በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በቀለማት ያሸበረቀች እመቤት—ሚስጥሩ ተገለጠ

በቀለማት ያሸበረቀች እመቤት—ሚስጥሩ ተገለጠ

አውሮፓውያን ተመራማሪዎች በቀለማት ያሸበረቀች እመቤት በመባል የሚታወቁት ቢራቢሮዎች (ቫኒሳ ካርዱይ) የበጋው ወቅት ሲያበቃ ወዴት እንደሚሰወሩ ግራ ይገባቸው ነበር። እነዚህ ቢራቢሮዎች ከአካባቢው የሚሰወሩት በቅዝቃዜው የተነሳ ስለሚሞቱ ይሆን? በቅርቡ የተካሄዱ ምርምሮች አንድ አስደናቂ መረጃ ይፋ አድርገዋል። ቢራቢሮዎቹ በየዓመቱ ከሰሜን አውሮፓ ተነስተው አፍሪካ ደርሰው ይመለሳሉ።

ተመራማሪዎቹ ከተራቀቁ ራዳሮችና በመላው አውሮፓ ከሚገኙ በሺህ የሚቆጠሩ ፈቃደኛ ተመልካቾች ያገኟቸውን መረጃዎች ለማጠናቀር ጥረት አድርገዋል። በውጤቱም የበጋው ወቅት እንዳለቀ በሚሊዮን የሚቆጠሩት እነዚህ ቢራቢሮዎች አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ሊያዩአቸው በማይችሉበት ከፍታ ማለትም ከ500 ሜትር በሚበልጥ ከፍታ እየበረሩ ወደ ደቡብ እንደሚፈልሱ ማወቅ ችለዋል። ቢራቢሮዎቹ አመቺ የሆነ ነፋስ የሚመጣበትን ጊዜ ጠብቀው በሰዓት እስከ 45 ኪሎ ሜትር በሚደርስ ፍጥነት እየተንሳፈፉ ወደ አፍሪካ የሚያደርጉትን ረጅም ጉዞ ይያያዙታል። በስተ ሰሜን በአርክቲክ ጫፍ ከሚገኙ በረዷማ አካባቢዎች ተነስተው እስከ ምዕራብ አፍሪካ ቆላማ አካባቢዎች ድረስ የሚያደርጉት ይህ ዓመታዊ ጉዞ 15,000 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል። ይህ ጉዞ በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው ሞናርክ የተባለው የቢራቢሮ ዝርያ ከሚያደርገው ጉዞ እጥፍ ገደማ ይበልጣል። በቀለማት ያሸበረቀች እመቤት የተባሉት ቢራቢሮዎች የደርሶ መልስ ጉዟቸውን ለማጠናቀቅ ስድስት ተከታታይ ትውልዶች ይፈጅባቸዋል።

በእንግሊዝ የሚገኘው የዮርክ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ጄን ሂል “በቀለማት ያሸበረቀችው እመቤት መጓዟን፣ መራባቷንና ወደ ፊት መገስገሷን ትቀጥላለች” ብለዋል። በዚህ ሂደት አማካኝነት መላው የቢራቢሮ መንጋ በየዓመቱ ከሰሜን አውሮፓ ተነስቶ አፍሪካ ደርሶ ይመለሳል።

የቢራቢሮዎች ጥበቃ ድርጅት የምርምር ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ሪቻርድ ፎክስ “አንድ ግራም የማይሞላ ክብደትና ከስፒል አናት ያልበለጠ አንጎል ያላት እንዲሁም ተሞክሮ ካካበቱ የቀደሙ ትውልዶች የመማር አጋጣሚ የሌላት ይህች አነስተኛ ፍጡር አስገራሚ የሆነ አህጉር አቋራጭ ጉዞ ታደርጋለች” ብለዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “በአንድ ወቅት፣ [ይህቺ ነፍሳት] ነፋሱ ወደወሰዳት አቅጣጫ በጭፍን የምትነዳና የለውጥ ሂደቷን ሳታጠናቅቅ ገዳይ በሆነው በብሪታንያ ክረምት የተነሳ ሕይወቷ እንደሚያከትም ይታመን ነበር።” ይህ ጥናት ግን “በቀለም ያሸበረቀችው እመቤት የተራቀቀ ችሎታ ያላት ተጓዥ መሆኗን አረጋግጧል።”