በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ይጠቅማል?

መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ይጠቅማል?

“በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ እውነተኛ ደስታ አገኘሁ።”

ሂልተን የቦክስ ስፖርት ይወድ ነበር። ገና በሰባት ዓመቱ በቦክስ ውድድር ላይም ሆነ በሌሎች ጊዜያት ከሰዎች ጋር መደባደብ ጀመረ! ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲገባ የሚደበድበው ሰው ለመፈለግ ከጓደኞቹ ጋር ይዞር ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “እሰርቅ፣ ቁማር እጫወት፣ ፖርኖግራፊ እመለከት፣ ሴቶችን አስቸግር እንዲሁም ወላጆቼን እሳደብ ነበር። በጣም መጥፎ ጠባይ ስለነበረኝ ወላጆቼ ፈጽሞ ልሻሻል እንደማልችል ያስቡ ነበር። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንደጨረስኩ ከቤት ወጣሁ።”

ሂልተን ከ12 ዓመት በኋላ ወደ ቤቱ ሲመለስ ወላጆቹ ልጃቸው መሆኑን ማመን አቃታቸው። ሂልተን ረጋ ያለ፣ ራሱን የሚገዛና ሰው አክባሪ ሆኖ ነበር። እንዲህ ያለ አስደናቂ ለውጥ እንዲያደርግ የረዳው ምንድን ነው? ከቤት ወጥቶ በነበረበት ጊዜ ሕይወቱ ወዴት እያመራ እንዳለ በጥሞና ማሰብ ጀመረ። ሕይወቱን ለማሻሻል እንደሚረዳው በማሰብም መጽሐፍ ቅዱስን መረመረ። ሂልተን እንዲህ ብሏል፦ “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የማነብበውን ነገር ተግባራዊ ማድረግ ጀመርኩ፤ ይህ ደግሞ የቀድሞ ጠባዬን ማስወገድንና በኤፌሶን 6:2, 3 ላይ የሚገኘውን ወላጆቼን ማክበር እንዳለብኝ የሚገልጸውን መመሪያ መታዘዝን ይጠይቅብኝ ነበር። በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ እውነተኛ ደስታ አገኘሁ፤ ለአባቴና ለእናቴም ምሬትና ሐዘን ሳይሆን ደስታ የማመጣ ልጅ ሆንኩ።”

የሂልተን ታሪክ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት የሥነ ምግባር እሴቶች በዛሬው ጊዜም ጠቃሚ እንደሆኑ እንዲሁም የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል እንዳላቸው ያሳያል። (ዕብራውያን 4:12) እንደ ሐቀኝነት፣ ራስን መግዛት፣ ታማኝነትና ፍቅር ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ እሴቶች የሰዎች ሕይወት እንዲሻሻል ያደረጉት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።