በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቃለ ምልልስ | አንቶንዮ ዴላ ጋታ

አንድ ቄስ ይከተለው የነበረውን ሃይማኖት የተወው ለምንድን ነው?

አንድ ቄስ ይከተለው የነበረውን ሃይማኖት የተወው ለምንድን ነው?

አንቶንዮ ዴላ ጋታ በሮም ውስጥ የዘጠኝ ዓመት ትምህርት ከተከታተለ በኋላ በ1969 የቅስና ማዕረግ አገኘ። በኋላም ጣሊያን ውስጥ በምትገኘው በኔፕልስ አቅራቢያ ባለ አንድ የሃይማኖት ትምህርት ቤት ውስጥ ኃላፊ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። እዚያ እያለም ብዙ ጥናት ካደረገና ካሰላሰለ በኋላ የካቶሊክ ሃይማኖት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነ እርግጠኛ ሆነ። ይህ ሰው አምላክን ለማወቅ ስላደረገው ፍለጋ ለንቁ! መጽሔት ተናግሯል።

እስቲ ስለ ልጅነት ሕይወትህ ንገረን።

የተወለድኩት ጣሊያን ውስጥ በ1943 ነው። ያደግኩት ከወንድሞቼና እህቶቼ ጋር በአንዲት ትንሽ መንደር ውስጥ ነው፤ አባቴ ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው በግብርናና በአናጺነት ሙያ ነበር። ወላጆቻችን ያሳደጉን ጥሩ ካቶሊኮች እንድንሆን አድርገው ነው።

ቄስ ለመሆን የፈለግከው ለምን ነበር?

በልጅነቴ ቄሶች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲሰብኩ መስማት ያስደስተኝ ነበር። የቄሶቹ ቅዳሴ እንዲሁም በዚያ የሚከናወነው የአምልኮ ሥርዓት ይማርከኝ ነበር። በመሆኑም ቄስ የመሆን ከፍተኛ ፍላጎት አደረብኝ። አሥራ ሦስት ዓመት ሲሞላኝ እናቴ ወንዶች ልጆችን ለቅስና ወደሚያዘጋጅ አንድ አዳሪ ትምህርት ቤት አስገባችኝ።

በዚያ የሚሰጣችሁ ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትን ያካትት ነበር?

አልነበረም። ዕድሜዬ 15 ዓመት ሲሆን ከአስተማሪዎቼ አንዱ የኢየሱስን ሕይወትና አገልግሎት የሚተርኩትን የወንጌል ዘገባዎች የያዘ መጽሐፍ ሰጠኝ፤ እኔም መጽሐፉን ደጋግሜ አነበብኩት። በ18 ዓመቴ ወደ ሮም ሄጄ በሊቀ ጳጳሳቱ በቀጥታ በሚተዳደሩ የጵጵስና ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መማር ጀመርኩ። በዚያም የላቲን፣ የግሪክኛ፣ የታሪክ፣ የፍልስፍና፣ የሥነ ልቦናና የሥነ መለኮት ትምህርት ተማርኩ። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቃል ከማነብነብና እሁድ እሁድ በሚደረጉ ስብከቶች ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ሲነበብ ከማዳመጥ ውጭ መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተን አናውቅም።

በኋላም የሃይማኖት ትምህርት ቤት ኃላፊ ሆንክ። ይህ ሥራ ማስተማርን ይጨምር ነበር?

ሥራዬ በአብዛኛው ከአስተዳደር ጋር የተያያዘ ነበር። ያም ቢሆን ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ስላስተላለፋቸው ድንጋጌዎች አስተምር ነበር።

በሃይማኖትህ ላይ ጥርጣሬ ያደረብህ ለምንድን ነው?

ሦስት ነገሮች ይረብሹኝ ነበር። ቤተ ክርስቲያን በፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ ትገባ ነበር። ካህናትና ምዕመናን የሚፈጽሙት የሥነ ምግባር ጉድለት በቸልታ ይታለፋል። በተጨማሪም አንዳንድ የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ትክክል እንደሆኑ አልተሰማኝም። ለምሳሌ ያህል፣ ‘አፍቃሪ የሆነው አምላክ ከሞት በኋላ ሰዎችን እንዴት ለዘላለም ይቀጣቸዋል? በተጨማሪም አምላክ መቁጠሪያ በመጠቀም በመቶዎች ለሚቆጠሩ ጊዜያት አንድን ጸሎት እንድንደጋግም ይፈልጋል?’ እያልኩ አስብ ነበር። *

ታዲያ ምን አደረግክ?

