አገሮችና ሕዝቦች
ኡዝቤኪስታንን እንጎብኝ
ትራንሳክሲኤነ። በወንዞች መካከል የምትገኝ ምድር። ታርታሪ። ቱርኪስታን። በዛሬው ጊዜ ኡዝቤኪስታን ማለትም “የኡዝቤኮች ምድር” የሚባለውን አገር የሚያካትተው አካባቢ እንዲህ ባሉ የተለያዩ ስሞች ይጠራ ነበር። የኡዝቤኪስታን ከተሞች ከ15ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ ሲልክ ሮድ (የሐር መንገድ) ተብሎ ይጠራ በነበረው መንገድ ይጠቀሙ ለነበሩ ነጋዴዎች ጠቃሚ አገልግሎት ይሰጡ ነበር፤ ይህ መንገድ በአንድ ወቅት ቻይናን ከሜድትራኒያን ጋር ያገናኝ ነበር። በአሁኑ ጊዜ በኡዝቤክ የጨርቃ ጨርቅ ገበያ ላይ ትልቁን ቦታ የያዘው ጥጥ ነው። ከጥጥ፣ ከሱፍ፣ ወይም ከሐር የተሠሩ የሚያምሩ ምንጣፎችም ይሸጣሉ።
በኡዝቤክ ባሕል ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩ በታሪክ ዘመናት የኖሩ የተለያዩ ሰዎች አሉ። ኃያል ሠራዊት የሚመሩ ታዋቂ ጦረኞች የኡዝቤኪስታንን ተራሮችና በረሃዎች አቋርጠዋል። ከእነዚህ መካከል ታላቁ እስክንድር (የሚወዳትን ሮክሳናን ያገኛት እዚህ ነው)፣ የሞንጎላውያን መሪ የነበረው ጀንጊስ ካን እንዲሁም በታሪክ ውስጥ እጅግ ሰፊ ግዛት ከነበሩት መካከል አንዱን ይገዛ የነበረው የአገሬው ተወላጅ ቲሙር (ታመርሌን በመባልም ይታወቃል) ይገኙበታል።
በሰማያዊ ጡቦች የተከደኑ ክብ ጣሪያዎች ያሏቸው፣ በቀለማት ያሸበረቁ ዕፁብ ድንቅ ታሪካዊ ሕንጻዎች ዘመናዊቷ ኡዝቤኪስታንን ውበት አጎናጽፈዋታል። ከእነዚህ ሕንጻዎች መካከል አብዛኞቹ ትምህርት ቤት ሆነው ያገለግላሉ።
ሲልክ ሮድ። ከክርስቶስ ልደት በፊት አንስቶ ወደ ሕንድ የሚወስደው የባሕር መንገድ እስከተከፈተበት እስከ 15ኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. መገባደጃ ድረስ አገልግሎት ይሰጥ የነበረ መንገድ ነው፤ የተለያዩ የንግድ መስመሮችን የሚያገናኘው ይህ መንገድ የዛሬዋን ኡዝቤኪስታንን አቋርጦ ያልፍ የነበረ ሲሆን በዚያን ጊዜ በነበረው ዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ቁልፍ ሚና ይጫወት ነበር።
የአራል ባሕር። በአንድ ወቅት በዓለማችን ካሉ ሐይቆች በትልቅነቱ በአራተኝነት ደረጃ ላይ ይገኝ የነበረው የአራል ባሕር ለመስኖ አገልግሎት እንዲውል በመደረጉ ምክንያት የባሕሩ መጠን በጣም ቀንሶ ሊጠፋ ተቃርቧል። ኡዝቤኪስታን በመካከለኛ እስያ ከሚገኙት ሌሎች አገሮች ጋር በመተባበር ለዚህ ችግር መፍትሔ ለማግኘት እየጣረች ነው።
በየጊዜው የሚለዋወጠው የኡዝቤኪስታን ፊደል። ኡዝቤኪስታን ውስጥ የተለያዩ ቋንቋዎች ይነገሩ የነበሩ ሲሆን በስምንተኛው መቶ ዘመን ሙስሊሞች ካደረጉት ወረራ በኋላ አረብኛ በስፋት ይሠራበት ጀመር። አገሪቱ ከሶቪየት ኅብረት ጋር ከተቀላቀለች በኋላ ደግሞ መጀመሪያ ላይ የላቲን ፊደል መጠቀም ተጀምሮ የነበረ ሲሆን በ1930ዎቹ መጨረሻ ላይ በሲሪሊክ ፊደል ተተካ። በ1993 በላቲን ፊደላት ላይ የተመሠረተ የኡዝቤክ ፊደል ሥራ ላይ እንዲውል የሚደነግግ አዲስ ሕግ ወጣ።