በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | በቤት ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ

ቤተሰብ እንዲጋጭ የሚያደርገው ነገር

ቤተሰብ እንዲጋጭ የሚያደርገው ነገር

ከያዕቆብ * ጋር ለ17 ዓመታት በትዳር ያሳለፈችውና በጋና የምትኖረው ሣራ “ብዙ ጊዜ የሚያጋጨን የገንዘብ ጉዳይ ነው” በማለት ተናግራለች። አክላም “እኔ ቤተሰቡን ለመንከባከብ ብደክምም እሱ ግን ስለ በጀታችን አናግሮኝ አያውቅም። ለሳምንታት የምንኮራረፍበት ጊዜ አለ” ብላለች።

ባለቤቷ ያዕቆብ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ልክ ነው፤ ኃይለ ቃል የምንነጋገርባቸው ጊዜያት አሉ። ብዙውን ጊዜ ለዚህ ምክንያቱ ተነጋግሮ አለመግባባትና ትርጉም ያለው ውይይት አለማድረግ ነው። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የምንጋጨው ቶሎ ቱግ ስለምንል ነው።”

በቅርቡ ትዳር የመሠረተውና በሕንድ የሚኖረው ናታን አንድ ቀን የሚስቱ አባት በሚስቱ እናት ላይ ሲጮኽባት የተፈጠረውን ነገር ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በጣም ስለተበሳጨች ቤቱን ጥላ ወጣች። ለምን እንደዛ እንደጮኸባት ስጠይቀው እንደናቅኩት ተሰማው። ከዚያም ሁላችንም ላይ መጮኽ ጀመረ።”

እናንተም ብትሆኑ በአጉል ሰዓት የተነገሩ ወይም ያልታሰበባቸው ቃላት በቤታችሁ ውስጥ ምን ያህል ግጭት እንደሚፈጥሩ ሳታስተውሉ አትቀሩም። ረጋ ባለ መንፈስ የተጀመረ ውይይት በድንገት ወደ ቃላት ጦርነት ሊቀየር ይችላል። ማናችንም ብንሆን ሁልጊዜ ትክክል የሆነ ነገር ልንናገር አንችልም፤ ስለዚህ ሌሎች የተናገሩትን ነገር ወይም አንድን ነገር ያደረጉበትን ምክንያት በተሳሳተ መንገድ ልንተረጉመው እንችላለን። ያም ቢሆን በቤተሰብ ውስጥ ሰላም ማግኘትና ተስማምቶ መኖር ይቻላል።

የጦፈ ጭቅጭቅ በሚነሳበት ጊዜ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? በቤታችሁ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት መልሶ እንዲሰፍን ለማድረግ ምን እርምጃዎች ልትወስዱ ትችላላችሁ? ቤተሰቦች፣ በቤት ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው? መልሱ በቀጣዮቹ ርዕሶች ላይ ይገኛል።

^ አን.3 በእነዚህ ርዕሶች ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።