አምላክ መመሪያ እንዲሰጠኝ እያለቀስኩ ጸለይኩ። በተጨማሪም በወቅቱ በጣሊያንኛ የታተመውን ጀሩሳሌም ባይብል የተባለውን የካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስ ገዝቼ ማንበብ ጀመርኩ። ከዚያም አንድ እሁድ ቀን ጠዋት ከቅዳሴ ወጥቼ የክህነት ልብሴን እየሰቀልኩ ሳለ ሁለት ወንዶች ወደ ሃይማኖት ትምህርት ቤቱ መጡ። ሰዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ ነገሩኝ። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ የእውነተኛ ሃይማኖት መለያ እንደሆኑ ስለሚናገራቸው ምልክቶች ከአንድ ሰዓት በላይ ተወያየን።

ስለእነዚህሰዎችምንተሰምቶህነበር?

እምነታቸውን በሙሉ ልብ እንደሚናገሩ እንዲሁም ጥቅሶችን ካቶሊኮች ካሳተሙት መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በቀላሉ እንደሚያወጡ ስመለከት ተደነቅኩ። በኋላም ማርዮ ከሚባል የይሖዋ ምሥክር ጋር መወያየት ጀመርኩ። ማርዮ ትዕግሥተኛና ከቃሉ ዝንፍ የማይል ሰው ነበር፤ ዝናብ ፀሐይ ሳይል ሁልጊዜ ቅዳሜ ጠዋት በ3 ሰዓት ላይ ወደ ትምህርት ቤቱ ይመጣ ነበር።

ሌሎቹ ቀሳውስት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስትወያይ ሲመለከቱ ምን ተሰማቸው?

በውይይታችን እንዲካፈሉ ጋብዣቸው ነበር፤ ይሁን እንጂ አንዳቸውም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ አልገፉም። እኔ ግን ውይይቱ በጣም ያስደስተኝ ነበር። ብዙ አስደናቂ ነገሮችን ተማርኩ፤ ለምሳሌ ያህል፣ ለረጅም ጊዜ ሲያሳስበኝ ለቆየው ‘አምላክ ክፋትና መከራ እንዲኖር ለምን ፈቀደ?’ ለሚለው ጥያቄ መልስ አገኘሁ።

የበላዮችህ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትህን እንድታቆም ለማድረግ አልሞከሩም?

አመለካከቴን ለማስረዳት በ1975 ብዙ ጊዜ ወደ ሮም ሄጄ ነበር። የበላዮቼ አስተሳሰቤን እንድለውጥ ለማድረግ ሞክረዋል፤ ግን አንዳቸውም ቢሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ አልተጠቀሙም። በመጨረሻም ጥር 9 ቀን 1976፣ ከዚያ በኋላ ካቶሊክ እንዳልሆንኩ የሚገልጽ ደብዳቤ ወደ ሮም ላክሁ። ከሁለት ቀን በኋላ ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቱን ለቅቄ ወጣሁ፤ ከዚያም ለመጀመሪያ ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ለመገኘት ባቡር ተሳፈርኩ፤ ይህ ስብሰባ በርካታ ጉባኤዎች የሚሰበሰቡበት ትልቅ ስብሰባ ነበር። በስብሰባው ላይ ያየሁት ነገር እኔ ከማውቀው ፈጽሞ የተለየ ነበር! ተናጋሪዎቹ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተመሠረቱ ንግግሮችን ሲያቀርቡ ተሰብሳቢዎቹ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን እያወጡ ይከታተሉ ነበር።

ቤተሰቦችህ ሁኔታውን ሲያውቁ ምን ተሰማቸው?

አብዛኞቹ አምርረው ተቃወሙኝ። ይሁን እንጂ በሰሜናዊ ጣሊያን በሚገኘው በሎምባርዲ የሚኖረው ወንድሜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እያጠና እንደሆነ አወቅኩ። እኔም እሱን ለመጠየቅ ሄድኩ፤ ከዚያም በአካባቢው የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራና መኖሪያ እንዳገኝ ረዱኝ። በዚያው ዓመት መጨረሻ አካባቢ ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።

አሁን ከአምላክ ጋር በጣም እንደተቀራረብኩ ይሰማኛል

የሚቆጭህ ነገር አለ?

በፍጹም! አሁን ከአምላክ ጋር በጣም እንደተቀራረብኩ ይሰማኛል፤ ምክንያቱም ስለ አምላክ የማውቀው ሁሉ የተመሠረተው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንጂ በፍልስፍና ወይም በቤተ ክርስቲያን ትውፊት ላይ አይደለም። በተጨማሪም ሌሎችን በእርግጠኝነትና ከልብ በመነጨ ስሜት ማስተማር ችያለሁ።

^ አን.13 መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህና ለሌሎች በርካታ ጥያቄዎች ግልጽ መልስ ይሰጣል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው በሚለው ሥር ተመልከት።