በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ሃይማኖት

ሃይማኖት

ሃይማኖቶች ይህን ያህል የበዙት ለምንድን ነው?

“የአምላክን ትእዛዝ ትታችሁ የሰውን ወግ አጥብቃችሁ ትከተላላችሁ።”—ማርቆስ 7:8

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ሰዎች በተፈጥሯቸው መንፈሳዊ ነገሮችን የማግኘት ፍላጎት አላቸው፤ ይህን ፍላጎታቸውን ማርካት የሚችሉት ደግሞ አምላክን በማምለክ ነው። (ማቴዎስ 5:3) ሰዎች ይህን ፍላጎታቸውን ለማርካት ሲሉም በአምላክ ሳይሆን በሰዎች አስተሳሰብ ላይ የተመሠረቱ በርካታ ሃይማኖቶችን ፈጥረዋል።

ለምሳሌ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስለነበረ ስለ አንድ ሃይማኖት አባላት ሲናገር የሚከተለውን ብሏል፦ “በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ አይሁን እንጂ ለአምላክ ቅንዓት [አላቸው]፤ የአምላክን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውን ጽድቅ ለመመሥረት ስለፈለጉ ራሳቸውን ለአምላክ ጽድቅ አላስገዙም።” (ሮም 10:2, 3) ዛሬም በተመሳሳይ “የሰውን ሥርዓት” የሚያስተምሩ በርካታ ሃይማኖቶች አሉ።—ማርቆስ 7:7

 የአንድ ሃይማኖት አባል መሆን የግድ አስፈላጊ ነው?

“እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ፤ . . . አንድ ላይ መሰብሰባችንን ቸል አንበል።”—ዕብራውያን 10:24, 25

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ዕብራውያን 10:25 “አንድ ላይ መሰብሰባችንን ችላ አንበል” ይላል። ይህ ጥቅስ፣ አምላክ ሰዎች ተደራጅተው በአንድ ላይ እንዲያመልኩት እንደሚፈልግ ያመለክታል። ይሁንና እያንዳንዱ አምላኪ፣ ስለ አምላክ ማንነትና እሱ ከእኛ ስለሚፈልጋቸው ነገሮች የየራሱ አተረጓጎም ይኖረዋል ማለት ነው? አይደለም። አምላክን በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ባለው መንገድ የሚያመልኩት ሰዎች ‘ሁሉም ንግግራቸው አንድ ሊሆን’ እንዲሁም “በአስተሳሰብም ሆነ በዓላማ ፍጹም አንድነት [ሊኖራቸው]” እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 1:10) እነዚህ ሰዎች በጉባኤዎች ውስጥ ሊታቀፉ እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ላለው “ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር [ሊኖራቸው]” ይገባል። (1 ጴጥሮስ 2:17፤ 1 ቆሮንቶስ 11:16) እንዲህ ዓይነት አንድነት ያለውና የተደራጀ አምልኮ አምላክን ያስደስተዋል።

እውነተኛው ሃይማኖት ተለይቶ ሊታወቅ ይችላል?

“በመካከላችሁ ፍቅር ካለ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።” —ዮሐንስ 13:35

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ እውነተኛ ሃይማኖት ያላቸውን ሰዎች እንዴት መለየት እንደሚቻል በምሳሌ ሲያስረዳ እንዲህ ይላል፦ “በፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ሰዎች ከእሾህ ወይን፣ ከአሜኬላስ በለስ ይለቅማሉ?” (ማቴዎስ 7:16) እሾህን ከወይን ለመለየት የሥነ ዕፅዋት ባለሙያ መሆን አይጠይቅም፤ በተመሳሳይ እውነተኛውን ሃይማኖት ከሐሰተኛው ለመለየት የሃይማኖት ሊቅ መሆን አያስፈልግም። ታዲያ እውነተኛው ሃይማኖት ተለይቶ የሚታወቅባቸው አንዳንድ ፍሬዎች ወይም ገጽታዎች ምንድን ናቸው?

  • እውነተኛው ሃይማኖት የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እውነት ያስተምራል። (ዮሐንስ 4:24፤ 17:17) በሰብዓዊ ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ አይደለም።

  • እውነተኛው ሃይማኖት ሰዎች አምላክን እንዲያውቁ ይረዳል፤ ይህም ይሖዋ የተባለውን ስሙን ማሳወቅን ይጨምራል።—ዮሐንስ 17:3, 6

  • እውነተኛው ሃይማኖት ለሰው ልጆች ችግሮች ብቸኛው ተስፋ ሰብዓዊ መንግሥታት ሳይሆኑ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ያሳውቃል።—ማቴዎስ 10:7፤ 24:14

  • እውነተኛው ሃይማኖት፣ ሰዎች ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር እንዲያሳዩ ያበረታታል። (ዮሐንስ 13:35) ሰዎች ሁሉንም ዘሮችና ጎሳዎች እንዲያከብሩ፣ ንብረታቸውንና ጊዜያቸውን ሌሎችን ለመርዳት እንዲያውሉ እንዲሁም ብሔራት በሚያካሂዷቸው ጦርነቶች ከመካፈል እንዲርቁ ያስተምራል።—ሚክያስ 4:1-4

  • እውነተኛ ሃይማኖት አንድን የአምልኮ ሥርዓት በዘልማድ የመከተል ጉዳይ ሳይሆን በአባላቱ ሕይወት በሙሉ የሚታይ ነገር ነው። አባላቱ የሚሰብኩትን ነገር በሥራ ላይ ያውላሉ።—ሮም 2:21፤ 1 ዮሐንስ 3:18

የዚህ መጽሔት አዘጋጆች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች በንግግራቸውም ሆነ በምግባራቸው አምላክን ለማክበር ይጥራሉ። በመንግሥት አዳራሻቸው በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ ተገኝተህ ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆኑ ለምን ራስህ አታይም?