በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በምድር ወገብ አካባቢ የሚገኘው ደን በራሪ አትክልተኞች

በምድር ወገብ አካባቢ የሚገኘው ደን በራሪ አትክልተኞች

ማንኛውም አትክልተኛ አንድ ተክል ማብቀል ከፈለገ ትክክለኛው ቦታ ላይ በትክክለኛው ጊዜ መዝራት እንዳለበት ያውቃል። ነገሩ እንግዳ ቢመስልም በምድር ወገብ አካባቢ በሚገኘው ደን ውስጥ ያሉ አንዳንድ ተክሎች ዘር የሚዘራው ግን በምሽት ያውም ከአየር ላይ ነው። ይህን ሥራ የሚያከናውኑት በራሪ አትክልተኞች፣ የአሮጌው ዓለም ፍሬ በል የሌሊት ወፍ ተብለው የሚጠሩት የሌሊት ወፍ ዝርያዎች ናቸው፤ አንዳንዶቹ በራሪ ቀበሮዎች ተብለውም ይጠራሉ። *

ዘር መዝራት

ፍሬ በል የሌሊት ወፎች ጣፋጭ ፍራፍሬ ለማግኘትና አበባ ለመቅሰም በደን ውስጥ የሚዟዟሩት በአብዛኛው ሌሊት ላይ ነው። ይህን በሚያደርጉበት ወቅት ከበሉት ፍሬ ሳይፈጭ የቀረው ክፍል ወይም ዘር ከእዳሪያቸው ጋር ይወጣል። ከዚህም ሌላ በጣም የሚወዱትን የአበባ ማር በሚቀስሙበት ጊዜ እግረ መንገዳቸውን የአበቦቹ ዘሮች እንዲራቡ በማድረግ የአትክልተኝነት ሥራቸውን ያከናውናሉ።

ፍሬ በል የሌሊት ወፍ ዝርያዎች በሌሊት የሚያደርጉት በረራ ብዙ ርቀት ሊሸፍን ስለሚችል በጣም ሰፊ በሆነ አካባቢ ዘር ያሰራጫሉ። በሌሊት ወፎቹ ሆድ ሳይፈጭ የሚያልፈው ዘር ከእዳሪያቸው ጋር አብሮ ስለሚወጣ እዳሪው ለዘሩ እንደ “ማዳበሪያ” ይሆንለታል። በምድር ወገብ አካባቢ በሚገኘው ደን ውስጥ ያሉ የተለያዩ ዕፀዋት፣ ዘራቸው እንዲሰራጭ ወይም የአበቦቻቸው ዘሮች እንዲራቡ የእነዚህ የሌሊት ወፎች እርዳታ የግድ የሚያስፈልጋቸው መሆኑ አያስደንቅም።

እነዚህ የሌሊት ወፍ ዝርያዎች በጣም ርቀው ስለሚበርሩ አቅጣጫ የማወቅና ለየት ያለ የማየት ችሎታ ያስፈልጋቸዋል። በጨለማ ከሰዎች የበለጠ አጥርተው ያያሉ። እንዲያውም አንዳንድ ቀለሞችን መለየት ይችላሉ። በተጨማሪም ቀንም ሆነ ሌሊት መብረር አያስፈራቸውም።

የቤተሰብ ሕይወት

ይህን ታውቅ ነበር? ከሌሎች በርካታ የሌሊት ወፍ ዝርያዎች በተለየ መልኩ ፍሬ በል የሌሊት ወፎች ምግባቸውን የሚፈልጉት የገደል ማሚቶን በመጠቀም አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የማየትና የማሽተት ችሎታቸውን ይጠቀማሉ። ለሌሊት እንቅስቃሴያቸው በጣም አመቺ የሆኑ ትላልቅ ዓይኖች አሏቸው።

ሳሞዋን ፍላዪንግ ፎክስ (የሳሞኣ በራሪ ቀበሮ) የሚባለው የሌሊት ወፍ ዝርያ ዕድሜ ልኩን የሚኖረው አንድ ተጓዳኝ ብቻ ነው። በአንዳንድ የሌሊት ወፍ ዝርያዎች ውስጥ እንስት የሌሊት ወፎች ልጆቻቸውን ለሳምንታት ይዘዋቸው ሲንቀሳቀሱ እንዲሁም ልጆቹ አድገው ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ ሲያጠቧቸው ታይቷል። በሁለት ፍሬ በል የሌሊት ወፍ ዝርያዎች ላይ እንደታየው ደግሞ እንስቷ በምትወልድበት ጊዜ እንደ “አዋላጅ” ሆና የምትረዳት ሌላ የሌሊት ወፍ ልትኖር ትችላለች።

የሚያሳዝነው፣ ፍሬ በል የሌሊት ወፍ ዝርያዎች ሙሉ በሙሉ የመጥፋት አደጋ ተደቅኖባቸዋል፤ ለዚህ አንዱ ምክንያት የመኖሪያ አካባቢያቸው እየወደመ መሆኑ ነው። በደቡባዊ የፓስፊክ ደሴቶች የሚገኙ አንዳንድ የዕፀዋት ዝርያዎች ያለሌሊት ወፎች እርዳታ ሊራቡ ስለማይችሉ የፍሬ በል የሌሊት ወፍ ዝርያዎች መጥፋት በዚህ አካባቢ የሚያስከትለው ጉዳት በጣም ከባድ ይሆናል። በመሆኑም እነዚህ በራሪ አትክልተኞች የሚሰጡት ከፍተኛ አገልግሎት እንደ ቀላል ነገር መታየት የለበትም።

^ አን.2 የአሮጌው ዓለም ፍሬ በል የሌሊት ወፎች በአውስትራሊያ፣ በአፍሪካ፣ በእስያና በአንዳንድ የፓስፊክ ደሴቶች ይገኛሉ።