በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአውሮፓ የተካሄደው የጠንቋዮች አደን

በአውሮፓ የተካሄደው የጠንቋዮች አደን

ከጥቂት መቶ ዓመታት በፊት በአውሮፓ ውስጥ ጥንቆላና መተት ያሳደሩት ፍርሃት በጥንቆላ ሥራ የሚጠረጠሩ ሰዎችን አድኖ የመግደል ዘመቻ እንዲካሄድ በር ከፍቶ ነበር። ይህ ዘመቻ በአብዛኛው የተካሄደው በስዊዘርላንድ፣ በጀርመን፣ በሰሜናዊ ጣሊያንና በፈረንሳይ፣ እንዲሁም በሉክሰምበርግ፣ በቤልጂየምና በኔዘርላንድ ነው። ዊች ኸንትስ ኢን ዘ ዌስተርን ዎርልድ * (በምዕራቡ ዓለም የተካሄደ የጠንቋዮች አደን) የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው “በአውሮፓና የአውሮፓ ቅኝ ግዛት በሆኑ አገሮች ውስጥ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሞቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ተሠቃይተዋል፣ ታስረዋል፣ ምርመራ ተካሂዶባቸዋል፤ እንዲሁም ጥላቻ፣ ውንጀላና ማስፈራሪያ ደርሶባቸዋል።” ለመሆኑ እንዲህ ያለው እብደት እንዴት ጀመረ? እንዲቀጣጠል ያደረገውስ ነገር ምንድን ነው?

ኢንክዊዚሽንና የጠንቋዮች መዶሻ

የአደኑን እሳት በዋነኝነት ያቀጣጠለው ኢንክዊዚሽን (የካቶሊክ ችሎት) ነው። ደ ኸክሰንቫን (ጠንቋዮችን ማሳደድ) የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ኢንክዊዚሽን የተፈጠረው በ13ኛው መቶ ዘመን በሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን ዓላማውም “ከሃዲዎችን መመለስና ሌሎች ከእምነት ጎዳና እንዳይወጡ ማድረግ ነበር።” ኢንክዊዚሽን ለቤተ ክርስቲያኒቱ እንደ ፖሊስ ኃይል ሆኖ ያገለግል ነበር ማለት ይቻላል።

ታኅሣሥ 5 ቀን 1484 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ኢኖሰንት ስምንተኛ ጥንቆላን የሚያወግዝ ጳጳሳዊ ድንጋጌ አወጡ። በተጨማሪም ያኮፕ ሽፕሬንገር እና ሃይንሪክ ክሬመር (በላቲን ስሙ ሄንሪከስ ኢንስቲቶረስ ተብሎም ይጠራል) ለተባሉ ሁለት መርማሪዎች ጉዳዩን ዳር እንዲያደርሱ ሥልጣን ሰጧቸው። ሁለቱ ሰዎች ማልዩስ ማለፊካሩም (የጠንቋዮች መዶሻ) የሚል ርዕስ የተሰጠው መጽሐፍ አዘጋጁ። ካቶሊኮችም ሆኑ ፕሮቴስታንቶች ይህን መጽሐፍ ከጥንቆላ ጋር በተያያዘ እንደ መጨረሻ ባለሥልጣን አድርገው ተቀብለውት ነበር። መጽሐፉ በተረት ላይ የተመሠረቱ ታሪኮችን የያዘ ነበር፤ ጥንቆላን የሚቃወሙ ሃይማኖታዊና ሕግ ነክ ማስረጃዎችን ከማቅረቡም በላይ ጠንቋዮችን መለየትና ማጥፋት ስለሚቻልበት መንገድ መመሪያ ይሰጣል። የጠንቋዮች መዶሻ  የተባለው መጽሐፍ “በአረመኔነቱና ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱ በዓለም የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት መጽሐፍ” ተብሏል።

የጠንቋዮች መዶሻ የተባለው መጽሐፍ “በአረመኔነቱና ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱ በዓለም የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት መጽሐፍ” ተብሏል

አንድን ሰው በጥንቆላ ወንጀል ለመክሰስ ጥፋተኛ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ አያስፈልግም። ኸክሰን ኡንት ኸክሰንፕሮዘሰ (ጠንቋዮችና የጠንቋዮች ችሎት) የተባለው መጽሐፍ እንደተናገረው ችሎቶቹ የሚካሄዱበት ዓላማ “ተከሳሹን በማሳመን፣ በመጫን ወይም በማስገደድ ወንጀሉን መሥራቱን እንዲቀበል ማድረግ ብቻ ነበር።” ቁም ስቅል ማሳየት የተለመደ ነበር።

የጠንቋዮች መዶሻ መውጣቱን እና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ኢኖሰንት ስምንተኛ ጳጳሳዊ ድንጋጌ ማወጃቸውን ተከትሎ በአውሮፓ ጠንቋዮችን ማደን ተጀመረ። በተጨማሪም ለዘመኑ አዲስ የነበረው የኅትመት ቴክኖሎጂ ይህ እብደት እንዲስፋፋ ሌላው ቀርቶ ከአትላንቲክ ማዶ ወዳለው አሜሪካ እንዲዳረስ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ተከሳሾቹ እነማን ነበሩ?

