በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መቻቻል

መቻቻል

ሰዎችን በማንነታቸው መቀበል፣ ይቅር ባይ መሆንና መቻቻል ሰላማዊ ግንኙነት ያሰፍናል። ይሁንና መቻቻል ገደብ ሊኖረው ይገባል?

መቻቻልን ለማዳበር ቁልፉ ምንድን ነው?

በዛሬው ጊዜ ያለው እውነታ

በዓለም ዙሪያ ተቻችሎ ያለመኖር ነፋስ በኃይለኛው እየነፈሰ ነው። ሰዎችን በዘራቸው ወይም በጎሳቸው በጭፍን መጥላት፣ ብሔራዊ ስሜት፣ ወገናዊነትና ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት ደግሞ ነፋሱን ያራግባሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ኢየሱስ ክርስቶስ አገልግሎቱን በሚያከናውንበት ወቅት ያለመቻቻል ባሕርይ በሚያንጸባርቁ ሰዎች ተከብቦ ነበር። በተለይ አይሁዳውያንና ሳምራውያን አንዳቸው ለሌላው ጥላቻ ነበራቸው። (ዮሐንስ 4:9) በወቅቱ በነበረው ኅብረተሰብ ሴቶች ከወንዶች እንደሚያንሱ ተደርገው ይታያሉ። ከዚህም ሌላ የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ለተራው ሕዝብ ንቀት ነበራቸው። (ዮሐንስ 7:49) ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ፍጹም የተለየ አቋም ተከትሏል። ተቃዋሚዎቹ እንኳ “ይህ ሰው ኃጢአተኞችን ይቀበላል፤ ከእነሱም ጋር ይበላል” ብለውታል። (ሉቃስ 15:2) ኢየሱስ የመጣው ሰዎችን በመንፈሳዊ ለመፈወስ እንጂ በእነሱ ላይ ለመፍረድ ስላልሆነ ደግነትና ትዕግሥት ያሳያቸው ከመሆኑም በላይ ችሏቸው ኖሯል። ማንኛውንም ነገር ያደረገው በፍቅር ተነሳስቶ ነው።—ዮሐንስ 3:17፤ 13:34

በመቻቻል ረገድ ምሳሌ ተደርጎ የሚታየው ኢየሱስ፣ የመጣው ሰዎችን በመንፈሳዊ ለመፈወስ እንጂ በእነሱ ላይ ለመፍረድ አይደለም

ፍቅር ሰዎች አለፍጽምናና ያልተለመደ ባሕርይ ቢኖራቸውም እንኳ ልባችንን ክፍት እንድናደርግላቸውና ድክመታቸውን ችለን እንድንኖር የሚረዳን ቁልፍ ባሕርይ ነው። ቆላስይስ 3:13 “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እንኳ እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ” ይላል።

“ከሁሉም በላይ አንዳችሁ ለሌላው የጠለቀ ፍቅር ይኑራችሁ፤ ምክንያቱም ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል።”1 ጴጥሮስ 4:8

መቻቻል በገደብ ሊሆን የሚገባው ለምንድን ነው?

እውነታው

ብዙ ማኅበረሰቦች ሕግና ሥርዓት ለማስከበር ጥረት ያደርጋሉ። በዚህ የተነሳ የሰዎችን ምግባር በተመለከተ ምክንያታዊ የሆነ ገደብ ማውጣታቸው የተለመደ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

“[ፍቅር] ጨዋነት የጎደለው ምግባር አያሳይም።” (1 ቆሮንቶስ 13:5) ኢየሱስ በመቻቻል ረገድ ምሳሌ ተደርጎ የሚታይ ቢሆንም ጨዋነት የጎደለውን ምግባር፣ ግብዝነትንና ሌሎች የክፋት ድርጊቶችን ችላ ብሎ አላለፈም። ከዚህ ይልቅ እነዚህን ድርጊቶች በድፍረት አውግዟል። (ማቴዎስ 23:13) ‘መጥፎ ነገር የሚያደርግ ሁሉ [የእውነትን] ብርሃን ይጠላል’ በማለት ተናግሯል።—ዮሐንስ 3:20

ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ “ክፉ የሆነውን ተጸየፉ፤ ጥሩ የሆነውን አጥብቃችሁ ያዙ” ሲል ጽፏል። (ሮም 12:9) እሱ ራሱም ይህን መመሪያ አክብሮ ኖሯል። ለምሳሌ አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች፣ አይሁዳውያን ካልሆኑት ክርስቲያኖች ራሳቸውን ባገለሉ ጊዜ ጳውሎስ ራሱ አይሁዳዊ ቢሆንም እንኳ ደግነት በተሞላበት መንገድ የሠሩትን ስህተት በግልጽ ነግሯቸዋል። (ገላትያ 2:11-14) ጳውሎስ፣ ‘የማያዳላው’ አምላክ ሕዝቦቹ የዘር ጥላቻ ቢያሳዩ ጉዳዩን በቸልታ እንደማያልፍ ያውቅ ነበር።—የሐዋርያት ሥራ 10:34

የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያኖች እንደመሆናቸው መጠን መጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር መመሪያ አድርገው ይቀበላሉ። (ኢሳይያስ 33:22) በመሆኑም በእነሱ መካከል አንድ ሰው የክፋት ድርጊት ቢፈጽም ጉዳዩን በቸልታ አያልፉም። ንጹሕ የሆነው የክርስቲያን ጉባኤ የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በማይከተሉ ሰዎች መበከል የለበትም። ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች “ክፉውን ሰው ከመካከላችሁ አስወግዱት” የሚለውን ግልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ይታዘዛሉ።—1 ቆሮንቶስ 5:11-13

“እናንተ ይሖዋን የምትወዱ፣ ክፉ የሆነውን ነገር ጥሉ።”መዝሙር 97:10

አምላክ ክፋትን ለዘላለም ዝም ብሎ ያያል?

ብዙዎች ምን ብለው ያምናሉ?

ክፋት የሰው ተፈጥሯዊ ባሕርይ በመሆኑ ምንጊዜም አብሮን ይኖራል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ነቢዩ ዕንባቆም ወደ ይሖዋ አምላክ እንዲህ በማለት ጸልዮ ነበር፦ “ለምን በደል ሲፈጸም እንዳይ ታደርገኛለህ? ጭቆናንስ ለምን ዝም ብለህ ታያለህ? ጥፋትና ግፍ በፊቴ የሚፈጸመው ለምንድን ነው? ጠብና ግጭትስ ለምን በዛ?” (ዕንባቆም 1:3) አምላክ፣ ሁኔታው ያስጨነቀው ይህ ነቢይ በጥርጣሬ ተውጦ እንዲኖር አላደረገም፤ ከዚህ ይልቅ ክፉዎችን ወደ ፍርድ እንደሚያመጣ አስረግጦ ነግሮታል። ይህን ተስፋ አስመልክቶ አምላክ “ያላንዳች ጥርጥር ይፈጸማልና። ራእዩ አይዘገይም!” ብሏል።—ዕንባቆም 2:3

እስከዚያ ድረስ ግን ክፉ አድራጊዎች ከመጥፎ ጎዳናቸው የመመለስ አጋጣሚ አላቸው። “‘እኔ በክፉ ሰው ሞት ደስ እሰኛለሁ?’ ይላል ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ። ‘እኔ ደስ የምሰኘው ከመንገዱ ቢመለስና በሕይወት ቢኖር አይደለም?’” (ሕዝቅኤል 18:23) መጥፎ ጎዳናቸውን በመተው ይሖዋን የሚፈልጉ ሰዎች የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ ይችላሉ። ምሳሌ 1:33 “እኔን የሚሰማ ሰው ግን ተረጋግቶ ይኖራል፤ መከራ ይደርስብኛል የሚል ስጋትም አያድርበትም” ይላል።

“ለጥቂት ጊዜ ነው እንጂ ክፉዎች አይኖሩም፤ . . . የዋሆች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል።”መዝሙር 37:10, 11