በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ከዓለም አካባቢ

የዜናው ትኩረት—ጤና

የዜናው ትኩረት—ጤና

በሕክምናው መስክ ትልቅ እመርታ እየታየ ቢሆንም የሰው ልጆች በተለያዩ በሽታዎች እያለቁ ነው። ይሁን እንጂ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ብዙዎቹን የጤና ችግሮች መከላከል ይቻላል።

ዓለም

የዓለም የጤና ድርጅት እንደገመተው በ2035 በዓመት 24 ሚሊዮን ሰዎች በካንሰር ይያዛሉ። ይህ አኃዝ በአሁኑ ጊዜ በየዓመቱ በበሽታው እንደሚያዙ የሚገመቱትን ሰዎች ብዛት 70 በመቶ ያሳድገዋል፤ በአሁኑ ጊዜ በየዓመቱ ከ14 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በካንሰር እንደሚያዙ ይታሰባል። ከእነዚህ መካከል ግማሽ ገደማ የሚሆኑት በበሽታው እንዲያዙ መንስኤ የሚሆኑት ከመጠን በላይ የአልኮል መጠጦችን መውሰድ፣ እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ለጨረራ መጋለጥና ማጨስ ናቸው።

ብሪታንያ

ሰዎችን ሊያጠቃ የሚችለው የእብድ ላም በሽታ፣ ደም እንደ መውሰድ ባሉ የሕክምና ሂደቶች ሊተላለፍ እንደሚችል የሚያሳይ ማስረጃ ከቀረበ በኋላ የብሪታንያ መንግሥት ሁኔታው በደንብ እንዲጣራ ትእዛዝ አስተላልፏል። የፓርላማ አባል የሆኑት አንድሩ ሚለር “ይህ መድኃኒት የሌለው በሽታ አሁንም የማኅበረሰቡን ጤና ስጋት ላይ እንደጣለው የሚጠቁም መረጃ ማግኘታችን በጣም አሳስቦናል” ብለዋል። አክለውም “በሽታው ሊሰራጭ የሚችለው የተበከለ ደም ወይም የሰውነት ክፍል [ለሕመምተኞች] በሚሰጥበት ወቅት እንደሆነ ሰምተናል” በማለት ተናግረዋል።

ኖርዌይ

ወደ 63,000 ገደማ በሚሆኑ የኖርዌይ ነዋሪዎች ላይ የተደረገ 11 ዓመት የፈጀ አንድ ጥናት እንዳመለከተው የመንፈስ ጭንቀት በልብ በሽታ የመያዝን አጋጣሚ እስከ 40 በመቶ ድረስ ሊጨምር ይችላል። የአውሮፓ የልብ ሕክምና ማኅበር ከጥናቱ አዘጋጆች መካከል አንዷን ጠቅሶ እንደተናገረው ከሆነ የመንፈስ ጭንቀት በውጥረት ጊዜ የሚመነጩ ሆርሞኖች በብዛት እንዲመረቱ የሚያደርግ ሲሆን ይህም ለልብ በሽታ ሊዳርግ ይችላል፤ ከዚህም በተጨማሪ ግለሰቡ የሚሰጡትን ጤንነቱን ለማሻሻል የሚረዱ ምክሮች ተግባራዊ ለማድረግ ያለውን ተነሳሽነት ያዳክምበታል።

ዩናይትድ ስቴትስ

የሳይንስ ሊቃውንት ሲጋራ ማጨስ በወቅቱ በቦታው ባልነበሩ ሰዎች ላይም እንኳ ሊያስከትል የሚችለውን የጤና ጉዳት በመመርመር ላይ ናቸው፤ ከሲጋራ የሚወጡት ኬሚካሎች በመኖሪያ ቤቶች፣ በሆቴል ክፍሎችና በተሽከርካሪዎች ውስጥ ባሉ የተለያዩ ቁሳቁሶች እንዲሁም አየሩ ላይ ሊቀሩ ይችላሉ። የተከማቹት ኬሚካሎች ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ይበልጥ መርዛማ ይሆናሉ።