በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንድፍ አውጪ አለው?

የዕፀዋት የሒሳብ ችሎታ

የዕፀዋት የሒሳብ ችሎታ

ዕፀዋት ከፀሐይ ብርሃን የሚያገኙትን ኃይል ተጠቅመው ፎቶሲንተሲስ በሚባል ውስብስብ ሂደት አማካኝነት ምግብ ያዘጋጃሉ። በአንዳንድ ዝርያዎች ላይ የተደረጉ ጥናቶች፣ ዕፀዋት ሌላም አስደናቂ ነገር እንደሚያከናውኑ ይኸውም ያዘጋጁትን ምግብ በአንድ ምሽት በተሻለ ፍጥነት ጥቅም ላይ የሚያውሉበትን መንገድ እንደሚያሰሉ አረጋግጠዋል።

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ዕፀዋት ቀን ላይ በከባቢ አየር ውስጥ የሚገኘውን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደ ስታርችና ወደ ስኳር ይለውጣሉ። አብዛኞቹ ተክሎች ሌሊት የሚጠቀሙት፣ ቀን ላይ ያከማቹትን ስታርች ነው፤ ይህም ተክሉ እንዳይራብና እድገት ማድረጉን እንዲቀጥል ያስችለዋል። በተጨማሪም ያጠራቀሙትን ስታርች ጥቅም ላይ የሚያውሉበት ሂደት በጣም ፈጣን ወይም በጣም አዝጋሚ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የተመጣጠነ ነው። ጎህ እስኪቀድ ማለትም ተጨማሪ ስታርች መሥራት የሚችሉበት ጊዜ እስከሚደርስ ድረስ 95 በመቶ ያህሉን ይጠቀሙበታል።

ጥናቱ የተካሄደው አራቢዶፕሲስ ታሊያና በተባለ የሰናፍጭ ዝርያ ላይ ነው። ሌሊቱ ሊነጋ የቀረው ሰዓት 8ም ሆነ 12 አሊያም 16 ይህ ተክል ያከማቸውን ምግብ እንደ ሌሊቱ ርዝማኔ አመጣጥኖ እንደሚጠቀም ተመራማሪዎች ደርሰውበታል። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ተክሉ ሊነጋ የቀረውን ሰዓት ግምት ውስጥ በማስገባት ያለውን ስታርች ያመጣጥናል፤ በዚህ መንገድ ምግቡን ጥቅም ላይ ሊያውል የሚችልበትን ከሁሉ የተሻለ ፍጥነት ያሰላል።

ለመሆኑ ዕፀዋት ምን ያህል የስታርች ክምችት እንዳላቸው የሚያውቁት እንዴት ነው? ጊዜን የሚለኩት እንዴት ነው? ስሌት የሚሠሩትስ ምን ዓይነት ዘዴ ተጠቅመው ነው? ወደፊት የሚደረጉ ተጨማሪ ምርምሮች ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ያስገኙ ይሆናል።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? ዕፀዋት ያላቸው የሒሳብ ችሎታ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?