በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

ኢንተርኔት ስለሚያስከትለው አደጋ ወጣቶችን ማስተማር

ኢንተርኔት ስለሚያስከትለው አደጋ ወጣቶችን ማስተማር

ተፈታታኙ ነገር

የዜና ዘገባዎች ላይ የሰማችሁት ነገር ኢንተርኔት የስም አጥፊዎች፣ የፆታ ጥቃት የሚፈጽሙና የሰውን ማንነት የሚሰርቁ ሰዎች መመሸጊያ እንደሆነ እንዲሰማችሁ አድርጎ ሊሆን ይችላል። ይህ ጉዳይ ቢያሳስባችሁ የሚያስገርም አይደለም፤ ምክንያቱም በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኘው ልጃችሁ ኢንተርኔት በመጠቀም ብዙ ሰዓት የሚያሳልፍ ከመሆኑም በላይ ኢንተርኔት ስላለው አደጋ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ይሰማችሁ ይሆናል።

ልጃችሁ ኢንተርኔት ሲጠቀም ጠንቃቃ እንዲሆን ልታስተምሩት ትችላላችሁ። በመጀመሪያ ግን ስለ ኢንተርኔት ዓለም ልታውቋቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮችን እንመልከት።

ልታውቋቸው የሚገቡ ነገሮች

ወጣቶች በተንቀሳቃሽ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች አማካኝነት ኢንተርኔት መጠቀም ይችላሉ። ኮምፒውተር ሌሎች ሊያዩት በሚችሉት ቦታ ላይ ይቀመጥ የሚለው ምክር አሁንም ጠቃሚ ነው። ይሁን እንጂ ልጃችሁ በታብሌት ወይም በሞባይል ስልክ አማካኝነት የኢንተርኔትን ዓለም ውስጥ መግባት ይችላል፤ በመሆኑም በዛሬው ጊዜ ኢንተርኔት ማግኘት በጣም ቀላል ሆኗል። ይህን የሚያደርገው ደግሞ ከእናንተ እይታ ውጭ ነው።

አንዳንዶች የመኪና አደጋ ስላጋጠማቸው ብቻ መኪና መንዳት ስህተት ነው ማለት አይደለም። ከኢንተርኔት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ልጃችሁ ኢንተርኔትን በጥንቃቄ “ማሽከርከር” የሚችለው እንዴት እንደሆነ መማር አለበት

አንዳንድ ወጣቶች ኢንተርኔት በመጠቀም ብዙ ጊዜ ያጠፋሉ። አንዲት የ19 ዓመት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ለአምስት ደቂቃ ያህል ኢ-ሜይል ለማየት ብዬ ኮምፒውተሬን አበራና ሳላስበው ለበርካታ ሰዓታት ቪዲዮ ሳይ እቆያለሁ። ራሴን መግዛት በጣም ያስፈልገኛል።”

ወጣቶች ኢንተርኔት ላይ ማስቀመጥ የማይገባቸውን መረጃ ሊያወጡ ይችላሉ። መሠሪ የሆኑ ሰዎች በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ በኢንተርኔት ላይ ያሰፈራቸውን ሐሳቦችና ያወጣቸውን ፎቶግራፎች አገጣጥመው ወጣቱ የሚኖርበትን ቦታ፣ የሚማርበትን ትምህርት ቤት እንዲሁም ቤተሰቡ ቤት የማይገኝበትን ጊዜና የመሳሰሉትን መረጃዎች ማወቅ ይችላሉ።

አንዳንድ ወጣቶች ኢንተርኔት ላይ የሚያወጡት መረጃ የሚያስከትለውን መዘዝ አያገናዝቡም። አንድ ነገር አንዴ ኢንተርኔት ላይ ከወጣ በኋላ እዚያው ይቀራል። አንድ ወጣት በኢንተርኔት ላይ ያስቀመጣቸው የሚያሳፍሩ ሐሳቦችና ፎቶግራፎች አንድ ቀን ሊገኙ ይችላሉ፤ ለምሳሌ ይህን ወጣት ሊቀጥር የሚፈልግ አንድ አሠሪ የወጣቱን ጀርባ ማጥናት ቢፈልግ እነዚህን መረጃዎች ማግኘት ይችላል።

