በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መከራ

መከራ

አንዳንዶች፣ በሰዎች ላይ መከራ የሚያመጣው አምላክ እንደሆነ ይሰማቸዋል፤ ይህ ባይሆን እንኳ አምላክ በሰዎች ላይ ለሚደርሰው መከራ ግድ እንደሌለው ያስባሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ ያስተምራል? የዚህ ጥያቄ መልስ ያስገርምህ ይሆናል።

መከራ የሚያመጣብን አምላክ ነው?

“በእውነት እግዚአብሔር ክፋትን አይሠራም።”ኢዮብ 34:12

ሰዎች ምን ይላሉ?

አንዳንዶች፣ ሁሉም ነገር የሚፈጸመው በአምላክ ፈቃድ እንደሆነ ይናገራሉ። በመሆኑም መከራ የሚያመጣብን አምላክ እንደሆነ ያምናሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የተፈጥሮ አደጋ አምላክ ኃጢአት የሠሩ ሰዎችን የሚቀጣበት መንገድ እንደሆነ ያስባሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ መከራ የሚያመጣብን አምላክ እንዳልሆነ በግልጽ ያስተምራል። ለምሳሌ፣ አስቸጋሪ ሁኔታ ሲገጥመን “አምላክ እየፈተነኝ ነው” ብሎ መናገር ስህተት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ለምን? ምክንያቱም “አምላክ በክፉ ነገሮች ሊፈተን አይችልም፤ እሱ ራሱም ማንንም አይፈትንም።” (ያዕቆብ 1:13) በሌላ አነጋገር፣ አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲደርስብንም ሆነ በዚያ ምክንያት እንድንሠቃይ የሚያደርገን አምላክ አይደለም። እንዲህ ማድረግ ክፋት ነው፤ አምላክ ደግሞ “ክፋትን አይሠራም።”—ኢዮብ 34:12

መከራ የሚያመጣብን አምላክ እንዳልሆነ ተመልክተናል፤ ታዲያ ለሚደርስብን መከራ መንስኤው ማን ወይም ምንድን ነው? የሚያሳዝነው፣ ብዙ ሰዎች መከራ የሚደርስባቸው ፍጹም ባልሆኑ ሌሎች ሰዎች ምክንያት ነው። (መክብብ 8:9) በተጨማሪም ‘ባልተጠበቁ ክስተቶች’ የተነሳ ማለትም በአጉል ሰዓት ላይ አጉል ቦታ በመገኘታችን ምክንያት መከራ ሊደርስብን ይችላል። (መክብብ 9:11 NW) መጽሐፍ ቅዱስ ‘መላው ዓለም በክፉው ኃይል ሥር’ እንደሆነ ያስተምራል፤ በመሆኑም በሰዎች ላይ ለሚደርሰው መከራ በዋነኝነት ተጠያቂው “የዚህ ዓለም ገዥ” የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። (ዮሐንስ 12:31፤ 1 ዮሐንስ 5:19) በሰዎች ላይ መከራ የሚያመጣው አምላክ ሳይሆን ሰይጣን ነው።

አምላክ መከራ ሲደርስብን ያዝንልናል?

“በጭንቃቸው ሁሉ ተጨነቀ።”ኢሳይያስ 63:9

ሰዎች ምን ይላሉ?

አምላክ በእኛ ላይ የሚደርሰው መከራ ግድ እንደማይሰጠው የሚያስቡ ሰዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ ጸሐፊ፣ አምላክ ‘መከራ ሲደርስብን እንደማይራራልን ወይም እንደማያዝንልን ሁኔታዎች በግልጽ ያሳያሉ’ በማለት ጽፏል። አምላክ አለ ቢባል እንኳ ለሰዎች “ምንም ርኅራኄ የሌለውና ግዴለሽ” አካል እንደሆነ ጸሐፊው ገልጿል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ርኅራኄ እንደሌለው ወይም ግዴለሽ እንደሆነ አይናገርም፤ እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው አምላክ መከራ ሲደርስብን በጣም እንደሚያዝንና በቅርቡም መከራን እንደሚያስወግድ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ሦስት አጽናኝ እውነቶችን ተመልከት።

አምላክ የሚደርስብንን መከራ ያውቃል። ንቁ የሆኑት የይሖዋ * ‘ዓይኖች’ ሁሉንም ነገር ይመለከታሉ፤ በመሆኑም በሰው ልጆች ላይ መከራ መድረስ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ከእሱ እይታ የተሰወረ አንድም የእንባ ጠብታ የለም። (መዝሙር 11:4፤ 56:8) ለምሳሌ፣ በጥንት ዘመን የነበሩት የይሖዋ አምላኪዎች ጭቆና በደረሰባቸው ወቅት አምላክ “የሕዝቤን መከራ በእርግጥ አይቻለሁ” ብሎ ነበር። ይሁንና አምላክ መከራቸውን በደንብ ተመልክቶት ነበር? አዎ፣ ምክንያቱም “እየደረሰባቸው ያለውንም ሥቃይ በሚገባ አውቃለሁ” ብሏል። (ዘፀአት 3:7 NW) የሚደርስብንን መከራ ሰዎች ባያውቁልንም እንኳ አምላክ እንደሚረዳልን ማወቃቸው በራሱ ብዙዎችን አጽናንቷቸዋል።—መዝሙር 31:7፤ ምሳሌ 14:10

አምላክ ሥቃያችን ይሰማዋል። ይሖዋ አምላክ በሰዎች ላይ የሚደርሰውን መከራ ከማወቅ ባለፈ ልቡ በጣም ያዝናል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ የጥንት አገልጋዮቹ መከራ በደረሰባቸው ጊዜ ስሜቱ ተረብሾ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “በጭንቃቸው ሁሉ ተጨነቀ” ይላል። (ኢሳይያስ 63:9) አምላክ ከሰዎች በእጅጉ ቢበልጥም ራሱን በእነሱ ቦታ ስለሚያደርግ ሥቃያቸው በጥልቅ ይሰማዋል! በእርግጥም “ይሖዋ ከአንጀት የሚራራና መሐሪ” አምላክ ነው። (ያዕቆብ 5:11) በተጨማሪም ይሖዋ የሚደርስብንን መከራ መቋቋም እንድንችል ይረዳናል።—ፊልጵስዩስ 4:12, 13

አምላክ በሰዎች ላይ የሚደርሰውን መከራ በሙሉ ያስወግዳል። አምላክ የእያንዳንዱን ሰው መከራ እንደሚያስወግድ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ይሖዋ በሰማይ ባቋቋመው መንግሥቱ አማካኝነት የሰው ልጆች ያሉበትን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ያስተካክላል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጊዜ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።” (ራእይ 21:4) የሞቱ ሰዎችስ ምን ተስፋ አላቸው? አምላክ ከሞት ያስነሳቸዋል፤ ከዚያም እዚሁ ምድር ላይ መከራ የሌለበት ሕይወት ይኖራሉ። (ዮሐንስ 5:28, 29) የደረሰበት መከራ በፈጠረበት መጥፎ ትዝታ የተነሳ የሚሠቃይ ሰው ይኖራል? አይኖርም፣ ምክንያቱም ይሖዋ “ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም፤ አይታወሱም” በማለት ቃል ገብቷል።—ኢሳይያስ 65:17 *

^ አን.13 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ ስም ይሖዋ ነው።