በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

ያልተነገረው የፍጥረት ታሪክ

ያልተነገረው የፍጥረት ታሪክ

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጽንፈ ዓለማት አጀማመር የሚናገረውን ታሪክ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አንብበውታል ወይም ሰምተውታል። ከ3,500 ዓመታት በፊት የተጻፈው ይህ ዘገባ የሚጀምረው “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” በሚለው የታወቀ ዓረፍተ ነገር ነው።

የፍጥረት ቀናት የ24 ሰዓት ርዝመት እንዳላቸው የሚያምኑ ክርስቲያኖችን ጨምሮ ብዙ የክርስትና መሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስን የፍጥረት ታሪክ በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም ከትክክለኛው ሐሳብ የራቁ ትንታኔዎችን እንደፈጠሩ ግን ብዙ ሰዎች አያውቁም። እነዚህ አተረጓጎሞች ከሳይንሳዊ እውነቶች ጋር በቀጥታ የሚጋጩ ናቸው። እርግጥ ነው፣ እነዚህ የፈጠራ ሐሳቦች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኙም፤ ያም ሆኖ አንዳንድ ሰዎች እነዚህን ሐሳቦች መስማታቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው የፍጥረት ዘገባ ምናብ የወለደው እንደሆነ አድርገው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል።

ብዙ ሰዎች ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ልብ ሳይሉት ቀርተዋል። ይህ በጣም አሳዛኝ ነው፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጽንፈ ዓለማት አጀማመር የሚናገረው ታሪክ በጣም አሳማኝና ትክክለኛ ነው። ከዚህም በላይ ይህ ታሪክ ከሳይንሳዊ ግኝቶች ጋር ይስማማል። አዎ፣ ያልተነገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ የፍጥረት ታሪክ ስታውቅ መደነቅህ አይቀርም!

ያልተፈጠረው ፈጣሪ

የመጽሐፍ ቅዱስ የፍጥረት ታሪክ፣ ከሁሉ የበላይና ሁሉን ቻይ የሆነ እንዲሁም ሁሉን የፈጠረ አንድ አካል መኖሩን በግልጽ ያሳያል። ታዲያ ይህ አካል ማን ነው? ያለውስ አካል ምን ዓይነት ነው? ይህ አካል በሰፊው በሚታወቁ ባሕሎችና ሃይማኖቶች ውስጥ ከሚገኙት አማልክት ፈጽሞ የተለየ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። እሱ የሁሉ ነገር ፈጣሪ ነው፤ ያም ቢሆን አብዛኞቹ ሰዎች ስለ እሱ ያላቸው እውቀት በጣም አነስተኛ ነው።

 • አምላክ አካል አለው። የራሱ የሆነ አካል የሌለውና እንዲያው ዝም ብሎ በሁሉም ቦታ ተሰራጭቶ የሚገኝ ኃይል አይደለም። የሚያስብ እንዲሁም ስሜትና ዓላማ ያለው አምላክ ነው።

 • አምላክ ገደብ የሌለው ኃይልና ጥበብ አለው። በሁሉም ፍጥረት በተለይ ደግሞ ሕይወት ባላቸው ነገሮች ላይ በጣም ውስብስብ የሆነ ንድፍ የምናየው በዚህ ምክንያት ነው።

 • ቁስ አካልን የፈጠረው አምላክ ነው። በመሆኑም እሱ ካስገኛቸው ንጥረ ነገሮች ሊሠራ አይችልም። ከዚህ ይልቅ መንፈሳዊ አካል ነው።

 • የአምላክ ሕልውና በጊዜ የተገደበ አይደለም። ያልነበረበት ጊዜ የለም፤ ወደፊትም ይኖራል። በመሆኑም በማንም አልተፈጠረም።

 • አምላክ የግል መጠሪያ ስም ያለው ሲሆን ይህ ስሙ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ጊዜያት ተጠቅሶ ይገኛል። ስሙም ይሖዋ ይባላል።

 • ይሖዋ አምላክ የሰው ልጆችን ይወዳል፤ እንዲሁም ያስብላቸዋል።

 አምላክ ጽንፈ ዓለማትን ለመፍጠር ምን ያህል ጊዜ ፈጅቶበታል?

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ‘ሰማያትንና ምድርን እንደፈጠረ’ ይናገራል። ይሁን እንጂ ይህ በጥቅሉ የሰፈረ ሐሳብ፣ አምላክ ጽንፈ ዓለማትን ለመፍጠር ምን ያህል ጊዜ እንደፈጀበትም ሆነ ጽንፈ ዓለማትን ቅርጽ ለማስያዝ በምን ዘዴ እንደተጠቀመ አይጠቅስም። ታዲያ ጽንፈ ዓለማት የተፈጠሩት ቃል በቃል የ24 ሰዓት ርዝማኔ ባላቸው ስድስት ቀናት እንደሆነ የሚያምኑ ሰዎች ስለሚናገሩት ነገርስ ምን ማለት ይቻላል? በሳይንስ ባለሙያዎች ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ይህ ሐሳብ የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ በትክክል ካለመረዳት የመጣ ነው። እስቲ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለውን ትክክለኛ ሐሳብ እንመልከት።

የፍጥረት ቀናት ቃል በቃል የ24 ሰዓት ርዝመት አላቸው የሚለውን እምነት መጽሐፍ ቅዱስ አይደግፍም

 • የፍጥረት ቀናት ቃል በቃል የ24 ሰዓት ርዝመት አላቸው የሚለውን እምነት መጽሐፍ ቅዱስ አይደግፍም።

 • በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ቀን” የሚለው ቃል የተለያየ የጊዜ ርዝመትን ለማመልከት ተሠርቶበታል። ቃሉ ያልተወሰነ የጊዜ ርዝመትን ለማመልከት የሚሠራበት ጊዜም አለ። በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ በሚገኘው የፍጥረት ታሪክ ውስጥ የተገለጸው “ቀን” ለዚህ እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል።

 • በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ እያንዳንዱ የፍጥረት ቀን በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ርዝመት ሊኖረው ይችላል።

 • የመጀመሪያው የፍጥረት ቀን ከመጀመሩ በፊት አምላክ ሕይወት አልባ የነበረችውን ምድር ጨምሮ ጽንፈ ዓለማትን ፈጥሮ ነበር።

 • ከሁኔታው ማየት እንደሚቻለው ስድስቱ የፍጥረት ቀናት፣ ይሖዋ አምላክ ምድርን ለሰው መኖሪያነት ምቹ አድርጎ ለማዘጋጀት የተጠቀመበትን ረዘም ያለ ጊዜ ያመለክታሉ።

 • የመጽሐፍ ቅዱስ የፍጥረት ታሪክ፣ ሳይንስ ስለ ጽንፈ ዓለማት ዕድሜ ከደረሰበት ግኝት ጋር አይጋጭም።

አምላክ በዝግመተ ለውጥ ተጠቅሟል?

በመጽሐፍ ቅዱስ የማያምኑ ብዙ ሰዎች፣ ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት በሙሉ ሕይወት አልባ ከሆኑ ኬሚካሎች እንዲሁ በአጋጣሚ ማለትም ባልታወቀና ዓላማ በሌለው ሂደት አማካኝነት እንደተገኙ ያምናሉ። በዚህ ጽንሰ ሐሳብ መሠረት በሆነ ወቅት ላይ ራሱን በራሱ የሚያባዛ ባክቴሪያ መሰል ሕያው ነገር ተገኘ፤ ከዚያም ይህ ባክቴሪያ ቀስ በቀስ በአሁኑ ጊዜ የሚገኙ ዝርያዎች በሙሉ አስገኘ ተብሎ ይታመናል። ይህ ማለት ከአእምሮ የመረዳት አቅም በላይ የሆነው ውስብስብ የሰው ልጅ ከባክቴሪያ ተሻሽሎ የመጣ ነው ማለት ነው።

የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ በሚያምኑ ሰዎች ዘንድ ሳይቀር ተቀባይነት አግኝቷል። እነዚህ ሰዎች እንደሚያምኑት ከሆነ አምላክ የመጀመሪያውን ሕይወት ያለው ነገር ምድር ላይ ካስገኘ በኋላ በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ሌሎች ሕይወት ያላቸውን ነገሮች እንዲገኙ አድርጓል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ከዚህ የተለየ ነው።

