በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አፕላይ ዩርሰልፍ ቱ ሪዲንግ ኤንድ ራይቲንግ የተባለው ጽሑፍ ከ100 በሚበልጡ ቋንቋዎች በብዙ ሚሊዮን በሚቆጠሩ ቅጂዎች ተዘጋጅቷል

የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማንበብና መጻፍ መማርን ያበረታታል

የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማንበብና መጻፍ መማርን ያበረታታል

“ማንበብና መጻፍ ሰብዓዊ መብት ነው፤ አንድ ሰው ችሎታውን እንዲያጎለብት የሚረዳ እንዲሁም በግለሰብም ሆነ በማኅበረሰብ ደረጃ እድገት እንዲታይ የሚያስችል መሣሪያ ነው።”—ዩኒስኮ *

የተለያዩ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት በዓለም ዙሪያ ዕድሜያቸው 15 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ከ700 ሚሊዮን በላይ የሆኑ ሰዎች ማንበብና መጻፍ አይችሉም። በዚህም የተነሳ እነዚህ ሰዎች “ለእኛ ትምህርት እንዲሆን” የተጻፈልንን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረውን ጠቃሚ ሥነ ምግባራዊም ሆነ መንፈሳዊ ትምህርት ብሎም በዓለም ላይ የሚገኘውን ሰፊ የእውቀት ክምችት መመርመር አይችሉም። (ሮም 15:4) ስለሆነም የይሖዋ ምሥክሮች በበርካታ አገሮች በሚያካሂዱት ከክፍያ ነፃ በሆነ መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ፕሮግራማቸው ውስጥ ማንበብና መጻፍ ማስተማርንም አካተዋል። ታዲያ ይህ ፕሮግራም ውጤት አስገኝቷል?

የይሖዋ ምሥክሮች፣ ስፓንኛ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎች በሚበዙባት በሜክሲኮ ያከናወኑትን ሥራ እንመልከት። የይሖዋ ምሥክሮች ከ1946 ጀምሮ ከ152,000 ለሚበልጡ ሰዎች ማንበብና መጻፍ ያስተማሩ ሲሆን ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል ብዙዎቹ ከጊዜ በኋላ እነሱ ራሳቸው አስተማሪዎች ሆነዋል። የሜክሲኮ መንግሥት ምሥክሮቹ ላከናወኑት ሥራ እውቅና በመስጠት በርካታ የምስጋና ደብዳቤዎችን ልኳል። ከደብዳቤዎቹ አንዱ እንዲህ ይላል፦ “ይህ ሁለገብ የትምህርት ቦርድ፣ በጎልማሶች የትምህርት ፕሮግራም ላበረከታችሁት አስተዋጽኦ እውቅና መስጠትና ምስጋና ማቅረብ ይፈልጋል።”

ከዚህ የትምህርት ፕሮግራም ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን ተጠቅመዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ኮሳፌና በኮርሱ ለመካፈል ሲመዘገቡ የ101 ዓመት አረጋዊት የነበሩ ሲሆን ትምህርቱን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ በተሳካ ሁኔታ አጠናቀዋል!

የሜክሲኮ የሥራ ቋንቋ ስፓንኛ ቢሆንም ማንበብና መጻፍ የማስተማር ፕሮግራሙ የሚካሄደው በዚህ ቋንቋ ብቻ አይደለም። በ2013፣ በአካባቢያቸው በሚነገሩ በተለያዩ ስምንት ቋንቋዎች የሚጠቀሙ ሰዎች በዚህ ፕሮግራም አማካኝነት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ማንበብና መጻፍ ችለዋል።

በእርግጥም ማንበብና መጻፍ አንድ ሰው ብዙ አዳዲስ ነገሮችን መማር እንዲችል አጋጣሚ የሚከፍትለት ጠቃሚ እሴት ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ማንበብና መጻፍ መቻል ሁሉም ዓይነት ሰዎች፣ ባሪያ አድርገው ከሚገዟቸው አጉል እምነቶች ብሎም የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶችና ጎጂ ልማዶች እንዲላቀቁ የሚረዳቸውን በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈውን መጽሐፍ ይኸውም መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነቡ አስችሏቸዋል።—ዮሐንስ 8:32

^ አን.2 የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት።