በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ጥበብ ጮኻ ትጣራለች’—ጥሪዋ ይሰማሃል?

‘ጥበብ ጮኻ ትጣራለች’—ጥሪዋ ይሰማሃል?

“ጥበብ ጮኻ አትጣራምን? ማስተዋልስ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ አታሰማምን? በመንገድ አጠገብ ባሉ ኰረብቶች፣ መንገዶቹ በሚገናኙበትም ላይ ትቆማለች፤ . . . በመግቢያዎቹ ላይ፣ ድምጿን ከፍ አድርጋ . . . ትጮኻለች።”—ምሳሌ 8:1-3

የጥበብ ዋጋ በገንዘብ ሊተመን አይችልም። ጥበብ ከሌለን ደግመን ደጋግመን የሞኝነት ስህተት ልንሠራ እንችላለን። ታዲያ እውነተኛ ጥበብ ከየት ሊገኝ ይችላል? የምሳሌ መጽሐፍ ጸሐፊ ከላይ ያለውን ሐሳብ የተናገረው፣ ፈጣሪያችን ያለውን ወደር የለሽ ጥበብ በአእምሮው ይዞ ነው። ይህ ጥበብ ደግሞ በጣም ልዩ በሆነው መጽሐፍ ይኸውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል ይህን መጽሐፍ ሊያገኘው ይችላል። እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት፦

  • ዘ ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ብሏል፦ “የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በሰፊው የተሠራጨ መጽሐፍ አይገኝም። ከማንኛውም መጽሐፍ በላይ ብዙ ጊዜና በብዙ ቋንቋዎች ተተርጉሟል።” በአሁኑ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል 2,600 ገደማ በሚሆኑ ቋንቋዎች የሚገኝ በመሆኑ ከዓለም ሕዝብ መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ሊያገኘው ይችላል።

  • ጥበብ በሌላም መንገድ ቃል በቃል ‘ድምጿን ከፍ አድርጋ እየጮኸች’ ነው ማለት እንችላለን። በማቴዎስ 24:14 ላይ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው [የዚህ ዓለም መጨረሻ] ይመጣል” የሚል ሐሳብ እናነባለን።

ይህ “ምሥራች” ጥበብ ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ ነው የምንለው አምላክ ለሰው ልጅ ችግሮች በሙሉ መፍትሔ የሚሰጥበትን መንገድ ስለሚጠቁም ነው፤ ይህም የአምላክ መንግሥት ነው። ይህ በአምላክ የተቋቋመ መስተዳድር ወደፊት መላዋን ምድር ይገዛል፤ በዚያን ጊዜ ዓለም የሚተዳደረው በአንድ መንግሥት ብቻ ይሆናል። (ዳንኤል 2:44፤ 7:13, 14) ስለሆነም ኢየሱስ ክርስቶስ “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን” ሲል ጸልዮአል።—ማቴዎስ 6:9, 10

የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት በ239 አገሮች እያስተዋወቁ ሲሆን ይህን መብታቸውን ከፍ አድርገው ይመለከቱታል። በእርግጥም፣ መለኮታዊ ጥበብ “በመግቢያዎች” ማለትም በእያንዳንዱ በር ‘እየጮኸች ነው።’ ታዲያ ጥሪዋ ይሰማሃል?