በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

‘በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ’

‘በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ’

‘በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ።’ (ማቴዎስ 10:8 አ.መ.ት) ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ይህን ትእዛዝ የሰጠው ምሥራቹን እንዲሰብኩ በላካቸው ጊዜ ነበር። ሐዋርያቱ ይህን ትእዛዝ ተከትለው ይሆን? አዎን፣ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላም እንኳን ትእዛዙን ጠብቀዋል።

ለምሳሌ ያህል አስማተኛ የነበረው ሲሞን ሐዋርያው ጴጥሮስና ሐዋርያው ዮሐንስ ተአምር የመፈጸም ችሎታ እንዳላቸው ሲመለከት ገንዘብ አመጣላቸውና ለእርሱም ይህን ችሎታ እንዲሰጡት ጠየቃቸው። ጴጥሮስ ግን “የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ” በማለት ገሠጸው።—ሥራ 8:18-20

ሐዋርያው ጳውሎስም የጴጥሮስ ዓይነት አመለካከት ነበረው። በቆሮንቶስ የሚኖሩት ክርስቲያን ወንድሞቹ በገንዘብ እንዲረዱት መጠየቅ ይችል ነበር። ይሁን እንጂ ራሱን ለመደገፍ በገዛ እጁ ይሠራ ነበር። (ሥራ 18:1-3) ስለሆነም ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ወንጌልን “ያለ ዋጋ” እንደሰበከላቸው አፉን ሞልቶ መናገር ችሏል።—1 ቆሮንቶስ 4:12፤ 9:18

የሚያሳዝነው ግን የክርስቶስ ተከታዮች እንደሆኑ የሚናገሩ ብዙ ሰዎች ‘በነጻ ለመስጠት’ ፈቃደኞች አይደሉም። እንደ እውነቱ ከሆነ አብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ መሪዎች ‘የሚያስተምሩት በዋጋ’ ነው። (ሚክያስ 3:11) እንዲያውም አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ከመንጎቻቸው በሚሰበስቡት ገንዘብ የናጠጡ ሃብታሞች ሆነዋል። በ1989 ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አንድ ወንጌላዊ የ45 ዓመት እስራት ተፈርዶበት ወኅኒ ወርዷል። ምክንያቱ ምን ነበር? “ሃይማኖቱን በገንዘብ ከሚደግፉ ሰዎች በሚልዮን የሚቆጠር ዶላር በማጭበርበር የተወሰነውን ገንዘብ ለሽርሽር መሄጃ እንዲሁም ቤቶች፣ መኪናዎችና ሌላው ቀርቶ የአየር ማቀዝቀዣ ያለው የውሻ ቤት ለመግዣ በማዋሉ ነው።”—ፒፕልስ ዴይሊ ግራፊክ፣ ጥቅምት 7, 1989

ጋናያን ታይምስ የተባለው ጋዜጣ በመጋቢት 31, 1990 እትሙ እንደዘገበው በጋና አንድ የሮማ ካቶሊክ ቄስ በአንድ የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ የተሰበሰበውን ገንዘብ መልሶ በምዕመናኑ ላይ በተነው። ጋዜጣው እንዳለው “ቄሱ ይህን ያደረገው ምእመናኑ ትልልቅ የገንዘብ ኖቶችን እንዴት አያዋጡም ብሎ ነበር።” እንዲያውም በርካታ ቤተ ክርስቲያኖች ቁማርን ጨምሮ ሌሎች የገቢ ማሰባሰቢያ ዘዴዎችን እየፈጠሩ አባላቶቻቸው የስግብግብነት ዝንባሌ እንዲያሳዩ ማድረጋቸው የተለመደ እየሆነ መጥቷል።

ከዚህ በተቃራኒ የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስና የመጀመሪያው መቶ ዘመን ደቀመዛሙርት የተዉትን ምሳሌ ለመከተል ይጥራሉ። ደመወዝ የሚከፈላቸው ቀሳውስት የሏቸውም። እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ የመስበክ ኃላፊነት ተጥሎበታል። (ማቴዎስ 24:14) በመሆኑም ከስድስት ሚልዮን የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች “የሕይወትን ውኃ” በነጻ ለሰዎች በማዳረሱ ሥራ ይካፈላሉ። (ራእይ 22:17) ይህም ‘ገንዘብ የሌላቸውም’ ሳይቀሩ ከመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ጥቅም እንዲያገኙ ያስችላል። (ኢሳይያስ 55:1) ዓለም አቀፋዊው ሥራቸው የሚደገፈው በፈቃደኝነት በሚደረግ መዋጮ ቢሆንም የገንዘብ እርዳታ አይለምኑም። እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናቸው መጠን ‘የአምላክን ቃል አይሸቃቅጡም፤’ ከዚህ ይልቅ ‘በቅንነት ከእግዚአብሔር  እንደተላኩ ሆነው’ ይናገራሉ።—2 ቆሮንቶስ 2:17

የይሖዋ ምሥክሮች በራሳቸው ወጪ ሌሎችን ለመርዳት ፈቃደኞች የሆኑት ለምን ይሆን? እንዲህ እንዲያደርጉ የሚገፋፋቸው ምንድን ነው? በነጻ ይሰጣሉ ሲባል ለጥረታቸው ምንም ወሮታ አይከፈላቸውም ማለት ነው?

