በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጅ አባቱን የረዳበት መንገድ

ልጅ አባቱን የረዳበት መንገድ

ልጅ አባቱን የረዳበት መንገድ

በእንግሊዝ አገር የሚኖረውና በሠላሳዎቹ የእድሜ ክልል መግቢያ ላይ የሚገኘው ጄምስ ከባድ የአእምሮ እክልና መጠነኛ የመናገር ችግር ነበረበት። ያም ሆኖ ከእናቱና ከእህቱ ጋር በመሆን ለብዙ ዓመታት በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎች ላይ ተገኝቷል። ሆኖም አባቱ ለእምነታቸው ምንም ፍላጎት አልነበረውም። አንድ ምሽት ላይ የሚያውቁትን ሰው በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ እንዲገኝ መጋበዝ የሚቻልበትን መንገድ የሚያሳይ ሠርቶ ማሳያ በስብሰባው ላይ ተመልክተው እቤት እንደተመለሱ ጄምስ እየተጣደፈ ወደ ክፍሉ ሄደ። እናቱ ምን ሊያደርግ እንደሆነ ለማወቅ በመጓጓት ተከትላው ስትሄድ የቆዩ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት እትሞችን በጥድፊያ ስሜት ሲያገላብጥ አገኘችው። ከዚያም በጀርባው ላይ የመታሰቢያው በዓል መጋበዣ ወረቀት ያለበትን መጽሔት መረጠና በፍጥነት ወደ አባቱ ሄደ። አንድ ጊዜ ሥዕሉን አንዴ ደግሞ አባቱን እያመለከተ “አንተ!” በማለት ተናገረ። ጄምስ አባቱን በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኝ እየጋበዘ እንደሆነ ሲረዱ እናቱና አባቱ በመገረም እርስ በርስ ተያዩ። አባቱ ምናልባት በስብሰባው ላይ ሊገኝ እንደሚችል ነገረው።

በመታሰቢያው በዓል ምሽት ጄምስ ወደ አባቱ ቁም ሣጥን ሄዶ አንድ ሱሪ ከመረጠ በኋላ ልብሱን ይዞ ወደ አባቱ አመራ። ከዚያም አባቱ ሱሪውን እንዲለብስ በምልክት ነገረው። ይሁን እንጂ አባቱ ወደ ስብሰባው እንደማይሄድ ነገረው። ስለዚህ ጄምስና እናቱ ብቻቸውን ወደ መንግሥት አዳራሽ ሄዱ።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን ጄምስ እናቱ አዘገጃጅታ ወደ ስብሰባ ይዛው ልትሄድ ስትል ከአባቱ ጋር ቤት ለመሆን በመምረጥ እምቢ ይላት ጀመር። ከዚያም አንድ እሁድ ጠዋት እናቱ አዘጋጅታው ወደ ስብሰባ ይዛው ልትሄድ ስትል እንደገና እምቢ አላት። የሚያስገርመው አባቱ ወደ እርሱ ዞር አለና “ጄምስ፣ እኔ ወደ ስብሰባ ብሄድ አንተም ትሄዳለህ?” ሲል ጠየቀው። የጄምስ ፊት በደስታ ፈካ። አባቱን እቅፍ አድርጎ “አዎን!” ሲል መለሰ። ከዚያም ሦስቱም አንድ ላይ ወደ መንግሥት አዳራሽ ሄዱ።

ከዚያን ጊዜ ወዲህ የጄምስ አባት እሁድ እሁድ በሚደረጉት በሁሉም ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ እድገት ለማድረግ በሌሎቹም ስብሰባዎች ላይ መገኘት እንደሚኖርበት ገለጸ። (ዕብራውያን 10:​24, 25) ከዚያም በሁሉም ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረና ከሁለት ወራት በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት ማጥናት ጀመረ። በሕይወቱ ውስጥ አስፈላጊዎቹን ማስተካከያዎች በማድረግ ፈጣን እድገት ካሳየ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በመንግሥቱ ስብከት ሥራ መካፈል ጀመረ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላ ራሱን ለይሖዋ ወሰነና ተጠመቀ። በአሁኑ ጊዜ የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ ያገለግላል። አሁን ሁሉም የቤተሰቡ አባላት በአንድነት ይሖዋን በማገልገል ላይ ናቸው።