በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ቃለ ምልልስ | ስቲቨን ቴይለር

የፋይናንስ ፕሮፌሰር ስለሚያምንበት ነገር ምን ይላል?

የፋይናንስ ፕሮፌሰር ስለሚያምንበት ነገር ምን ይላል?

ፕሮፌሰር ስቲቨን ቴይለር የሚያስተምረውና ምርምር የሚያደርገው ሲድኒ፣ አውስትራሊያ ውስጥ በሚገኘው የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው። የአክሲዮን ገበያዎች ስለሚሠሩበትና በእነዚህ ገበያዎች ውስጥ የሚደረገውን ግብይት መቆጣጠር ስለሚቻልበት መንገድ ያጠናል። የምርምር ሥራው በእምነቱ ላይ ተጽዕኖ ያሳደረው እንዴት እንደሆነ ንቁ! ጠይቆታል።

እስቲ ስለ አስተዳደግህ ንገረን።

ወላጆቼ ቤተ ክርስቲያን የሚያዘወትሩ እንዲሁም ሐቀኛና ታታሪ ሠራተኞች ናቸው። እንድማር ያበረታቱኝ ስለነበር በኒው ሳውዝ ዌልስ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ሥራ ተማርኩ። ምርምር ማካሄድ እንደምወድ ስለተገነዘብኩ በቀለም ትምህርት ላይ ለማተኮር ወሰንኩ።

የተሰማራህበት የምርምር መስክ ምን ነበር?

የአክሲዮን ገበያዎችን አሠራር የማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ። * የአክሲዮን ገበያዎች፣ የአንድን ኩባንያ አክሲዮኖች መግዛትና መሸጥ ያስችላሉ፤ ሰዎች ከሽያጩ በተገኘው ገንዘብ ተጠቅመው ንግዳቸውን ያካሂዳሉ። በአክሲዮን ዋጋ ላይ ተጽዕኖ በሚያሳድሩ ምክንያቶች እንዲሁም ከዚህ ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ሌሎች ነገሮች ላይ ምርምር አደርጋለሁ።

አንድ ምሳሌ ልትሰጠን ትችላለህ?

ኩባንያዎች በየጊዜው ገቢያቸውን እንዲያሳውቁ ይጠበቅባቸዋል። ባለሀብቶች የአንድን ኩባንያ ትርፋማነት ለመመዘን እነዚህን መረጃዎች ግምት ውስጥ ያስገባሉ። ይሁንና ኩባንያዎች ገቢያቸውን የሚያሳውቁት ወጥ የሆነ መንገድ ተከትለው አይደለም። በመሆኑም አንዳንድ የሒሳብ ባለሙያዎች ይህ ሁኔታ ኩባንያዎች እውነተኛ ዋጋቸውንና ትርፋማነታቸውን እንዲደብቁ የሚያስችል ክፍተት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ታዲያ ባለሀብቶች ትክክለኛና የተሟላ መረጃ ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው? ደግሞስ ተቆጣጣሪዎች፣ የአክሲዮን ገበያዎች በትክክል እንደሚሠሩ ለማረጋገጥ ምን መረጃ ያስፈልጋቸዋል? እኔና የሥራ ባልደረቦቼ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ጥረት እያደረግን ነው።

 ቀደም ሲል ሃይማኖትህ ምን ነበር?

ከወላጆቼ ጋር አዘውትሬ ወደ ፕሪስባይቴሪያን ቤተ ክርስቲያን እሄድ ነበር፤ ወደ አሥራዎቹ ዕድሜ ስገባ ግን ሃይማኖተኛ አልነበርኩም። በፈጣሪ አምናለሁ፤ እንዲሁም ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት አለኝ፤ ሆኖም ሃይማኖት ለሰው ልጆች ችግር ምንም የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ይሰማኝ ነበር። ሃይማኖቶች ለእኔ፣ ሰዎችን የሚያሰባስቡ ማኅበሮች ከመሆን ያለፈ ትርጉም አልነበራቸውም። አውሮፓ ውስጥ ያሉ በርካታ ትላልቅ አብያተ ክርስቲያናትን ጎብኝቻለሁ፤ ዓለም በድህነት እየማቀቀ፣ እነሱ ግን ይህን ያህል ብዙ ሀብት ያላቸው መሆኑ ያስገርመኝ ነበር። ይህን ሁኔታ መቀበል በጣም ስለከበደኝ የሃይማኖት ድርጅቶችን መጠራጠር ጀመርኩ።

አመለካከትህን እንድትለውጥ ያደረገህ ምንድን ነው?

ባለቤቴ ጄኒፈር ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና ስብሰባዎቻቸው ላይ መገኘት ጀመረች፤ ስለዚህ እኔም ከእሷ ጋር በመሄድ በዚያ የሚከናወነውን ነገር ለመመልከት አሰብኩ። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም ነገር እንደማላውቅ ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደብኝም። ይህም በጣም አስገረመኝ! በመሆኑም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ።

የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑበት መንገድ በጣም አስደነቀኝ። ጥያቄዎች ይጠይቃሉ፤ ማስረጃዎችን ሰብስበው ይመረምራሉ፤ ከዚያም ምክንያታዊ የሆነ መደምደሚያ ላይ ይደርሳሉ፤ ይህ ደግሞ ለሥራዬ ምርምር ሳደርግ ከምጠቀምበት ዘዴ ጋር ተመሳሳይ ነው! ጄኒፈር ከተጠመቀች ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ማለትም በ1999 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።

የኢኮኖሚክስ እውቀትህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለህን እምነት አጠናክሮልሃል?

በትክክል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ለጥንቱ እስራኤል የሰጠው ሕግ፣ አሁንም ድረስ ምሁራንን ለሚፈታተኑ የኢኮኖሚ ችግሮች መፍትሔ ሰጥቶ ነበር። ሕጉ እስራኤላውያን ለድሆች የሚሆን ምርት እንዲያስተርፉ (ግብር እና ኢንሹራንስ)፣ ለችግረኞች ከወለድ ነፃ የሆነ ብድር እንዲሰጡ (የብድር አገልግሎት) እንዲሁም የውርስ መሬት በየ50 ዓመቱ ለባለቤቱ እንዲመለስ (የንብረት ባለቤትነት መብት) ያዝዝ ነበር። (ዘሌዋውያን 19:9, 10፤ 25:10, 35-37፤ ዘዳግም 24:19-21) እነዚህና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ዝግጅቶች ለሕዝቡ በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ጥቅም ያስገኙ ነበር፦ (1) የገንዘብ ችግር በሚያጋጥማቸው ጊዜ ረድተዋቸዋል፤ (2) ለረጅም ጊዜ በድህነት ውስጥ እንዳይማቅቁ አድርገዋቸዋል፤ እንዲሁም (3) በመካከላቸው የኑሮ ልዩነት እንይፈጠር ረድተዋቸዋል፤ ይህ ሁሉ ተግባራዊ የተደረገው የኢኮኖሚክስ ትምህርት ከመጀመሩ ከ3,000 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ነበር!

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝ የኢኮኖሚ ሁኔታ ለማስፈን የሚያስችል አመለካከትና ምግባር እንዲኖረን ያበረታታል። ለምሳሌ ሰዎች ሐቀኞች፣ እምነት የሚጣልባቸው፣ ሩኅሩኅና ለጋስ እንዲሆኑ ይመክራል። (ዘዳግም 15:7-11፤ 25:15፤ መዝሙር 15) የሚገርመው ነገር፣ በቅርቡ የተከሰተውን ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተከትሎ አንዳንድ የንግድ ትምህርት ቤቶችና ድርጅቶች፣ በንግድና በሒሳብ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች የሙያ ሥነ ምግባር መሥፈርቶችን ለማክበር ቃል እንዲገቡ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል። እኔ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ደንቦች ከእነዚህ የንግድ መመሪያዎች እጅግ የላቁ እንደሆኑ ይሰማኛል።

እምነትህ አንተን በግል የጠቀመህ እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እስከ ዛሬ ካፈራሁት “ሀብት” ሁሉ የላቀ ነው

ጄኒፈር ይበልጥ ምክንያታዊ እንደሆንኩ ይሰማታል። ቀደም ሲል ከሰዎች ፍጽምና እጠብቅ ነበር፤ እንዲሁም አንድ ነገር ወይ ትክክል አሊያም ስህተት መሆን አለበት ብዬ አምን ነበር። ምናልባትም የሒሳብ ባለሙያ በመሆን ረገድ የተሳካልኝ ለዚህ ሊሆን ይችላል! የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተል ይበልጥ ሚዛናዊ እንድሆን ረድቶኛል። አሁን እኔም ሆንኩ ቤተሰቦቼ በጣም ደስተኞች ነን። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኘው ጥበብ ያዘለ ሐሳብ ለሌሎች መናገር ያስደስተናል። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እስከ ዛሬ ካፈራሁት “ሀብት” ሁሉ የላቀ ነው።

^ አን.7 Also called share or equity markets.