ከ70 በመቶ የሚበልጡት ተከሳሾች ሴቶች ነበሩ፤ ከእነዚህ ውስጥ ተሟጋች የሌላቸው መበለቶች ይገኙበታል። ድሆች፣ አረጋውያን፣ የባሕል መድኃኒት የሚሸጡ ሴቶች (በተለይ የሰጡት መድኃኒት ካልሠራ) የዚህ ዘመቻ ሰለባ ይሆኑ ነበር። ሀብታም ድሃ፣ ወንድ ሴት የማይል እንዲሁም ከተራ ሰው እስከ ባለሥልጣን ድረስ ማንንም ሰው ሊነካ የሚችል ዘመቻ ነበር።

ጠንቋይ እንደሆኑ የሚታሰቡ ሰዎች ለማንኛውም ዓይነት ክፉ ነገር ተጠያቂ ይደረጉ ነበር። “በረዶ እንዲዘንብ በማድረግ እንዲሁም ቀንድ አውጣና አባ ጨጓሬ በመላክ ሰብሉንና የምድሪቱን ፍሬ ያጠፋሉ” ተብለው ይከሰሱ እንደነበር ዳማልስ የተባለ የጀርመን መጽሔት ተናግሯል። ሰብል በበረዶ ቢመታ፣ ላም ወተት ባትሰጥ፣ አንድ ወንድ ስንፈተ ወሲብ ቢኖርበት ወይም አንዲት ሴት መካን ብትሆን የሚወነጀሉት ጠንቋዮች ነበሩ።

ጠንቋዮች ክብደት የላቸውም ተብሎ ይታሰብ ስለነበር አንዳንድ ተጠርጣሪዎች ይመዘኑ ነበር

ለመሆኑ አንድ ሰው ጠንቋይ መሆኑ የሚለየው እንዴት ነበር? አንዳንድ ተጠርጣሪዎች ታስረው ቀዝቃዛ ጠበል ውስጥ ይነከራሉ። ከሰመጡ ንፁሕ እንደሆኑ ተቆጥረው ተጎትተው እንዲወጡ ይደረጋል። ከተንሳፈፉ ግን ጠንቋዮች ናቸው ተብለው እዚያው ይገደላሉ ወይም ለፍርድ ይቀርባሉ። ሌሎች ተጠርጣሪዎች ደግሞ ክብደታቸው ይመዘናል፤ ምክንያቱም ጠንቋዮች ክብደት የላቸውም ተብሎ ይታሰብ ነበር።

ሌላው መለያ ዘዴ ደግሞ በምዕራቡ ዓለም የተካሄደ የጠንቋዮች አደን በተባለው መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው “ዲያብሎስ ከጠንቋዩ ጋር ከተገናኘ በኋላ የሚተወውን ግልጽ የዲያብሎስ ምልክት” ፈልጎ ማግኘት ነው። ባለሥልጣናቱ ተከሳሹን በሕዝብ ፊት ያቆሙትና “በሰውነቱ ላይ ያለውን ፀጉር በሙሉ ከላጩ በኋላ እያንዳንዱን የሰውነት ክፍል ምንጥር አድርገው ይመረምራሉ።” ከዚያም በቆዳው ላይ ያገኙትን ማንኛውንም ምልክት፣ ኪንታሮትና ጠባሳ መርፌ ይወጋሉ። መርፌው ካላሳመመው ወይም ካላደማው ያ ቦታ የሰይጣን ምልክት እንደሆነ ይቆጠራል።

የካቶሊክም ሆኑ የፕሮቴስታንት መንግሥታት የጠንቋዮችን አደን ደግፈዋል፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ፕሮቴስታንት መሪዎች ከካቶሊኮቹ የበለጠ ጨካኝ ሆነው ተገኝተዋል። ውሎ አድሮ ግን ምክንያታዊ አስተሳሰብ መስፈን ጀመረ። ለምሳሌ ያህል፣ ጠንቋዮች ተብለው የተፈረደባቸውን በርካታ ሰዎች በግንድ ላይ ተሰቅለው ወደሚቃጠሉበት ቦታ አጅበው ይወስዱ የነበሩት ፍሪድሪክ ሽፔይ የተባሉት የካቶሊክ ቄስ በእሳቸው አመለካከት አንዱም ተከሳሽ ጥፋተኛ እንዳልነበረ በ1631 ጽፈዋል። የጠንቋዮች አደን ካልተገታ ምድሪቱ ባዶ እንደምትሆንም አስጠንቅቀው ነበር። ይህ በዚህ እንዳለ ሐኪሞች፣ የሚጥል በሽታና ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች በአጋንንት ምክንያት የሚመጡ ሳይሆኑ የጤና እክሎች እንደሆኑ መገንዘብ ጀመሩ። በ17ኛው መቶ ዘመን በችሎት ፊት የሚቀርቡ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰ ሲሆን በዚያው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ቆሞ ነበር ማለት ይቻላል።

ከዚህ ዘግናኝ ዘመን ምን እንማራለን? አንዱ ትምህርት የሚከተለው ነው፦ ክርስቲያን ነን ባዮች ንጹሕ የሆኑትን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶች በሃይማኖታዊ ውሸቶችና በአጉል እምነቶች ሲቀይሩ ለብዙ ዓይነት የክፋት ድርጊቶች በር ከፍተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያሉ ከሃዲዎች በእውነተኛው ክርስትና ላይ ስለሚያመጡት ነቀፋ አስቀድሞ ሲናገር “የእውነት መንገድ ይሰደባል” ብሏል።—2 ጴጥሮስ 2:1, 2

^ አን.2 የአውሮፓ ቅኝ ግዛቶች አሜሪካንም ይጨምሩ ነበር።