በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንድፍ አውጪ አለው?

ዘይት የሚያሟሙ ረቂቅ ተሕዋስያን

ዘይት የሚያሟሙ ረቂቅ ተሕዋስያን

በ2010 በሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ ላይ የነዳጅ ማውጫ መሣሪያ ፈንድቶ በሰመጠ ጊዜ ወደ አምስት ሚሊዮን በርሜል (800 ሚሊዮን ሊትር) የሚሆን ድፍድፍ ዘይት ባሕሩ ላይ ፈሰሰ። ይሁንና በወራት ጊዜ ውስጥ ዘይቱ ያስከተለው ብክለት ተወገደ። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ሳይንሳዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ብዙ የባሕር ላይ ባክቴሪያዎች በዘይት ውስጥ ያለውን የካርቦን ሞለኪውል ረጅም ሰንሰለት የመበጣጠስ አቅም አላቸው። ጥቃቅን ተሕዋስያን በአካባቢያችን ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ የሚያጠኑት ፕሮፌሰር ቴሪ ሄዘን እነዚህን ተሕዋስያን “ዘይት አዳኝ ሚሳይሎች” በማለት ጠርተዋቸዋል። በመግቢያው ላይ ለተጠቀሰው በሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ ለተከናወነው ነገር እነዚህ ተሕዋስያን የበኩላቸውን ድርሻ አበርክተዋል።

በቢቢሲ የቀረበ አንድ ዘገባ “ባሕር ውስጥ ዘይት የተራቡ ተሕዋስያን መኖራቸው የሚያስገርም አይደለም” ሲል ገልጿል። ምክንያቱም ከረጅም ዘመናት አንስቶ ‘በተፈጥሮ ከውቅያኖስ ወለል እያፈተለከ ወደ ውኃው የሚወጣ ዘይት አለ።’

እርግጥ ነው፣ የሰው ልጆች ወደ ባሕር የፈሰሰውን ዘይት ለማጽዳት ያደረጉት ጥረት አመርቂ ውጤት አስገኝቷል። ሆኖም የሰው ልጆች የፈሰሰ ዘይት ለማጽዳት የሚያደርጉት ከሁሉ የተሻለ ነው የተባለው ጥረት እንኳ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል። ኬሚካሎችን ተጠቅሞ ዘይትን ከባሕር ለማስወገድ መጣር ተፈጥሯዊው ሂደት ሊያስገኝ የሚችለውን ጠቃሚ ውጤት ያስተጓጉላል። በተጨማሪም እንዲህ ያሉ ኬሚካሎች መርዛማ ከመሆናቸውም ሌላ በአካባቢ ላይ ዘላቂ የሆነ የጎንዮሽ ጉዳት ያስከትላሉ። ሆኖም ዘይትን የተራቡ ተሕዋስያንን ጨምሮ ተፈጥሮ ያለው ዘይትን የማሟሟት ችሎታ ባሕር ራሱን በራሱ የማጽዳት ሂደቱን እንዲጀምር ያስችላሉ፤ ይህ ደግሞ ሰው ሠራሽ ከሆኑት ዘዴዎች በተቃራኒ የጎንዮሽ ጉዳት የለውም። *

ታዲያ ምን ይመስልሃል? በባሕር ውስጥ የሚገኙት ዘይትን ሙልጭ አድርገው የሚያጸዱት ተሕዋስያን እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኙ ናቸው? ወይስ ንድፍ አውጪ አላቸው?

^ አን.6 በሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ ላይ የተከሰተው አደጋ በባሕሩ ውስጥ ባሉት ሕያዋን ፍጥረታት ላይ ምን ዓይነት ዘላቂ ጉዳት ሊኖረው እንደሚችል በአሁኑ ሰዓት በእርግጠኝነት መናገር አንችልም።