በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጥበብ ጥበቃ ያስገኛል

ጥበብ ጥበቃ ያስገኛል

“የሰው ሀብቱ ለሕይወቱ ቤዛ ሊሆነው ይችላል፤ ድኻው ግን ሥጋት የለበትም።” —ምሳሌ 13:8

ሀብታም መሆን አንዳንድ ጥቅሞች ያሉት ቢሆንም በተለይ በዚህ አስጨናቂ ዘመን ለጉዳት ሊያጋልጥ ይችላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በአንዳንድ አገሮች ባለጸጋ የሚመስሉ ቱሪስቶችን ጨምሮ ሀብታም የሆኑ ሰዎች የሌቦችና የአጋቾች ዒላማ ሆነዋል።

አንድ የዜና ዘገባ በማደግ ላይ ያለን አንድ አገር አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ዝርፊያ፣ ማታለልና የአጋቾች ጥቃት ሀብታሞችና ድሆች በጥላቻ ዓይን እንዲተያዩ አድርገዋል። ምግብ ቤቶች የታጠቁ ዘበኞችን ያቆማሉ፤ ባለጸጎች ቤቶቻቸውን በአደገኛ አጥር ያጥራሉ፤ ባውዛ መብራቶችንና ካሜራዎችን ይተክላሉ፤ እንዲሁም የጥበቃ ሠራተኞችን ይቀጥራሉ።” በሌሎች ብዙ አገሮችም ተመሳሳይ ሁኔታ ይታያል።

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ድኻ . . . ሥጋት የለበትም” በማለት ይናገራል። ከዚህ ጥበብ የሚንጸባረቅበት አባባል ምን ትምህርት እናገኛለን? ወንጀልና ዓመፅ በሚበዛበት አካባቢ የምትኖር ወይም እንዲህ ወዳለው አካባቢ የምትጓዝ ከሆነ ሀብታም መስለህ በመታየት ትኩረት አትሳብ። ስለምትለብሰው ልብስና ስለምትይዘው ዕቃ ማሰብ ይኖርብሃል፤ በተለይ ደግሞ የምትይዘው ዕቃ ዓይን ውስጥ የሚገባ ከሆነ ጥንቃቄ አድርግ። ምሳሌ 22:3 “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል፤ ብስለት የጐደለው ግን በዚያው ይቀጥላል፤ መከራም ያገኘዋል” ይላል።

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ጥበብ ያዘሉ ሐሳቦች እንደሚያሳዩት ፈጣሪያችን ያስብልናል። እንዲሁም ጉዳት እንዲደርስብን አይፈልግም። መክብብ 7:12 እንዲህ ያለው ጥበብ “ጥላ ከለላ” እንደሆነ ይናገራል፤ ምክንያቱም ‘የባለቤቱን ሕይወት ይጠብቃል።’