ፓሮት ፊሽ—አሸዋ አምራች ማሽን
አሸዋ የሚገኘው ከምንድን ነው? ብዙ መንገዶች አሉ። በዚህ ርዕስ ላይ የተገለጸው ግን ሊያስደንቃችሁ ይችላል። ፓሮት ፊሽ ኮራል የሚባለውን የባሕር ፍጥረት ፈጭቶ ወደ ደቃቅ አሸዋነት ይቀይረዋል!
ፓሮት ፊሽ በመላው ዓለም በሚገኙ ሞቃታማ አካባቢዎች ባሉ ባሕሮች ውስጥ ይኖራል። እነዚህ ዓሣዎች አኝከው ያደቀቁትን ኮራል ከዋጡ በኋላ ከውስጡ የሚፈልጉትን ነገር አስቀርተው ሌላውን በአሸዋ መልክ ያስወጣሉ። ፓሮት ፊሽ ይህን የሚያደርገው ጠንካራ በሆኑት መንቁር የመሰሉ መንገጭላዎቹና በመንጋጋዎቹ ነው። አንዳንዶቹ የፓሮት ፊሽ ዝርያዎች ጥርሳቸው ሳይሸረፍ እስከ 20 ዓመት ድረስ ይኖራሉ።
ፓሮት ፊሽ በአንዳንድ አካባቢዎች የሞቱ ኮራሎችን ያለማቋረጥ በማኘክ የሚያመርቱት አሸዋ ብዛት በተፈጥሮ ከሚገኘው አሸዋ ይበልጣል። አንዳንድ ተመራማሪዎች አንድ ፓሮት ፊሽ በዓመት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠር ኪሎ አሸዋ እንደሚያመርት ይገምታሉ።
ፓሮት ፊሽ የሚያከናውነው ሌላ ጠቃሚ ሥራም አለ። የሞቱና አልጌ የተሸፈኑ ኮራሎችን እንዲሁም ሌሎች ዕፀዋትን በመመገብ ኮራሎቹ ንጹሕ እንዲሆኑ ያስችላሉ። በዓይነቱ ልዩ የሆነው የፓሮት ፊሽ አመጋገብ ለኮራል ሪፎቹ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል። ፓሮት ፊሽና ዕፀዋት የሚመገቡ ሌሎች ፍጥረታት በማይኖሩበት ጊዜ ኮራል ሪፎች ወዲያው በአልጌና በባሕር አረም ይሸፈናሉ። “በዚህ ዘመን የሚገኙት ሪፎች፣ ዕፀዋት የሚመገቡ ፍጥረታት ባይኖሩ ኖሮ አሁን ባሉበት ሁኔታ ላይ ሊገኙ እንደማይችሉ አንዳንዶች ይናገራሉ” በማለት ሪፍ ላይፍ የተባለው መጽሐፍ ይገልጻል።
ይህን የሚያህል ብዙ ሥራ በቀን ለመሥራት ማታ ላይ ጥሩ እረፍት ማግኘት ያስፈልጋል፤ በዚህ ረገድ ፓሮት ፊሽ ለየት ያለ ባሕርይ አለው። የሌሊቱ ጊዜ አዳኞች በብዛት የሚሰማሩበት ጊዜ ስለሆነ በጣም አደገኛ ነው። ብዙ ጊዜ ፓሮት ፊሽ ስርቻ ውስጥ ተደብቀው ይተኛሉ፤ ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው መሸሸጊያ ከተራቡ ሻርኮች ሊያድናቸው አይችልም።
አንዳንድ የፓሮት ፊሽ ዝርያዎች ተጨማሪ ጥበቃ ለማግኘት ማታ ማታ ራሳቸውን ይጠቀልላሉ። መላ አካላቸውን የሚያለብስ የሌሊት ልብስ የሚመስል ልፋጭ ያመነጫሉ። ይህ መጥፎ ጠረን ያለው መከላከያ ሽፋን ከአዳኝ እንስሳት እንደሚጠብቃቸው ስለ ባሕር ፍጥረታት የሚያጠኑ የሳይንስ ሊቃውንት ይናገራሉ።
ፓሮት ፊሽ በኮራል ሪፎች ውስጥ በብዛት ከሚታዩትና እጅግ ከሚያምሩት የዓሣ ዝርያዎች አንዱ ነው። ደማቅ ቀለም ያላቸው (እንዲህ ዓይነቱ ቀለም የሚኖራቸው እያደጉ ሲሄዱ ነው) ወንድና ሴት ፓሮት ፊሾች እጅብ ብለው ሲጓዙ ማየት የተለመደ ነው። የፓሮት ፊሽ ዝርያዎች በብዛት በማይታደኑባቸው አካባቢዎች ለማዳ ሆነው መኖር ይችላሉ። በመሆኑም በቀላሉ ከሚታዩት የዓሣ ዝርያዎች መካከል አንዱ ይህ ዓሣ ነው።
ፓሮት ፊሾች ኮራል ሲፈጩ መስማትና በቅርበት መመልከት ለብዙዎች የማይረሳ ትዝታ ጥሎ የሚያልፍ ነገር ነው። ፓሮት ፊሾች እጅብ ብለው ሲሄዱ ከሚፈጥሩት ውበት በተጨማሪ አካባቢያቸውን በማጽዳት ለባሕር ፍጥረታትም ሆነ ለሰዎች ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ።