በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ለቤተሰብ | ትዳር

የጋብቻን ቃለ መሐላ ጠብቆ መኖር የሚቻለው እንዴት ነው?

የጋብቻን ቃለ መሐላ ጠብቆ መኖር የሚቻለው እንዴት ነው?

ተፈታታኙ ነገር

በሠርጋችሁ ዕለት ቃለ መሐላ ፈጽማችኋል። በዚያ ዕለት የገባችሁት ቃል ዕድሜ ልክ የሚጸና ነበር፤ የሚያጋጥማችሁን ማንኛውንም ችግር በመፍታት ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ተጣብቃችሁ ለመኖር ቃል ገብታችኋል።

ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ግን በትዳር ውስጥ በሚያጋጥሙ ችግሮች ምክንያት ግንኙነታችሁ እየሻከረ ሄዷል። ታዲያ ለትዳር ጓደኛችሁ የገባችሁትን ቃል ትጠብቃላችሁ?

ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር

ቃለ መሐላ ትዳራችሁ እንዳይናጋ እንደሚያደርግ መልሕቅ ነው

ቃል መግባታችሁ ለችግሩ መፍትሔ እንጂ መንስኤ አይደለም። በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ቃለ መሐላ ለመፈጸም ይሰጋሉ። አንዳንድ ሰዎች ቃለ መሐላን ካደረግነው መጥፎ ውሳኔ ጋር ጠፍሮ ከሚያስር እግር ብረት ጋር ያመሳስሉታል። ከዚህ ይልቅ ቃለ መሐላን ትዳራችሁ እንዳይናጋ እንደሚያደርግ መልሕቅ አድርጋችሁ ተመልከቱት። ሜጋን የተባለች አንዲት ባለትዳር ሴት “ቃለ መሐላ መግባት ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች አንዱ በትዳራችሁ ውስጥ አለመግባባት በሚከሰትበት ጊዜ እናንተም ሆናችሁ የትዳር ጓደኛችሁ ትዳራችሁን ጥላችሁ እንዳትሄዱ ማድረጉ ነው” ብላለች። * ትዳራችሁ አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩበትም ይፈርሳል የሚል ስጋት የሌላችሁ መሆኑ ችግሩን ለመፍታት እንድትነሳሱ ያደርጋችኋል።—“ ቃለ መሐላን ጠብቆ መኖርና ታማኝነት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ዋናው ነጥብ፦ በትዳርህ ውስጥ አለመግባባት ከተፈጠረ የገባኸውን ቃል ጠብቀህ ለመኖር ጥረት አድርግ እንጂ መሐላውን በመፈጸምህ አትቆጭ። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

 ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

አመለካከትህን መርምር። “የዕድሜ ልክ ጥምረት።” ይህ አባባል መፈናፈኛ እንደሚያሳጣ ሆኖ ይሰማሃል ወይስ ተረጋግተህ እንድትኖር ያደርግሃል? ችግር በሚነሳበት ጊዜ ጥሎ መሄድ እንደ አማራጭ ሆኖ ይታይሃል? ቃለ መሐላህን ለማጠናከር ጋብቻን እንደ ዘላቂ ጥምረት አድርጎ መመልከት አስፈላጊ ነው።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ማቴዎስ 19:6

አስተዳደግህን መለስ ብለህ ተመልከት። በወላጆችህ ላይ የተመለከትከው ሁኔታ ለቃለ መሐላ ባለህ አመለካከት ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ ይሆናል። ሊያ የተባለች አንዲት ባለትዳር እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ የተፋቱት ገና ልጅ ሳለሁ ነበር፤ በመሆኑም በእነሱ ላይ የደረሰው ሁኔታ ለቃለ መሐላ አሉታዊ አመለካከት እንዲኖረኝ አድርጎ ይሆን? ብዬ እሰጋለሁ።” ትዳራችሁን ከእነሱ በተለየ መንገድ መምራት እንደምትችሉ እርግጠኛ ሁኑ። የወላጆቻችሁን ስህተት የግድ መድገም አያስፈልጋችሁም!—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ገላትያ 6:4, 5

ስለምትናገረው ነገር አስብ። ከትዳር ጓደኛህ ጋር የተፈጠረው አለመግባባት በሚካረርበት ጊዜ “ጥዬሽ እሄዳለሁ” ወይም “ስንት የሚያደንቁኝ ሰዎች አሉ” እንደሚሉ ያሉትን የምትቆጭባቸውን አነጋገሮች አስወግድ። እንደነዚህ ያሉት አነጋገሮች የገባኸውን ቃል አክብደህ እንደማታይ የሚያሳዩ ከመሆናቸውም በላይ የተነሳውን ችግር ከመፍታት ይልቅ ሁለታችሁንም ኃይለ ቃል ወደ መናገር ይመሯችኋል። ጎጂ ቃላት ከመናገር ይልቅ እንዲህ ልትል ትችላለህ፦ “ሁለታችንም እንደተበሳጨን ግልጽ ነው። ይሁንና ይህን ችግር እንዴት መፍታት እንችላለን?”—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 12:18

ቃለ መሐላህን ጠብቀህ ለመኖር እንደምትፈልግ የሚያሳዩ ነገሮችን አድርግ። በሥራ ቦታ የትዳር ጓደኛህን ፎቶግራፍ ጠረጴዛህ ላይ አስቀምጥ። ስለ ትዳር ጓደኛህ ለሌሎች ስታወራ አዎንታዊ ነገሮችን ተናገር። ለተወሰነ ጊዜ ከቤት ርቀህ የምትሄድ ከሆነ በየቀኑ ለባለቤትህ ስልክ ለመደወል ግብ አውጣ። ብዙ ጊዜ በጋራ ስላደረጋችኋቸው ነገሮች ተናገር፤ “እኔና ባለቤቴ” እንደሚሉ ያሉ አባባሎችን ተጠቀም። እንዲህ ስታደርግ ለትዳር ጓደኛህ የገባኸውን ቃል ከፍ አድርገህ እንደምትመለከት ለሌሎች ታሳያለህ፤ አንተም ብትሆን ቃለ መሐላህን ዘወትር እንድታስታውስ ያደርግሃል።

ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑህን ሰዎች ፈልግ። በትዳራቸው ውስጥ ያጋጠሟቸውን ችግሮች በተሳካ ሁኔታ የተወጡ የጎለመሱ ባልና ሚስቶችን ተመልከት። “ቃለ መሐላን ጠብቆ መኖር ለእናንተ ምን ትርጉም አለው? ለትዳራችሁስ ምን አስተዋጽኦ አድርጓል?” ብላችሁ ጠይቋቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “ብረት ብረትን እንደሚስል ሁሉ ሰውም ጓደኛውን ይስለዋል” ይላል። (ምሳሌ 27:17) ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በአእምሮህ በመያዝ በትዳራቸው ስኬታማ የሆኑ ሰዎችን ለምን ምክር አትጠይቅም?

^ አን.7 መጽሐፍ ቅዱስ ያገባ ሰው የትዳር ጓደኛውን መፍታት የሚችለው የፆታ ብልግና ከፈጸመ ብቻ እንደሆነ ይናገራል። “መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?—ምንዝር” የሚለውን በዚህ መጽሔት ውስጥ የሚገኘውን ርዕስ ተመልከት።