በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የምትጠቀመው በጥበብ ነው?

የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የምትጠቀመው በጥበብ ነው?

ጄኒ፣ የቪዲዮ ጌም ሱስ ሆኖባታል። እንዲህ ብላለች፦ “አሁን አሁን በየቀኑ ለስምንት ሰዓት ያህል ጌም እጫወታለሁ፤ ትልቅ ችግር ሆኖብኛል ማለት ይቻላል።”

ዴኒስ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችና ኢንተርኔት ሳይጠቀም ለሰባት ቀን ለመቆየት ሞክሮ ነበር። ይሁንና ይህን ማድረግ የቻለው ለ40 ሰዓት ብቻ ነበር።

ጄኒ እና ዴኒስ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች አይደሉም። ጄኒ የአራት ልጆች እናት ስትሆን 40 ዓመቷ ነው። ዴኒስ ደግሞ 49 ዓመቱ ነው።

አንተስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን * ትጠቀማለህ? ብዙ ሰዎች የእነዚህ ነገሮች ተጠቃሚ ሲሆኑ ይህን የሚያደርጉበት አስፈላጊ ምክንያትም አላቸው። የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ከሥራ፣ ከማኅበራዊ ሕይወትና ከመዝናኛ ጋር በተያያዘ ጉልህና ጠቃሚ ሚና ይጫወታሉ።

ይሁን እንጂ እንደ ጄኒ እና ዴኒስ ያሉ ብዙ ሰዎች ከአንዳንድ የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ጋር ከልክ በላይ የተቆራኙ ይመስላል። ለምሳሌ ያህል፣ የ20 ዓመቷ ኒኮል እንዲህ ትላለች፦ “ነገሩ ባያስደስተኝም እኔና ሞባይሌ የማንነጣጠል ጓደኛሞች ሆነናል። ሞባይሌ ከአጠገቤ እንዲርቅ አልፈልግም። ኔትወርክ በሌለበት አካባቢ ከሆንኩ ላብድ እደርሳለሁ፤ እንዲሁም በግማሽ ሰዓት ውስጥ የተላኩልኝን መልእክቶች ማየት አለብኝ። ሁኔታው ትንሽ ለማመን ይከብዳል!”

እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች የተላኩላቸውን መልእክቶችና ወቅታዊ ነገሮች ለማየት ሲሉ ሌሊቱን በተደጋጋሚ ከእንቅልፋቸው ይነሳሉ። እነዚህ ሰዎች ጓደኛቸው ከሆነው የቴክኖሎጂ ውጤት ሲነጠሉ ሱስ የሆነበትን ነገር ያቆመ ሰው የሚያድርበት ዓይነት የስሜት ቀውስ ሊያጋጥማቸው ይችላል። አንዳንድ ተመራማሪዎች ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ሱስ ተብሎ ሊጠራ እንደሚችል ይናገራሉ፤ አንድ ሰው በአጠቃላይ ከቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር ወይም በተናጠል ከኢንተርኔት አሊያም እንደ ሞባይል ካለ አንድ መሣሪያ ጋር እንዲህ ያለ ቁርኝት ሊፈጥር ይችላል። ሌሎች ግን ይህን ችግር የሚገልጸው “ሱስ” የሚለው ቃል ሳይሆን አስቸጋሪ የሆነ አባዜ የሚለው አገላለጽ እንደሆነ ይሰማቸዋል።

ይህ ሁኔታ ምንም ተባለ ምን፣ ጥበብ የጎደለው የቴክኖሎጂ ውጤቶች አጠቃቀም ችግር ሊፈጥር ይችላል። በአንዳንድ ሁኔታዎች በቤተሰብ አባላት መካከል ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት የ20 ዓመት ወጣት እንደሚከተለው በማለት ምሬቷን ገልጻለች፦ “አባቴ በእኔ ሕይወት ውስጥ እየተከናወነ ስላለው ነገር ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። ሳሎን ውስጥ ተቀምጦ እኔን እያነጋገረኝ የኢሜይል መልእክቶችን ይጽፋል። ስልኩን ለአፍታ እንኳ ማስቀመጥ አይችልም። አባቴ ምናልባት ያስብልኝ ይሆናል፤ አንዳንድ ጊዜ ግን እንደሚያስብልኝ አይሰማኝም።”

የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለተወሰነ ጊዜ አለመጠቀም

እንደ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ዩናይትድ ኪንግደም ያሉ አገሮች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን አላግባብ መጠቀምን ለማስቀረት ሲሉ አንድ ግለሰብ ለበርካታ ቀናት ኢንተርኔትንና የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን ሳይጠቀም እንዲቆይ የሚደረግባቸው ማዕከላት አቋቁመዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ብሬት የተባለውን ወጣት እንመልከት፤ ይህ ወጣት፣ በአንድ ወቅት በየቀኑ ለ16 ሰዓታት የኢንተርኔት ጌሞችን በመጫወት ያሳልፍ እንደነበረ ተናግሯል። “ኢንተርኔት ስጠቀም በዕፅ የመረቀንኩ ያህል ሆኖ ይሰማኝ ነበር” ብሏል። ብሬት ቀደም ሲል ወደተጠቀሰው ዓይነት ማዕከል በገባበት ወቅት ሥራ አልነበረውም፤ ንጽሕናውን የማይጠብቅ ሰው ነበር፤ እንዲሁም ምንም ጓደኛ አልነበረውም። አንተስ እንዲህ ዓይነቱ አሳዛኝ ውጤት እንዳይደርስብህ መከላከል የምትችለው እንዴት ነው?

የቴክኖሎጂ ውጤቶች አጠቃቀምህን ገምግም። ቴክኖሎጂ በሕይወትህ ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሆነ ለማወቅ ሞክር። ራስህን እንደሚከተለው እያልክ ጠይቅ፦

  • ኢንተርኔት ወይም የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዬን መጠቀም ካልቻልኩ ከልክ በላይ እበሳጫለሁ ወይም እነጫነጫለሁ?

  • ኢንተርኔት ወይም የቴክኖሎጂ መሣሪያ ስጠቀም አስቀድሜ ከወሰንኩት ጊዜ የበለጠ ጊዜ እወስዳለሁ?

  • ምን መልእክቶች እንደመጡልኝ ለማየት ስል በተደጋጋሚ ከእንቅልፌ እነሳለሁ?

  • የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የምጠቀምበት መንገድ ቤተሰቤን ችላ እንድል እያደረገኝ ነው? የቤተሰቤ አባላት ለዚህ ጥያቄ በምሰጠው መልስ ይስማማሉ?

የቴክኖሎጂ አጠቃቀምህ ቤተሰብህንና ሌሎች ኃላፊነቶችን ጨምሮ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች” ችላ እንድትል እያደረገህ ከሆነ ለውጥ ማድረግ ያለብህ አሁን ነው። (ፊልጵስዩስ 1:10) እንዴት?

ምክንያታዊ የሆኑ ገደቦችን አውጣ። ጥሩ ነገርም እንኳ ከመጠን ያለፈ ከሆነ ጎጂ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም የቴክኖሎጂ ውጤቶችን የምትጠቀመው ለሥራም ይሁን ለመዝናኛ ለምን ያህል ጊዜ እንደምትጠቀም አስቀድመህ ወስን፤ ከዚያም ያወጣኸውን የጊዜ ገደብ አክብር።

ጠቃሚ ምክር፦ በዚህ ረገድ አንድ የቤተሰብህ አባል ወይም ጓደኛህ እንዲረዳህ ለምን አትጠይቅም? መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል፤ . . . አንዱ ቢወድቅ ሁለተኛው ባልንጀራውን ደግፎ ሊያነሳው ይችላልና” ይላል።—መክብብ 4:9, 10

በቴክኖሎጂ ውጤቶች ለመጠቀም ያለህ ፍላጎት ወደ “ሱሰኝነት” እንዲመራህ አትፍቀድ

መረጃዎችን ይበልጥ ቀላልና ፈጣን በሆነ መንገድ ለማግኘትና ለማስተላለፍ የሚረዱ አዳዲስ መሣሪያዎች በተፈለሰፉ መጠን ጥበብ የጎደለው የቴክኖሎጂ አጠቃቀምም እየጨመረ እንደሚሄድ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ በእነዚህ ነገሮች ለመጠቀም ያለህ ፍላጎት ወደ “ሱሰኝነት” እንዲመራህ አትፍቀድ። ‘ጊዜህን በተሻለ መንገድ የምትጠቀም’ ከሆነ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በአግባቡ መጠቀም ትችላለህ።—ኤፌሶን 5:16

^ አን.5 በዚህ ርዕስ ውስጥ “የቴክኖሎጂ ውጤቶች” የሚለው ስያሜ ኤሌክትሮኒክ መረጃዎችን ለማግኘት ወይም ለማስተላለፍ የሚያስችሉ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን ያመለክታል፤ ከእነዚህ መረጃዎች መካከል የኢ-ሜይል መልእክቶች፣ የስልክ ጥሪዎች፣ የሞባይል መልእክቶች፣ ቪዲዮዎች፣ ሙዚቃ፣ ጌሞችና ፎቶዎች ይገኙበታል።