ሰይጣን ላነሳው ጥያቄ መልስ መስጠት

አምላክ ቤዛውን ለሰው ልጆች በነጻ መስጠቱ ክርስቲያኖችም ወንጌልን በነጻ እንዲሰብኩ ይገፋፋቸዋል

በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች ዋነኛው ዓላማቸው ይሖዋን ማስደሰት እንጂ ራሳቸውን ማበልጸግ አይደለም። እንዲህ በማድረጋቸውም ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ሰይጣን ዲያብሎስ ላነሳው አንድ ጥያቄ መልስ መስጠት ችለዋል። ሰይጣን ጻድቅ ሰው የነበረውን ኢዮብን በተመለከተ “በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራ በከንቱ ነውን?” በማለት ለይሖዋ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ኢዮብ አምላክን የሚያገለግለው ጥበቃ ስለሚደረግለት ነው የሚል ምክንያት አቀረበ። ንብረቱን ቢያጣ አምላክን ይሰድበዋል በማለት ተከራከረ።—ኢዮብ 1:7-11

አምላክ ለዚህ ክስ መልስ ለማስገኘት “ለእርሱ ያለው ሁሉ በእጅህ ነው” በማለት ኢዮብን እንዲፈትነው ፈቀደለት። (ኢዮብ 1:12) ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ኢዮብ የሰይጣንን ውሸታምነት አረጋገጠ። ኢዮብ ምንም ዓይነት መከራ ቢፈራረቅበትም ታማኝነቱን ጠብቋል። “እስክሞት ድረስ ፍጹምነቴን [“ታማኝነቴን፣” NW] ከእኔ አላርቅም” በማለት ተናግሯል።—ኢዮብ 27:5, 6

በዛሬው ጊዜ የሚገኙ እውነተኛ አምላኪዎችም የኢዮብን ዓይነት ዝንባሌ ያሳያሉ። አምላክን የሚያገለግሉት ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ብለው አይደለም።

የአምላክ የጸጋ ስጦታ

እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘በነጻ የሚሰጡበት’ ሌላው ምክንያት እነርሱም ከአምላክ ‘በነጻ ስለተቀበሉ’ ነው። የሰው ልጆች ከመጀመሪያው አባታቸው ከአዳም በወረሱት ኃጢአት ምክንያት የኃጢአትና የሞት ባሪያ ሆነዋል። (ሮሜ 5:12) ይሖዋ በፍቅሩ ተነሳስቶ ልጁ ቤዛዊ መሥዋዕት ሆኖ እንዲሞት ያደረገ ሲሆን ይህም ትልቅ ዋጋ ጠይቆበታል። ይህ ዝግጅት የሰው ልጆች ይገባናል ብለው የሚጠይቁት አልነበረም። ከአምላክ ያገኙት ስጦታ ነው።—ሮሜ 4:4፤ 5:8፤ 6:23

በሮሜ 3:23, 24 ላይ ጳውሎስ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን እንዲህ ብሏቸው ነበር:- “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ።” ይህን የጸጋ ስጦታ ከሚቀበሉት መካከል በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸውም ይገኙበታል። ይህ ስጦታ እንደ ጻድቅ ተቆጥሮ የይሖዋ ወዳጅ መባልንም ይጨምራል።—ያዕቆብ 2:23፤ ራእይ 7:14

በተጨማሪም የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ለሁሉም ክርስቲያኖች የአምላክ አገልጋዮች የመሆን አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ “በእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ የዚህ ወንጌል አገልጋይ ሆኛለሁ” በማለት ጽፏል። (ኤፌሶን 3:4-7 አ.መ.ት) እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች ይህን የአገልግሎት መብት ያገኙት ይገባናል በማይሉት የጸጋ ስጦታ ስለሆነ ስለ ቤዛው ዝግጅት ለሌሎች በሚሰብኩበት ጊዜ ደመወዝ እንዲከፈላቸው መጠበቅ አይችሉም።

ለዘላለም ለመኖር መፈለግ ራስ ወዳድነት ነውን?

