በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

ልጆችን ማድነቅ የሚቻልበት መንገድ

ልጆችን ማድነቅ የሚቻልበት መንገድ

ተፈታታኙ ነገር

አንዳንዶች ልጅ ሁሌም መደነቅ እንዳለበት ያስባሉ። ሌሎች ደግሞ አንድ ልጅ ሁሌ ከተደነቀ እንደሚቀብጥና እንደሚሞላቀቅ ይሰማቸዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ልጃችሁ ምን ያህል መደነቅ እንዳለበት ብቻ ሳይሆን ምን ዓይነት አድናቆት ሊቸረው እንደሚገባም ልታስቡበት ይገባል። ልጃችሁን የሚያበረታታው ምን ዓይነት አድናቆት ነው? አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያሳድርበት የሚችለውስ ምን ዓይነት አድናቆት ነው? ጥሩ ውጤት በሚያስገኝ መንገድ ልጃችሁን ማድነቅ የምትችሉትስ እንዴት ነው?

ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር

ሁሉም አድናቆት አንድ ዓይነት ውጤት ይኖረዋል ማለት አይደለም። እስቲ የሚከተለውን አስቡ።

ከልክ ያለፈ አድናቆት ጎጂ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ወላጆች ልጃቸው በራስ የመተማመን ስሜት እንዲሰማው ሲሉ ከልክ በላይ ያሞግሱታል። ዶክተር ዴቪድ ዎልሽ “ልጆች ብልጥ ስለሆኑ አድናቆቱ ከልብ ይሁን አይሁን መለየት አያቅታቸውም” በማለት አስጠንቅቀዋል። አክለውም “የማይገባቸው [አድናቆት] እየተቸራቸው እንደሆነ ስለሚያውቁ በእናንተ መተማመን ሊቸገሩ ይችላሉ” ብለዋል። *

ችሎታቸውን ማድነቅ ጥሩ ነው። ለምሳሌ ልጃችሁ የሥዕል ተሰጥኦ አላት እንበል። ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን ለዚህ ተሰጥኦዋ አድናቆታችሁን እንደምትገልጹላት የታወቀ ነው፤ ይህም ችሎታዋን ይበልጥ እንድታዳብር ያነሳሳታል። ይሁንና እንዲህ ማድረግ አሉታዊ ውጤትም ሊኖረው ይችላል። በተሰጥኦ ላይ ብቻ ያተኮረ አድናቆት ልጃችሁ የምትወደውን ነገር ብቻ መሥራት እንዳለባት እንዲሰማት ያደርግ ይሆናል። አልፎ ተርፎም ሌላ ነገር ብትሞክር እንደማይሳካላት ስለሚሰማት ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መጋፈጥ ሊያስፈራት ይችላል። ‘ይህን ያህል የሚያታግለኝ ከሆነ ምን አለፋኝ? ለምን አልተወውም?’ ብላ ማሰብ ልትጀምር ትችላለች።

ጥረታቸውን ማድነቅ የተሻለ ነው። ልጆች ለተሰጥኦዋቸው ብቻ ሳይሆን ለጥረታቸውና ለጽናታቸውም የሚደነቁ ከሆነ አንድ መሠረታዊ እውነታ ይኸውም አንድን ችሎታ ለማዳበር ትዕግሥትና ጥረት እንደሚጠይቅ ይገነዘባሉ። ይህን ከተገነዘቡ ደግሞ “የፈለጉትን ውጤት ለማግኘት ጠንክረው ይሠራሉ” በማለት ሌቲንግ ጎ ዊዝ ላቭ ኤንድ ኮንፊደንስ የተባለው መጽሐፍ ተናግሯል። “አንድ ነገር ባይሳካላቸው እንኳ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ከስህተታቸው ይማራሉ።”

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ተሰጥኦዋቸውን ብቻ ሳይሆን ጥረታቸውንም አድንቁ። ልጃችሁን “የሚገርም የሥዕል ተሰጥኦ አለሽ” ከማለት ይልቅ “ይህን ሥዕል ብዙ እንደለፋሽበት ማየት ይቻላል” ማለቱ የተሻለ ውጤት ሊኖረው ይችላል። ሁለቱም ሐሳቦች አድናቆትን የሚገልጹ ናቸው፤ ሆኖም የመጀመሪያው አነጋገር ልጃችሁ የተሻለ መሥራት የምትችለው ተሰጥኦዋ የሆነውን ነገር ብቻ እንደሆነ እንዲሰማት ሊያደርግ ይችላል።

ልጃችሁን የሚያደርገውን ጥረት አይታችሁ የምታደንቁት ከሆነ፣ ችሎታ በልምምድ ሊዳብር እንደሚችል ይማራል። ይህ ደግሞ ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎችን በልበ ሙሉነት እንዲጋፈጥ ይረዳዋል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 14:23

ልጃችሁ ሳይሳካለት ሲቀርም ደግፉት። ጥሩ ሰዎችም እንኳ በተደጋጋሚ ስህተት ሊሠሩ ይችላሉ። (ምሳሌ 24:16) ሆኖም ስህተት በሠሩ ቁጥር ከስህተታቸው ይማራሉ። ልጃችሁ እንዲህ ያለ አዎንታዊ አመለካከት እንዲያዳብር ልትረዱት የምትችሉት እንዴት ነው?

አሁንም ቢሆን ልጁ በሚያደርገው ጥረት ላይ አተኩሩ። ለምሳሌ ያህል፣ ልጃችሁን ሁልጊዜ “አንተ እኮ የሒሳብ ተሰጥኦ አለህ” ትሉታላችሁ እንበል፤ ሆኖም አንድ ቀን በሒሳብ ትምህርት ዝቅተኛ ውጤት አመጣ። በዚህ ጊዜ ተሰጥኦውን እንዳጣና ለማሻሻል ጥረት ማድረጉም ቢሆን ምንም ለውጥ እንደማያመጣ ሊሰማው ይችላል።

ይሁንና ልጁ በሚያደርገው ጥረት ላይ ማተኮራችሁ በቀላሉ እጅ እንዳይሰጥ ይረዳዋል። ልጃችሁ አንድ ነገር ሳይሳካለት ቀረ ማለት አለቀለት ማለት እንዳልሆነ ይገነዘባል። ስለዚህ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ሌሎች ዘዴዎችን ይሞክራል አሊያም ተግቶ ይሠራል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ያዕቆብ 3:2

ገንቢ የሆነ አስተያየት ስጡ። በትክክለኛው መንገድ የተሰጠ አስተያየት የልጃችሁን ቅስም ከመስበር ይልቅ ይጠቅመዋል። በተጨማሪም ልጃችሁን ሁሌም በተገቢው ጊዜ የምታደንቁት ከሆነ ማስተካከያ እንዲያደርግ ስትነግሩት እርማቱን በደስታ ይቀበላል። እንደዚህ ማድረጋችሁ ልጃችሁ ስኬታማ እንዲሆን ይረዳዋል፤ ይህ ደግሞ ለእናንተም ሆነ ለእሱ ደስታ ያስገኛል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 13:4

^ አን.8 ኖ፦ ዋይ ኪድስ ኦቭ ኦል ኤጅስ ኒድ ቱ ሂር ኢት ኤንድ ዌይስ ፓረንትስ ካን ሴይ ኢት ከተባለው መጽሐፍ ላይ የተወሰደ።