በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ደቡብ ምሥራቅ እስያ

የዓለም የዱር እንስሳት ተቋም እንደገለጸው ከ1997 እስከ 2011 ባሉት ዓመታት ላኦስን፣ ምያንማርን፣ ታይላንድን፣ ካምቦዲያን፣ ቻይና ውስጥ ያለውን የዩናን ግዛትንና ቬትናምን በሚያጠቃልለው በታላቁ ሚኮንግ አካባቢ ውስጥ ባለቀይ ዓይን እፉኝትን ጨምሮ በርካታ አዳዲስ የዕፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎች ተገኝተዋል። በ2011 ብቻ ከተገኙት አዳዲስ ዝርያዎች መካከል 82 የዕፅዋት ዝርያዎች፣ 21 በደረት የሚሳቡ እንስሳት፣ 13 የዓሣ ዝርያዎች፣ 5 በውኃ ውስጥም ሆነ በየብስ ላይ የሚኖሩ እንስሳት እና 5 አጥቢዎች ይገኛሉ።

አውሮፓ

ዘ ሞስኮ ታይምስ ላይ የወጣ አንድ ዘገባ እንደገለጸው ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር “በመላው የአውሮፓ ኅብረት አገራት” ከባድ ችግር ሆኗል። ሰዎች ወሲባዊ መጠቀሚያ ለመሆን፣ ለግዳጅ ሥራ እንዲሁም “ሕገ ወጥ ለሆነ የሰው አካል ንግድ” ጭምር ይሸጣሉ። ድህነት፣ ሥራ አጥነትና የፆታ መድልዎ በተስፋፋባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ሕገ ወጥ ለሆነ የሰዎች ዝውውር ይበልጥ የተጋለጡ ናቸው።

ኒው ዚላንድ

ሕፃናትና በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ቴሌቪዥን በማየት የሚያሳልፉትን ጊዜ ያጠኑ ተመራማሪዎች፣ ለረጅም ሰዓታት ቴሌቪዥን የመመልከት ልማድ “በወጣትነት ዕድሜ ላይ ለሚታይ ከሰዎች ጋር የመቀላቀል ችግር ምክንያት እንደሚሆን” ደምድመዋል። ተመራማሪዎቹ “ልጆች ማየት የሚኖርባቸው ጥሩ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ሆኖ በቀን ውስጥ ከ1 ወይም ከ2 ሰዓት መብለጥ” እንደሌለበት የሚሰጠው ምክር ተገቢ እንደሆነ ደርሰውበታል።

አላስካ

ጥንታዊ ነዋሪዎች የሚኖሩባቸው የአላስካ መንደሮች፣ ሁሉም ለማለት ይቻላል በባሕር ዳርቻዎች ወይም በወንዞች አቅራቢያ የተቆረቆሩ ናቸው፤ በመሆኑም ከእነዚህ መንደሮች መካከል 86 በመቶ የሚሆኑት በጎርፍ ወይም በመሬት መሸርሸር ይጠቃሉ። በባሕር ዳርቻዎች ላይ ይጋገር የነበረው በረዶ በሙቀት መጨመር ምክንያት ለመርጋት በቂ ጊዜ ስለማያገኝ መንደሮቹ በመጸው ወራት ለውሽንፍር ተጋላጭ ሆነዋል።

ዓለም

እንደ ነፋስና ፀሐይ ያሉትን ብክለት የማያስከትሉ የኃይል ምንጮች የሚጠቀሙ ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋት ከፍተኛ ገንዘብ ቢፈስስም “ዛሬም ኃይል ለማመንጨት ሲባል የሚደርሰው ብክለት ከ20 ዓመት በፊት ከነበረው ያነሰ አይደለም” በማለት የዓለም አቀፍ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ማርያ ቫን ደር ሁቨን ተናግረዋል።