በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ይጠቅማል?

ሐቀኝነት

ሐቀኝነት

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፤ በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? . . . አካሄዱ ንጹሕ የሆነ፣ ጽድቅን የሚያደርግ፤ ከልቡ እውነትን የሚናገር።”መዝሙር 15:1, 2

የሚያስገኘው ጥቅም፦ አብዛኞቹ ሰዎች ለሐቀኝነት ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት መፈጸሙ ጥቅም የሚያስገኝለት ቢሆንና ሐቀኝነት ማጉደሉን ማንም ሰው እንደማያውቅበት ቢሰማው ምን ያደርጋል? በዚህ ጊዜ የሚወስደው እርምጃ ውስጣዊ ማንነቱን ማለትም በልቡ ውስጥ ያለውን ነገር በግልጽ ያሳያል።

ራኬል ሥራዋ ከዕቃ ግዢ ጋር የተያያዘ ሲሆን እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ የሽያጭ ወኪሎች ጉቦ እንስጥሽ ይሉኝ ነበር። ከእነሱ ዕቃ ከገዛሁ የተወሰነ ገንዘብ በድብቅ እንደሚሰጡኝ ቃል ይገቡ ነበር። እኔ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሐቀኝነት የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ስለፈለግኩ እምቢ አልኳቸው። አለቃዬ ይህን ስትሰማ በእኔ ላይ ያላት እምነት ጨመረ።”

ራኬል በቀረበላት ጥያቄ ተታልላ ቢሆን ኖሮ ለጊዜውም ቢሆን የገንዘብ ጥቅም ታገኝ ነበር። ይሁን እንጂ አሠሪዋ ሁኔታውን ብታውቅስ? ራኬል ከሥራዋ ልትባረር ትችል ነበር። ወደፊት ሥራ የማግኘት አጋጣሚዋ ደግሞ ሊቀንስ ይችላል። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ራኬል ሕሊናዋን ማቆሸሽ እንዲሁም ለራስዋ ያላትን አክብሮት ማጣት አልፈለገችም። ምሳሌ 22:1 “መልካም ስም ከብዙ ብልጽግና ይመረጣል፤ መከበርም ከብርና ከወርቅ ይበልጣል” ይላል።

ጄሲ ሐቀኛ ሠራተኛ በመሆኑ ጥሩ ስም አትርፏል

ጄሲ ሐቀኛና እምነት የሚጣልበት ሰው በመሆኑ በአሠሪው ዘንድ ጥሩ ስም አትርፏል። ይህስ ምን ጥቅም አስገኘለት? የኃላፊነት ቦታ የተሰጠው ከመሆኑም በላይ ከሥራ ሰዓቱ ጋር በተያያዘ የበለጠ ነፃነት አለው። በመሆኑም ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር ተጨማሪ ጊዜ ማሳለፍ እንዲሁም መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን ሰፋ ያለ ጊዜ ማግኘት ችሏል።

አንዳንድ አሠሪዎች ሠራተኛ በሚቀጥሩበት ጊዜ በሐቀኝነታቸው የሚታወቁ አባሎች ያሏቸውን ድርጅቶች የጠየቁበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ በፊሊፒንስ የሚገኝ የአንድ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ በአገሩ ላለው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ደብዳቤ በመጻፍ የይሖዋ ምሥክሮች ወደዚህ ኩባንያ የሥራ ማመልከቻ እንዲያስገቡ ግብዣ አቅርቦ ነበር። ይህ ሰው የይሖዋ ምሥክሮች “ጠንካራ ሠራተኞች፣ ሐቀኞችና ታታሪዎች” እንደሆኑ ገልጿል። እርግጥ ነው፣ ለዚህ ሁሉ ሊመሰገን የሚገባው ‘ክፉውን እንድንጠላና መልካሙን እንድንወድ’ የሚያስተምረን ይሖዋ አምላክ ነው።—አሞጽ 5:15