በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

አምላክ አለ? ይህን ማወቅ ምን ለውጥ ያመጣል?

አምላክ አለ? ይህን ማወቅ ምን ለውጥ ያመጣል?

ብዙዎች፣ ስለ አምላክ መኖር የሚነሳው ጥያቄ መልስ እንደማይገኝለት ያስባሉ፤ ወይም የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቅ ያን ያህል አስፈላጊ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። ፈረንሳይ ውስጥ ያደገው ኤርቬ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ የለሽ ወይም አምላክ መኖሩን የሚጠራጠር ሰው ባልሆንም አማኝ ግን አይደለሁም። ለእኔ ሕይወቴን ለመምራት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ትክክል የመሰለኝን ነገር ማድረግ ነው። ይህ ዓይነቱ አኗኗር ደግሞ በአምላክ ማመንን አይጠይቅም።”

ሌሎች ደግሞ በዩናይትድ ስቴትስ እንደሚኖረው እንደ ጆን ይሰማቸው ይሆናል። ጆን እንዲህ ብሏል፦ “ወላጆቼ አምላክ የለሾች ነበሩ። ወጣት ሳለሁ ከአምላክ መኖር ወይም አለመኖር ጋር በተያያዘ ይህ ነው የምለው አቋም አልነበረኝም። ይሁንና ስለዚህ ጉዳይ የማስብበት ጊዜ ነበር።”

ስለ አምላክ መኖር አስበህ ታውቃለህ? ካለስ ሕይወት ዓላማ እንዳለው ተሰምቶህ ያውቃል? ምናልባትም አምላክ ከሌለ አንዳንድ እውነታዎችን ማብራራት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ግራ ገብቶህ ይሆናል፤ ከእነዚህ እውነታዎች መካከል ሕይወት በዚህች ፕላኔት ላይ እንዲኖር ስላስቻሉት የተስተካከሉ የተፈጥሮ ኃይሎች የሚገልጹት ሳይንሳዊ መረጃዎች ወይም ሕይወት ያለው ነገር ሕይወት ከሌለው ነገር ሊመጣ እንደማይችል የሚያረጋግጡት ማስረጃዎች ይገኙበታል።—“ ማስረጃውን መርምር” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ከላይ የተጠቀሱት እውነታዎች ምን ትርጉም እንዳላቸው አስብ። እነዚህ እውነታዎች አንድ ውድ ሀብት የተቀበረበትን ቦታ እንደሚያመለክቱ ጠቋሚ ቀስቶች ናቸው። አምላክ እንዳለ የሚያሳምን ማስረጃ እንዲሁም ስለ እሱ አስተማማኝ መረጃ ካገኘህ ብዙ ጥቅሞች ታገኛለህ። ከእነዚህ ጥቅሞች መካከል አራቱን እንመልከት።

1. የሕይወትን ትርጉም ማወቅ ትችላለህ

ሕይወታችን ዓላማ ካለው ይህ የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ እንዲሁም ይህን ማወቅ በእኛ ሕይወት ላይ ምን ለውጥ እንደሚያመጣ መረዳት እንፈልጋለን። ምክንያቱም አምላክ ኖሮ እኛ ይህንን ሳንገነዘብ ብንቀር በመላው ጽንፈ ዓለም ውስጥ እጅግ በጣም መሠረታዊ የሆነውን እውነት ሳናውቅ እየኖርን ነው ማለት ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወት ሁሉ ምንጭ አምላክ እንደሆነ ይናገራል። (ራእይ 4:11) ይህን ማወቃችን ሕይወታችን ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያደርገው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደሚያስተምር እስቲ እንመልከት።

በምድር ላይ ካሉት ፍጥረታት በሙሉ የሰው ልጅ የተለየ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው አምላክ የፈጠረን በእሱ አምሳል ይኸውም የእሱን ባሕርያት ማንጸባረቅ እንድንችል አድርጎ ነው። (ዘፍጥረት 1:27) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች የአምላክ ወዳጅ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያስተምራል። (ያዕቆብ 2:23) ከፈጣሪያችን ጋር እንዲህ ዓይነቱን ዝምድና ከመመሥረት የበለጠ ሕይወታችን ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያደርግ ነገር የለም።