እንዲህ ዓይነት አሳሳቢ ነገሮች ቢኖሩም ጠላታችሁ ኢንተርኔት እንዳልሆነ አትርሱ። ከዚህ ይልቅ ችግር የሚፈጥረው ጥበብ የጎደለው የኢንተርኔት አጠቃቀም ነው።

 ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ቅድሚያ ሊሰጣቸው ስለሚገቡ ነገሮችና ስለ ጊዜ አጠቃቀም ልጃችሁን አስተምሩት። አንድ ሰው ኃላፊነት የሚሰማው መሆኑ ከሚታወቅባቸው መንገዶች አንዱ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ነገሮች ቅድሚያ የሚሰጥ መሆኑ ነው። ከቤተሰብ ጋር መነጋገር እንዲሁም የትምህርት ቤትና የቤት ውስጥ ሥራዎችን መሥራት ኢንተርኔትን በመቃኘት ጊዜ ከማሳለፍ የበለጠ አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። ልጃችሁ ኢንተርኔት ላይ የሚያሳልፈው ጊዜ ካሳሰባችሁ ገደብ አውጡለት፤ አስፈላጊ ከሆነ የጊዜ መቆጣጠሪያ ሰዓት ማስቀመጥ ይቻላል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ፊልጵስዩስ 1:10

ልጃችሁ ማንኛውንም ነገር ኢንተርኔት ላይ ከማስቀመጡ በፊት እንዲያመዛዝን አሠልጥኑት። ልጃችሁ እንደሚከተሉት ያሉትን ጥያቄዎች እንዲያስብባቸው አድርጉ፦ ኢንተርኔት ላይ ለማስቀመጥ (ፖስት ለማድረግ) ያሰብኩት ሐሳብ ሌላን ሰው ሊጎዳ ይችላል? ይህ ፎቶግራፍ ምን ዓይነት ስም ያሰጠኛል? ወላጆቼ ወይም ሌላ ትልቅ ሰው ይህን ፎቶግራፍ ወይም ሐሳብ ቢያዩት እሸማቀቃለሁ? ኢንተርኔት ላይ ያስቀመጥኩትን ነገር ቢመለከቱት ስለ እኔ ምን ይሰማቸዋል? አንድ ሰው እንዲህ ያለ ሐሳብ ወይም ፎቶግራፍ ፖስት ቢያደርግ ስለ እሱ ምን ዓይነት ግምት ይኖረኛል?—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 10:23 NW

ልጃችሁ በሕግ ብቻ የሚመራ ሳይሆን የራሱ የሥነ ምግባር አቋም እንዲኖረው አሠልጥኑት። ልጃችሁ የሚያደርገውን ነገር ተከታትላችሁ አትዘልቁትም። ደግሞም ዓላማችሁ ልጆቻችሁን መቆጣጠር ሳይሆን “ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችሉ የማስተዋል ችሎታቸውን” እንዲያሠለጥኑ መርዳት ነው። (ዕብራውያን 5:14) ስለዚህ ሕጎችንና ቅጣትን እንደ ዋነኛ መሣሪያ ከመጠቀም ይልቅ ልጃችሁ የሥነ ምግባር አቋም እንዲኖረው እርዱት። ምን ዓይነት ስም ማትረፍ ይፈልጋል? መታወቅ የሚፈልገው በምን ዓይነት ባሕርይ ነው? ግባችሁ እናንተ ኖራችሁም አልኖራችሁ ልጃችሁ ጥሩ ውሳኔ እንዲያደርግ መርዳት ነው።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 3:21

“ልጆች ስለ ቴክኖሎጂ የተሻለ እውቀት አላቸው። ወላጆች ደግሞ ስለ ሕይወት የተሻለ እውቀት አላቸው”

ኢንተርኔት መጠቀም መኪና ከማሽከርከር ጋር ይመሳሰላል፤ ሁለቱም የቴክኖሎጂ እውቀት ብቻ ሳይሆን ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ይፈልጋሉ። በመሆኑም የእናንተ አመራር ወሳኝ ነው። የኢንተርኔት ደኅንነት ኤክስፐርት የሆኑት ፓሪ አፍታብ የተባሉት ባለሙያ የተናገሩት ነገር ጉዳዩን ጠቅለል አድርጎ ያስቀምጠዋል፦ “ልጆች ስለ ቴክኖሎጂ የተሻለ እውቀት አላቸው። ወላጆች ደግሞ ስለ ሕይወት የተሻለ እውቀት አላቸው።”