሳብም አቅርቦ ነበር:- “በላቲንኛ በተጻፉ የአዲስ ኪዳን ቅጂዎች መካከል ልዩነት በተገኘ ቁጥር ከጥንታዊ የግሪክኛ ቅጂዎች ጋር ማመሳከር ይኖርብናል። በተለያዩ የላቲንኛ ቅጂዎች ወይም በላቲንና በግሪክኛ በተዘጋጁ የብሉይ ኪዳን ቅጂዎች መካከል የሚጋጭ ሐሳብ ሲገኝ ትክክለኛውን ለማግኘት አስተማማኝ የሆነውን የዕብራይስጥ ጽሑፍ መመርመር ይኖርብናል።”
የዚስኒሮስ ምላሽ ምን ነበር? በመጽሐፍ ቅዱሱ መቅድም ላይ ያሰፈረው ሐሳብ አመለካከቱን በግልጽ ያሳያል። “የሮማ ወይም የላቲን ቤተ ክርስቲያንን በሚወክለው በኢየሱስ ግራና ቀኝ ሌቦች ተሰቅለው እንደነበረ ሁሉ የተባረከውን የጄሮምን የላቲን ትርጉም በምኩራብና [በዕብራይስጡ ጽሑፍ] በምሥራቃዊ ቤተ ክርስቲያን [በግሪክኛው ጽሑፍ] መካከል አስቀምጠነዋል።” በመሆኑም ኔብሪሃ የላቲኑን ቩልጌት ቅዱሳን ጽሑፎች መጀመሪያ ከተጻፉባቸው ቋንቋዎች ጋር እያመሳከረ እንዲያርም አልፈቀደለትም። ኔብሪሃ እንከን ባለበት ትርጉም ውስጥ ስሙ እንዲጠቀስ ስላልፈለገ ሥራውን ለመተው ወሰነ።
ከጊዜ በኋላ የተጨመረ ሐሳብ
በአልካላ ዜ ኤናሬስ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀው ይህ በርካታ ቋንቋዎችን አጣምሮ የያዘ መጽሐፍ ቅዱስ ቅዱሳን ጽሑፎች በመጀመሪያ በተጻፉባቸው ቋንቋዎች ከበፊቱ የተሻለ ትርጉም በማዘጋጀት ረገድ ትልቅ እመርታ የታየበት ነበር። ቢሆንም በሥራው ላይ አልፎ አልፎ ከትክክለኛው እውቀት ይልቅ ሲወርድ ሲዋረድ ለመጣው ሃይማኖታዊ አመለካከት ቅድሚያ ይሰጥ ነበር። ለቩልጌት ትልቅ ቦታ ይሰጠው ስለነበር አዘጋጆቹ የላቲኑን ጽሑፍ ከግሪኩ ጋር እንዲስማማ አድርጎ ከማስተካከል ይልቅ በግሪክኛው “አዲስ ኪዳን” ላይ ማስተካከያ ማድረግ እንዳለባቸው ተሰምቷቸው ነበር። ለዚህ በምሳሌነት ከሚጠቀሱት ጥቅሶች መካከል ኮማ ዮሃኒየም ተብሎ የሚጠራው ከጊዜ በኋላ የተጨመረ ጥቅስ ይገኝበታል። d ዮሐንስ ደብዳቤውን ከጻፈ ከበርካታ ዘመናት በኋላ የተጨመረው ይህ ሐሳብ በየትኛውም የጥንት የግሪክኛ ቅጂም ሆነ ጥንታዊ በሆኑ የላቲን ቩልጌት ቅጂዎች ላይ አይገኝም። በመሆኑም ኢራስመስ እርሱ ባዘጋጀው የግሪክኛ “አዲስ ኪዳን” ትርጉም ውስጥ አልጨመረውም።
የመጽሐፍ ቅዱሱ አዘጋጆች ለዘመናት የላቲኑ ቩልጌት ክፍል ሆኖ የቆየውን ይህን ሐሳብ ማውጣት በጣም ከብዷቸው ነበር። በመሆኑም በላቲኑ ጽሑፍ ውስጥ ጥቅሱን እንዳለ የተውት ሲሆን ከግሪክኛው ጽሑፍ ጋር ለማስማማት ሲሉ ተርጉመው በግሪክኛው ውስጥ ጨምረውታል።
ለአዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መሠረት ሆኖ አገልግሏል
የኮምፕሉቴንስ ፖሊግሎት መጽሐፍ ቅዱስን ጠቃሚ ያደረገው የመጀመሪያውን የተሟላ የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ስብስብ እና የሰብዓ ሊቃናትን (ሴፕቱጀንት) ትርጉም አጣምሮ መያዙ ብቻ አይደለም። በኢራስመስ የተዘጋጀው የግሪክኛ “አዲስ ኪዳን” ትርጉም የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን ወደ ሌሎች ቋንቋዎች ለመተርጎም መሠረት ሆኖ እንዳገለገለ ሁሉ በኮምፕሉቴንስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የዕብራይስጥ ጽሑፍም የዕብራይስጥና የአረማይክ ቅዱሳን ጽሑፎችን ወደ ሌሎች ቋንቋዎች ለመተርጎም እንደ መሠረት ሆኖ አገልግሏል። e ዊልያም ቲንደል መጽሐፍ ቅዱስን ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ የተረጎመው በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው የዕብራይስጥ ጽሑፍ ነው።
ስለሆነም የኮምፕሉቴንስ ፖሊግሎት መጽሐፍ ቅዱስን ያዘጋጀው ቡድን ያከናወነው ታላቅ ሥራ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ በሚደረገው ጥናት ረገድ ለታየው እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የታተመው በመላው አውሮፓ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው ፍላጎት እያደገ በመምጣቱ በተራው ሕዝብ ቋንቋ ተተርጉሞ እንዲቀርብ ከፍተኛ ግፊት ይደረግ በነበረበት ወቅት ነበር። የግሪክና የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ከስህተት ጠርተውና ይዞታቸው ተጠብቆ እንዲቆዩ አስተዋጽኦ ካበረከቱት በርካታ ሥራዎች መካከል አንዱ የኮምፕሉቴንስ ፖሊግሎት መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ይህ ሁሉ ይሖዋ ‘የነጠረው ቃሉ’ ‘ለዘላለም ጸንቶ እንዲኖር’ ለማድረግ ካለው ዓላማ ጋር ይስማማል።—መዝሙር 18:30፤ ኢሳይያስ 40:8፤ 1 ጴጥሮስ 1:25
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ስድስት መቶዎቹ ቅጂዎች የታተሙት በወረቀት ሲሆን 6 ቅጂዎች ደግሞ በብራና ተዘጋጅተው ነበር። በ1984 የመጀመሪያውን ቅጂ በማስመሰል የተወሰኑ መጽሐፍ ቅዱሶች ታትመው ነበር።
b ዕብራይስጥ፣ ግሪክና ላቲን።—ዮሐንስ 19:20
c ኔብሪሃ ለስፔይን ለዘብተኛ ምሑራን መንገድ ጠራጊ ተደርጎ ይታያል። በ1492 የመጀመሪያውን ግራማቲካ ካስቲልያና (የካስቲል ቋንቋ የሰዋስው መጽሐፍ) ያሳተመው ኔብሪሃ ከሦስት ዓመታት በኋላ ቀሪ ሕይወቱን ቅዱሳን ጽሑፎችን በማጥናት ለማሳለፍ ወስኗል።
d በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ በአንደኛ ዮሐንስ 5:7 ላይ የተጨመረው ሐሳብ እንዲህ ይላል:- “በሰማይ የሚመሰክሩ ሶስት ናቸውና እርሳቸውም አብ ቃልም መንፈስ ቅዱስም። እሌህ ሶስትም አንድም ናቸው።” (የ1879 ትርጉም)
e የኢራስመስን ሥራ በሚመለከት ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት የመስከረም 15, 1982 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 8-11 ተመልከት።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ካርዲናል ሂሜኔዝ ዜ ዚስኒሮስ
[ምንጭ]
Biblioteca Histórica. Universidad Complutense de Madrid
[ምንጭ]
Biblioteca Histórica. Universidad Complutense de Madrid
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንቶኒዮ ዴ ኔብሪሃ
[ምንጭ]
Biblioteca Histórica. Universidad Complutense de Madrid
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Biblioteca Histórica. Universidad Complutense de Madrid