የአምላክ ወዳጅ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? የአምላክ ወዳጆች ሐሳባቸውን በቀጥታ ለእሱ መግለጽ ይችላሉ። እሱም እንደሚያዳምጣቸውና የሚፈልጉትን ነገር እንደሚያደርግላቸው ቃል ገብቷል። (መዝሙር 91:15) የአምላክ ወዳጆች ስንሆን እሱ በተለያዩ ጉዳዮች ረገድ ያለውን አመለካከት ማወቅ እንችላለን። ይህም በሕይወታችን ውስጥ ለሚነሱ ከባድ ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ እንድናገኝ ያስችለናል።

አምላክ ኖሮ እኛ ይህንን ሳንገነዘብ ብንቀር በመላው ጽንፈ ዓለም ውስጥ እጅግ በጣም መሠረታዊ የሆነውን እውነት ሳናውቅ እየኖርን ነው ማለት ነው

2. የአእምሮ ሰላም ታገኛለህ

ለምሳሌ፣ አንዳንዶች በአምላክ ማመን አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው ያደረገው በዓለም ዙሪያ በሰዎች ላይ የሚደርሰውን ሥቃይና መከራ መመልከታቸው ነው። ‘ሁሉን ቻይ የሆነ ፈጣሪ ክፋትና መከራ እንዲኖር የሚፈቅደው ለምንድን ነው?’ ብለው ይጠይቃሉ።

አምላክ የሰው ልጆች በመከራና በሥቃይ እንዲኖሩ ፈጽሞ ዓላማው እንዳልነበረ በመግለጽ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያጽናና መልስ ይሰጣል። የሰው ልጅ ሲፈጠር ምንም ዓይነት መከራ አልነበረም። ሞት እንኳ አምላክ ለሰው ልጆች ባለው ዓላማ ውስጥ አልነበረም። (ዘፍጥረት 2:7-9, 15-17) ይህ ለማመን የሚከብድ ሐሳብ ነው? ወይም የፈጠራ ታሪክ ነው? አይደለም። ሁሉን ማድረግ የሚችል ፈጣሪ ካለና ዋነኛ ባሕርይው ፍቅር ከሆነ ይህ ፈጣሪ የሰው ልጆች እንዲኖራቸው የሚፈልገው እንዲህ ዓይነት ሕይወት ነው ብሎ መጠበቅ ተገቢ ነው።

ታዲያ የሰው ልጅ አሁን ባለበት ሁኔታ ውስጥ ሊገኝ የቻለው እንዴት ነው? አምላክ የሰው ልጆችን ሲፈጥር የመምረጥ ነፃነት እንደሰጣቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ያለፈቃዳችን አምላክን የምንታዘዝ ሮቦቶች አይደለንም። የሰው ዘር ወላጆች የሆኑት የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት የአምላክን መመሪያ ለመጣስ መረጡ። እንዲያውም በራስ ወዳድነት ተነሳስተው በራሳቸው ለመመራት ወሰኑ። (ዘፍጥረት 3:1-6, 22-24) አሁን መከራ እየደረሰብን ያለው የእነሱ ምርጫ ባስከተለው መዘዝ የተነሳ ነው።

አምላክ፣ የሰው ልጆች ሥቃይና መከራ እንዲደርስባቸው ዓላማው እንዳልነበረ ማወቃችን ከፍተኛ የአእምሮ ሰላም ያስገኝልናል። ይሁን እንጂ ከችግር ለመገላገል መፈለጋችንም ተፈጥሯዊ ነገር ነው። የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ተስፋ ሊኖረን ይገባል።

3. ተስፋ ይኖርሃል

የሰው ልጅ በአምላክ ላይ ካመፀ በኋላ አምላክ፣ ለምድር ያወጣውን የመጀመሪያ ዓላማ እንደሚፈጽም ወዲያውኑ ተስፋ ሰጠ። ሁሉን ቻይ ስለሆነ ይህን ከማድረግ ሊያግደው የሚችል ነገር የለም። (ኢሳይያስ 55:11) አምላክ በእሱ ላይ የተነሳው ዓመፅ ያስከተላቸውን መጥፎ ውጤቶች በሙሉ በቅርቡ ያስወግዳል፤ የሰው ልጆችም ሆነ የምድር ሁኔታ አምላክ አስቀድሞ ከነበረው ዓላማ ጋር የሚስማማ ይሆናል።

ይህ ለአንተ ምን ትርጉም ይኖረዋል? አምላክ የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲመዘገቡ ካደረጋቸው ተስፋዎች መካከል እስቲ ሁለቱን እንመልከት።

