መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
የዓለም መጨረሻ
አንደኛ ዮሐንስ 2:17 “ዓለምም ሆነ ምኞቱ ያልፋሉ” ይላል። እዚህ ላይ የተጠቀሰው “ዓለም” ምን ያመለክታል? የሚያልፈውስ እንዴትና መቼ ነው?
የዓለም መጨረሻ ሲባል የትኛው “ዓለም” ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ይህ ዓለም አምላክን የማያስደስት ‘ምኞት’ እንዳለው ስለተጠቀሰ ግዑዟን ምድር እንደማያመለክት ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ ለአምላክ ጀርባቸውን በመስጠት የእሱ ጠላት የሆኑ ሰዎችን ያመለክታል። (ያዕቆብ 4:4) “እነዚህ ሰዎች ዘላለማዊ ጥፋት ተፈርዶባቸው . . . ይወገዳሉ።” (2 ተሰሎንቄ 1:7-9) በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚታዘዙና የዚህ ዓለም ክፍል ከመሆን የሚርቁ ሰዎች ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው።—ዮሐንስ 15:19
አንደኛ ዮሐንስ 2:17 “የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ . . . ለዘላለም ይኖራል” ይላል። አዎ፣ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ሰው በመዝሙር 37:29 ላይ በተገለጸው መሠረት እዚችው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አለው። ጥቅሱ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት ይገልጻል።
“ዓለምንም ሆነ በዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች አትውደዱ። ማንም ዓለምን የሚወድ ከሆነ የአብ ፍቅር በውስጡ የለም።”—1 ዮሐንስ 2:15
ዓለም የሚጠፋው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
የዓለም መጨረሻ ሁለት ምዕራፎች ይኖሩታል። በመጀመሪያ አምላክ “ታላቂቱ ባቢሎን” በተባለች አመንዝራ የተመሰሉትን የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች ያጠፋል። (ራእይ 17:1-5፤ 18:8) “ታላቂቱ ባቢሎን” ለአምላክ ታማኝ እንደሆነች ብትናገርም ከዓለም የፖለቲካ መሪዎች ጋር ሽርክና በመፍጠር ምንዝር ፈጽማለች። ይሁንና እነዚህ መሪዎች ራሳቸው ጥቃት ይሰነዝሩባታል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አመንዝራዋን ይጠሏታል፤ ከዚያም ይበዘብዟታል፤ ራቁቷንም ያስቀሯታል፤ እንዲሁም ሥጋዋን [ወይም ሀብቷን] ይበላሉ፤ ሙሉ በሙሉም በእሳት ያቃጥሏታል።”—ራእይ 17:16
ቀጥሎ ደግሞ አምላክ ትኩረቱን ወደ ፖለቲካ መሪዎች ይኸውም “ወደ ዓለም ነገሥታት ሁሉ” ያዞራል። እነሱም ሆኑ ሌሎች ክፉ ሰዎች ‘ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ ይኸውም ‘በአርማጌዶን’ ይጠፋሉ።—ራእይ 16:14, 16
“በምድር ላይ የምትኖሩ የዋሆች ሁሉ ይሖዋን ፈልጉ። ጽድቅን ፈልጉ፤ የዋህነትን ፈልጉ። ምናልባት በይሖዋ የቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።”—ሶፎንያስ 2:3
የዓለም መጨረሻ መቼ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
የዓለም መጨረሻ የሚመጣው ሰብዓዊ መንግሥታት መላውን ዓለም በሚቆጣጠረው የአምላክ መንግሥት እንደሚተኩ የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ ለመላው የሰው ዘር ከታወጀ በኋላ ነው። (ዳንኤል 7:13, 14) ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴዎስ 24:14) የአምላክን ፍትሕና ምሕረት የሚያንጸባርቀው ይህ የስብከት ሥራ የዓለም መጨረሻ መቅረቡን የሚያሳየው “ምልክት” ካሉት ገጽታዎች አንዱ ነው። በዓለም ዙሪያ ያሉ ጦርነቶች፣ የምድር ነውጦች፣ የምግብ እጥረትና በሽታዎችም የምልክቱ ገጽታዎች ናቸው።—ማቴዎስ 24:3፤ ሉቃስ 21:10, 11
መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ላይ ስለሚታዩት ትላልቅ ክስተቶች ከመተንበዩም በተጨማሪ “በመጨረሻዎቹ ቀናት” የሚኖሩ ሰዎች የሚያሳዩአቸውን ባሕሪያትም ይገልጻል። እንዲህ ይላል፦ “በመጨረሻዎቹ ቀናት ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ ይህን እወቅ። ምክንያቱም ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ . . . ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ . . . ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ . . . ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ።” *—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
አሁን ያለው ክፉ ዓለም በቅርቡ ‘ያልፋል።’—1 ዮሐንስ 2:17
እነዚህ ሁሉ ነገሮች በ1914 አንደኛው የዓለም ጦርነት ከፈነዳበት ጊዜ ገደማ ወዲህ ያለውን ዘመን ለይተው የሚያሳውቁ ናቸው። በተጨማሪም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የአምላክ መንግሥት በሁሉም የዓለም ክፍል እየታወጀ ነው፤ የይሖዋ ምሥክሮችም በዚህ ሥራ መታወቃቸውን እንደ ክብር ይቆጥሩታል። እንዲያውም ዋነኛው መጽሔታቸው የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ የሚል ርዕስ አለው።
“ቀኑንም ሆነ ሰዓቱን ስለማታውቁ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።”—ማቴዎስ 25:13
^ አን.14 ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ተመልከት። መጽሐፉ www.jw.org/am ላይም ይገኛል።