በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ይጠቅማል?

ፍቅር

ፍቅር

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ፍቅርን ልበሱ፤ ምክንያቱም ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነው።”ቆላስይስ 3:14

የሚያስገኘው ጥቅም፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዛት የተጠቀሰው የፍቅር ዓይነት በወንድና በሴት መካከል የሚፈጠረው ፆታዊ ፍቅር አይደለም። ከዚህ ይልቅ እንደ ርኅራኄ፣ ይቅር ባይነት፣ ትሕትና፣ ታማኝነት፣ ደግነት፣ ገርነትና ትዕግሥት ያሉትን ባሕርያት ያካተተ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን መሠረት ያደረገ የፍቅር ዓይነት ነው። (ሚክያስ 6:8፤ ቆላስይስ 3:12, 13) ይህ ዓይነቱ ፍቅር፣ በጊዜ ብዛት እየከሰመ ከሚሄደው የወረት ፍቅር በተለየ መልኩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይሄዳል።

ብሬንዳ በትዳር ሕይወት 30 ዓመታት ገደማ አሳልፋለች፤ እንዲህ ብላለች፦ “በአዲስ ተጋቢዎች መካከል የሚኖረው ፍቅር ለረጅም ጊዜ በትዳር ዓለም በቆዩ ሰዎች መካከል ካለው ፍቅር ጋር ፈጽሞ አይወዳደርም።”

ሳም ትዳር ከመሠረተ ከ12 ዓመት በላይ ሆኖታል፤ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “እኔና ባለቤቴ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች ምን ያህል ውጤታማና ቀላል እንደሆኑ ስንመለከት ከመደሰት አልፈን በጣም የተደነቅንባቸው ጊዜያት አሉ። ምክሮቹን ተግባራዊ ካደረግህ ሁሉ ነገር ይሳካልሃል። ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ብፈልግም እንዲህ ሳላደርግ የምቀርባቸው ጊዜያት አሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሚያጋጥመኝ ከመጠን በላይ ስሜታዊ ስሆን፣ የራስ ወዳድነት ስሜት ሲያድርብኝ ወይም ስደክም ነው። እንደነዚህ ባሉት ጊዜያት መጥፎ ስሜቶችን እንዳስወግድ እንዲረዳኝ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ። በኋላም ባለቤቴን ሄጄ እቅፍ አደርጋታለሁ፤ ከዚያም የተፈጠረውን ነገር ሙሉ በሙሉ እንረሳዋለን!”

“ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በሥራዋ ተረጋግጧል”

ኢየሱስ ክርስቶስ “ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በሥራዋ ተረጋግጧል” ብሏል። (ማቴዎስ 11:19) መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ሲመዘን የእውነተኛ ጥበብ ምንጭ መሆኑን የሚያረጋግጡ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። የያዛቸው ትምህርቶችና እሴቶች ጠቃሚ ናቸው። ጊዜ አይሽራቸውም። ባሕል ወይም ብሔር የሚገድባቸው አይደሉም። የሰው ልጆችን ተፈጥሮ ግምት ውስጥ ያስገቡ በመሆናቸው የመጽሐፉ ምንጭ ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ አምላክ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። በእርግጥ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ጠቀሜታ ማየት የሚቻልበት ዋነኛው መንገድ ምክሮቹን ተግባራዊ በማድረግ ውጤቱን መመልከት ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ” በማለት ይጋብዘናል። (መዝሙር 34:8) ይህን ግብዣ ትቀበላለህ?