የመጽሐፍ ቅዱስ የፍጥረት ታሪክ በአንድ ወገን ውስጥ በሚገኙ እንስሳት ወይም ዕፅዋት መካከል ልዩነት መኖሩን ከሚገልጸው ሳይንሳዊ ግኝት ጋር አይጋጭም

 • በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ይሖዋ አምላክ የተለያዩ ዕፅዋትንና እንስሳትን የፈጠረው በወገን በወገናቸው ነው፤ እንዲሁም ራሳቸውን የማወቅ ብሎም እንደ ፍቅር፣ ጥበብና ፍትሕ ያሉ ባሕርያትን የማንጸባረቅ ችሎታ ያላቸውን ፍጹማን ወንድና ሴት ፈጥሯል።

 • አምላክ የፈጠራቸው እንስሳትና ዕፅዋት እየበዙ ሲሄዱ ከወገናቸው ሳይወጡ ዛሬ የሚታዩትን የተለያዩ ዝርያዎችን አስገኝተዋል። እነዚህ ዝርያዎች በአብዛኛው አንዳቸው ከሌላው ይለያሉ።

 • የመጽሐፍ ቅዱስ የፍጥረት ታሪክ በአንድ ወገን ውስጥ በሚገኙ እንስሳት ወይም ዕፅዋት መካከል ልዩነት መኖሩን ከሚገልጸው ሳይንሳዊ ግኝት ጋር አይጋጭም።

 ፍጥረት ስለ ፈጣሪ ያሳውቀናል

በ1800ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ አልፍሬድ ራሰል ዋላስ የተባለው የብሪታንያ የባዮሎጂ ባለሙያ ዝግመተ ለውጥ የሚከናወነው በተፈጥሯዊ ምርጦሽ አማካኝነት ነው ከሚለው የዳርዊን ንድፈ ሐሳብ ጋር ተስማምቶ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ እውቅ የዝግመተ ለውጥ አራማጅ እንኳ እንደሚከተለው እንዳለ ይነገራል፦ “የሚያይ ዓይንና ማሰብ የሚችል አእምሮ ያለው ሁሉ ቅንጣት በምታክለው ሴል፣ በደም፣ በመላው ምድር፣ እንዲሁም በግዙፉ ጽንፈ ዓለማት . . . ውስጥ ብልሃትና እውቀት በአጭሩ አእምሮ መኖሩን ማስተዋል ይችላል።”

ዋላስ ከኖረበት ዘመን ሁለት ሺህ ዓመት ያህል ቀደም ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሏል፦ “[የአምላክ] የማይታዩት ባሕርያቱ ይኸውም ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል።” (ሮም 1:20) አልፎ አልፎ፣ ጊዜ ወስደህ ከአንዲት የሣር ቅጠል አንስቶ ቁጥር ስፍር እስከሌላቸው የሰማይ አካላት ድረስ ባሉት ፍጥረታት ውስጥ የሚታየውን አስደናቂና ውስብስብ የሆነ ንድፍ ለማሰብ ሞክር። የፍጥረት ሥራዎችን ልብ ብለህ በመመልከት ስለ ፈጣሪ ማወቅ ትችላለህ።

ሆኖም እንደሚከተለው ያሉ ጥያቄዎች ይፈጠሩብህ ይሆናል፦ ‘ሁሉን ነገር የፈጠረ አፍቃሪ የሆነ አምላክ ካለ ታዲያ ለምን መከራ እንዲኖር ፈቀደ? በምድር ላይ ያሉ ፍጥረታቱን ትቷቸዋል? የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞ ይመጣል?’ መጽሐፍ ቅዱስ ሌሎች ብዙ ያልተነገሩ ዘገባዎችን ይዟል፤ እነዚህ እውነቶች ሰዎች በፈጠሯቸው ሐሳቦች እንዲሁም በሃይማኖታዊ ትምህርቶች የተነሳ ከአብዛኞቹ የሰው ልጆች ተሰውረው ኖረዋል። ይህን መጽሔት የሚያዘጋጁት የይሖዋ ምሥክሮች፣ ያልተበረዘውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንድትመረምር እንዲሁም ስለ ፈጣሪና የሰው ልጆች ወደፊት ስለተዘጋጀላቸው ተስፋ ተጨማሪ እውቀት እንድታገኝ ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው።