በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንድፍ አውጪ አለው?

ወደ ላይ የሚቀለበስ ክንፍ ያላቸው ወፎች

ወደ ላይ የሚቀለበስ ክንፍ ያላቸው ወፎች

አውሮፕላን በሚበርበት ወቅት በክንፉ ጫፍ ላይ በፍጥነት የሚሽከረከሩ የአየር አዙሪቶች ይፈጠራሉ። እነዚህ አዙሪቶች አውሮፕላኑን ወደኋላ ስለሚጎትቱት ብዙ ነዳጅ እንዲቃጠል ያደርጋሉ። በተጨማሪም አውሮፕላኑን በቅርበት የሚከተል ሌላ አውሮፕላን ካለ እንቅስቃሴው ይዛባል። በመሆኑም አንድ አውሮፕላን፣ ከእሱ በፊት የተነሳው አውሮፕላን የፈጠራቸው የአየር አዙሪቶች እስኪጠፉ ድረስ የግድ መጠበቅ ይኖርበታል።

የአውሮፕላን መሐንዲሶች ይህን ችግር ለመቀነስ የሚያስችል መንገድ አግኝተዋል። ይህም እንደ ገዴ፣ ንስር እና ራዛ ያሉ ወደ ላይ የሚቀለበስ ክንፍ ያላቸው ወፎችን በመመልከት ተመሳሳይ ቅርፅ ያለው የአውሮፕላን ክንፍ መሥራት ነው።

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ እነዚህ ትላልቅ ወፎች በሚበርሩበት ወቅት በክንፎቻቸው ጫፍ ላይ ያሉት ላባዎች ወደ ላይ ይቀለበሳሉ። ይህም አነስ ካለው የክንፋቸው ርዝመት አንጻር ሲታይ ከፍተኛ የሆነ ወደ ላይ የሚገፋ ኃይል እንዲኖራቸው ያደርጋል። በመሆኑም ወፎቹ በተሻለ ቅልጥፍና መብረር ይችላሉ። መሐንዲሶች ከወፎቹ ክንፍ ጋር የሚመሳሰል ቅርጽ ያለው የአውሮፕላን ክንፍ ሠርተዋል። ለጊዜው በጣም ዘመናዊ የነበረውን የመፈተሻ ዘዴ ተጠቅመው ባደረጉት ፍተሻ፣ የአውሮፕላኑ ክንፍ ጫፉ በትክክል የተቀለበሰ እንዲሁም ከአየሩ ግፊት ጋር በሚጣጣም መንገድ የተሠራ ከሆነ የአውሮፕላኑ የመብረር ብቃት ይበልጥ እንደሚጨምር አስተውለው ነበር፤ ይህ የፈጠራ ውጤት በአሁኑ ጊዜ የአውሮፕላኖቹ ቅልጥፍና 10 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ እንዲጨምር አድርጓል። ምክንያቱም ጫፋቸው ወደ ላይ የተቀለበሱ ክንፎች የአየር አዙሪቶቹ መጠን እንዲቀንስ ያደርጋሉ። ከዚህም በተጨማሪ “አውሮፕላኑን ወደ ኋላ የሚጎትተውን ማንኛውንም ዓይነት ግፊት የሚቋቋም” ኃይል እንዲፈጠር እንደሚያደርጉ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ፍላይት ተናግሯል።

ጫፋቸው ወደ ላይ የተቀለበሱ ክንፎች ያሏቸው አውሮፕላኖች ረዘም ያለ ርቀት መብረርና ከበፊቱ የበለጠ ጭነት መሸከም የሚችሉ ከመሆኑም ሌላ ነዳጅ ቆጣቢ ናቸው፤ በተጨማሪም ክንፋቸው አጠር ያለ ስለሆነ በሚቆሙበት ጊዜ ብዙ ቦታ አይይዙም። ለምሳሌ ያህል፣ ናሳ ያወጣው የዜና ዘገባ እንደገለጸው እንዲህ ያሉት አውሮፕላኖች በ2010 “በዓለም አቀፍ ደረጃ [7,600 ሚሊዮን ሊትር] የሚሆን ነዳጅ እንዳይባክን” አድርገዋል፤ ይህ ደግሞ ከአውሮፕላኖቹ የሚወጣው በካይ ጭስ እንዲቀንስ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? ወደ ላይ የተቀለበሰ ክንፍ ያላቸው ወፎች የተገኙት በዝግመተ ለውጥ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አላቸው?