ታዲያ እንዲህ ሲባል አምላክ ክርስቲያኖች ምንም ወሮታ ሳይጠብቁ እንዲያገለግሉት ይፈልጋል ማለት ነውን?  በፍጹም። ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን አምላክ “ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና” ብሏቸዋል። (ዕብራውያን 6:10) ይሖዋ ፍትሐዊ አምላክ ነው። (ዘዳግም 32:4) ‘ለሚፈልጉት ዋጋ ይሰጣል።’ (ዕብራውያን 11:6) ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች በገነት ውስጥ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ ማድረጋቸው ራስ ወዳድነት ነውን?—ሉቃስ 23:43

በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች ዋነኛው ዓላማቸው ይሖዋን ማስደሰት እንጂ ራሳቸውን ማበልጸግ አይደለም

በፍጹም አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም የመኖርን ሐሳብ ያመነጨው አምላክ ራሱ ነው። ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ይህንን ተስፋ የሰጠው እርሱ ነበር። (ዘፍጥረት 1:28፤ 2:15-17) አዳምና ሔዋን በሠሩት ኃጢአት ምክንያት ይህንን መብት ስናጣም የዘላለም ሕይወት የምናገኝበትን ሌላ ዝግጅት አድርጎልናል። አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው” በማለት ቃል ገብቷል። (ሮሜ 8:21) በመሆኑም በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች እንደ ጥንቱ ሙሴ ‘ብድራታቸውን ትኩር ብለው’ መመልከታቸው የተገባ ነው። (ዕብራውያን 11:25, 26) አምላክ ይህን ሽልማት ያዘጋጀው ለአገልጋዮቹ ባለው እውነተኛ ፍቅር ተነሳስቶ እንጂ ለመደለያ ብሎ አይደለም። (2 ተሰሎንቄ 2:16, 17) “እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን።”—1 ዮሐንስ 4:19

አምላክን የምናገለግልበት ትክክለኛው ምክንያት

የሆነ ሆኖ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖች አምላክን ለማገልገል የተነሳሱበት ምክንያት ምን እንደሆነ ራሳቸውን መጠየቅ ይኖርባቸዋል። ዮሐንስ 6:10-13 ኢየሱስ ከአምስት ሺህ የሚበልጡ ሰዎችን በተአምር እንደመገበ ይናገራል። በዚህም ምክንያት አንዳንዶች ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ኢየሱስን መከተል ጀመሩ። ኢየሱስ “የምትፈልጉኝ እንጀራን ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው” አላቸው። (ዮሐንስ 6:26) ከተወሰኑ አሥርተ ዓመታት በኋላ አንዳንድ ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖችም አምላክን የሚያገለግሉት ‘የራሳቸውን ጥቅም ፈልገው እንጂ በቅን አሳብ’ አልነበረም። (ፊልጵስዩስ 1:17) እንዲያውም “ከኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ጤናማ ቃል” የማይገዙ አንዳንዶች ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ያላቸውን ትውውቅ ለግል ጥቅም ማግኛ ይጠቀሙበት ነበር።—1 ጢሞቴዎስ 6:3-5

ዛሬም ቢሆን በገነት ውስጥ ለዘላለም ለመኖር ሲል ብቻ አምላክን የሚያገለግል አንድ ክርስቲያን የግል ጥቅም ለማግኘት ብለው ከሚያገለግሉት ተለይቶ አይታይም። ይዋል ይደር እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ዝንባሌ ለመንፈሳዊ ውድቀት ሊዳርገው ይችላል። ምክንያቱም የሰይጣን ሥርዓት የሚጠፋበት ጊዜ ከጠበቀው በላይ የዘገየ ከመሰለው ‘ሊዝል’ ይችላል። (ገላትያ 6:9) እንዲያውም መሥዋዕት ያደረጋቸውን ቁሳዊ ጥቅሞች እያሰበ ይቆጭ ይሆናል። ኢየሱስ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ” በማለት አሳስቦናል። (ማቴዎስ 22:37) አዎን፣ በፍቅር ተነሳስቶ አምላክን የሚያገለግል ክርስቲያን ለአገልግሎቱ የጊዜ ገደብ አያበጅም። ይሖዋን ለማገልገል የሚፈልገው ለዘላለም ነው። (ሚክያስ 4:5) አምላክን ከማገልገል ጋር በተያያዘ ስለከፈላቸው ቁሳዊ መሥዋዕቶች አይቆጭም። (ዕብራውያን 13:15, 16) ለአምላክ ያለው ፍቅር በሕይወቱ ውስጥ የእርሱን ፍላጎት እንዲያስቀድም ይገፋፋዋል።—ማቴዎስ 6:33

በዛሬው ጊዜ ከስድስት ሚልዮን የሚበልጡ እውነተኛ አምላኪዎች ይሖዋን ለማገልገል ራሳቸውን ‘በገዛ ፈቃዳቸው’ ያቀርባሉ። (መዝሙር 110:3 አ.መ.ት) አንተስ ከእነዚህ አንዱ ነህ? ካልሆንህ አምላክ ንጹሑን የእውነት እውቀት እንድትቀስም፣ ከሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ነጻ እንድትወጣና የዘላለም ሕይወት እንድታገኝ ስላደረገልህ ዝግጅት አሰላስል። (ዮሐንስ 17:3፤ 8:32፤ ራእይ 21:3, 4) የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን በረከቶች እንዴት ማግኘት እንደምትችል በነጻ ያስተምሩሃል።