  • ሰላም በመላው ምድር ላይ ይሰፍናል፤ እንዲሁም ክፋት ይወገዳል። “ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ ስፍራውንም ብታስስ አታገኘውም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።”—መዝሙር 37:10, 11

  • በሽታና ሞት ይወገዳሉ። “‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።” (ኢሳይያስ 33:24) “ሞትንም ለዘላለም ይውጣል። ጌታ እግዚአብሔር ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።”—ኢሳይያስ 25:8

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት የአምላክ ተስፋዎች መፈጸማቸው እንደማይቀር የምንተማመነው ለምንድን ነው? በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙ በርካታ ትንቢቶች በትክክል ስለተፈጸሙ ነው። እርግጥ ነው፣ ወደፊት እፎይታ እንደምናገኝ ያለን ተስፋ በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥሙንን ችግሮች አያስወግድልንም። ታዲያ አምላክ በዚህ ረገድ ምን ተጨማሪ እርዳታ ይሰጠናል?

4. ችግሮችን መፍታትና ጥሩ ውሳኔ ማድረግ ትችላለህ

አምላክ፣ ችግሮቻችንን ለመፍታት እንዲሁም ጥሩ ውሳኔዎች ለማድረግ የሚረዳ መመሪያ ይሰጠናል። ብዙ ውሳኔዎች ቀላል ናቸው፤ አንዳንዶቹ ውሳኔዎች የሚያስከትሉት ውጤት ግን ዕድሜ ልክ አብሮን የሚቆይ ሊሆን ይችላል። ፈጣሪያችን የሚሰጠንን ጥበብ የሚንጸባረቅበት መመሪያ ያህል ውጤታማ የሆነ ሰብዓዊ ጥበብ የለም። ፈጣሪ አሁን እየተከናወነ ያለውንም ሆነ ወደፊት የሚሆነውን ነገር ማወቅ ይችላል፤ እንዲሁም የሰው ልጆችን የፈጠራቸው እሱ ነው። በመሆኑም የሚበጀንን ያውቃል።

ይሖዋ አምላክ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲጽፉ በመንፈሱ መርቷቸዋል፤ በመሆኑም ይህ መጽሐፍ የይሖዋን ሐሳቦች ይዟል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲህ የሚል ሐሳብ እናገኛለን፦ “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ።”—ኢሳይያስ 48:17, 18

አምላክ ገደብ የሌለው ኃይል አለው፤ ይህንን ኃይሉን እኛን ለመርዳት ሊጠቀምበት ይፈልጋል። አምላክ እኛን ለመርዳት እንደሚፈልግ አፍቃሪ አባት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። “በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን [ይሰጣቸዋል]” በማለት ይናገራል። (ሉቃስ 11:13) ከአምላክ የሚገኘው ይህ ኃይል ይመራናል እንዲሁም ያበረታናል።

ከአምላክ እንዲህ ያለውን እርዳታ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ አምላክ የሚቀርብ ሰው እሱ መኖሩንና ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን ማመን ይኖርበታል” በማለት ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል። (ዕብራውያን 11:6) አምላክ እንዳለ በእርግጠኝነት ለማመን ማስረጃዎቹን ራስህ መመርመር ይኖርብሃል።

ማስረጃውን ለመመርመር ፈቃደኛ ነህ?

ስለ አምላክ እውነቱን ለማወቅ ምርምር ማድረግ ጊዜ የሚወስድ ነገር ቢሆንም ይህን ማድረግህ ብዙ ጥቅም ያስገኝልሃል። ቻይና ውስጥ የተወለደውና በአሁኑ ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው ሽዩጂን ሽያዎ ያጋጠመውን እንመልከት። ሽዩጂን ሽያዎ እንዲህ ብሏል፦ “በዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ አምን የነበረ ቢሆንም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ጉጉት ነበረኝ። በመሆኑም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩ። የመጨረሻ ዓመት የኮሌጅ ተማሪ ሳለሁ በጣም ሥራ ይበዛብኝ ስለነበረ መጽሐፍ ቅዱስ የማጠናበት ጊዜ አጣሁ። ይሁን እንጂ ደስታ እየራቀኝ ሄደ። ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ እንደገና ቅድሚያ መስጠት ስጀምር ግን ውስጣዊ ደስታ አገኘሁ።”

ስለ ፈጣሪያችን ስለ ይሖዋ አምላክ ተጨማሪ ትምህርት ማግኘት ትፈልጋለህ? ለምን የተወሰነ ጊዜ መድበህ ስለ እሱ ለማወቅ አትሞክርም?