በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የመንፈስ ጭንቀት

የመንፈስ ጭንቀት

የመንፈስ ጭንቀት ምንድን ነው?

“ዐንገቴን ደፋሁ፤ ጐበጥሁም፤ ቀኑንም ሙሉ በትካዜ ተመላለስሁ።”—መዝሙር 38:6

ተመራማሪዎች ምን ይላሉ?

ሁሉም ሰው አልፎ አልፎ የሚተክዝበት ጊዜ ይኖራል፤ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ያለበት ሰው ግን እንዲህ ያለው ስሜት ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይበት ሲሆን ሕመሙ አቅም ሊያሳጣውና በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ማንኛውም ጤናማ ሰው ሊያጋጥመው በሚችለው የሐዘን ስሜትና በመንፈስ ጭንቀት መካከል ስላለው ልዩነት ምሁራን ያላቸው አመለካከት የተለያየ እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባዋል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች ሥር የሰደደ አሉታዊ ስሜት የሚያድርባቸው ሲሆን አንዳንድ ጊዜም የዋጋ ቢስነትና ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አሉታዊ ስሜቶች ያስቸግሯቸው ስለነበሩ ብዙ ወንዶችና ሴቶች ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፣ ሐና “በነፍሷ ተመርራ” ነበር፤ ይህ ሐረግ ‘ልቧ ተሰብሮ’ እና ‘ከባድ ሐዘን ተሰምቷት’ ተብሎም ተተርጉሟል። (1 ሳሙኤል 1:10) ነቢዩ ኤልያስም በአንድ ወቅት እጅግ ከማዘኑ የተነሳ ነፍሱን ከእሱ እንዲወስድ ወደ አምላክ ጸልዮ ነበር!—1 ነገሥት 19:4

የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ደግሞ “የተጨነቁትን ነፍሳት አጽናኗቸው” ተብለው ነበር። (1 ተሰሎንቄ 5:14) አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው ከሆነ “የተጨነቁትን ነፍሳት” የሚለው ሐረግ “ለጊዜውም ቢሆን የኑሮ ጭንቀት ከአቅም በላይ እንደሆነባቸው የሚሰማቸው” ሰዎችን ሊያመለክት ይችላል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ታማኝ የሆኑ ወንዶችና ሴቶችም እንኳ በጭንቀት የሚዋጡበት ጊዜ ነበር።

 የመንፈስ ጭንቀት የሚመጣው በግለሰቡ ጥፋት ነው?

‘ፍጥረት ሁሉ በአንድነት ሆኖ በመቃተትና አብሮ በመሠቃየት ላይ ይገኛል።’—ሮም 8:22

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የጤና እክል የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ማመፃቸው ያስከተለው ውጤት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። ለምሳሌ ያህል፣ መዝሙር 51:5 “ስወለድ ጀምሮ በደለኛ፣ ገና እናቴም ስትፀንሰኝ ኀጢአተኛ ነኝ” በማለት ይናገራል። ሮም 5:12 ደግሞ “በአንድ ሰው [በመጀመሪያው ሰው፣ በአዳም] አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ” ይላል። ከአዳም አለፍጽምናን ስለወረስን ማንኛችንም ብንሆን አካላዊ ሕመም እና የስሜት መቃወስ ሊያጋጥመን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ፍጥረት ሁሉ በአንድነት ሆኖ በመቃተትና አብሮ በመሠቃየት ላይ ይገኛል’ በማለት የሚናገረው በዚህ የተነሳ ነው። (ሮም 8:22) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የትኛውም ሐኪም ሊሰጥ የማይችለውን ተስፋ፣ ይኸውም የመንፈስ ጭንቀትን ጨምሮ ሁሉም ዓይነት በሽታዎችና የጤና እክሎች የማይኖሩበት ሰላማዊ አዲስ ዓለም ለማምጣት አምላክ የሰጠውን ተስፋም ይዟል።—ራእይ 21:4

የመንፈስ ጭንቀትን እንዴት መቋቋም ትችላለህ?

“እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።”—መዝሙር 34:18

ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?

በሕይወታችን ውስጥ አንዳንድ ጊዜ ምን ሊያጋጥመን እንደሚችል አናውቅም፤ መጥፎ ሁኔታዎች የሚደርሱብን ጊዜም ይኖራል። (መክብብ 9:11, 12) አፍራሽ ስሜቶች ሕይወትህን እንዳይቆጣጠሩት ማድረግ የምትችላቸው ነገሮች ግን አሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ የታመሙ ሰዎች ሐኪም እንደሚያስፈልጋቸው ይገልጻል። (ሉቃስ 5:31) በመሆኑም ከባድ የሆነ የስሜት መቃወስ እያሠቃየህ ከሆነ የሕክምና እርዳታ መፈለግ ሊያሳፍርህ አይገባም። ጸሎትም በዚህ ረገድ ሊረዳህ እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስ አጥብቆ ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል፣ መዝሙር 55:22 “የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል፤ የጻድቁንም መናወጥ ከቶ አይፈቅድም” ይላል። ጸሎት አእምሮን ለማረጋጋት የሚረዳ መንገድ ብቻ ተደርጎ ሊታይ አይገባም፤ ከዚህ ይልቅ “ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ” ከሆነው ከይሖዋ አምላክ ጋር ለመነጋገር የሚያስችል መንገድ ነው።—መዝሙር 34:18

በተጨማሪም ስሜትህን ለምታምነው የቅርብ ወዳጅህ ማካፈል ሊጠቅምህ ይችላል። (ምሳሌ 17:17) ከይሖዋ ምሥክሮች አንዷ የሆነችው ዳንዬላ እንዲህ ብላለች፦ “አንድ የእምነት አጋሬ ስላለብኝ የመንፈስ ጭንቀት እንድናገር አበረታታኝ። ለዓመታት ስለዚህ ጉዳይ ለማውራት ፈቃደኛ ያልነበርኩ ቢሆንም ስሜቴን ከተናገርሁ በኋላ ግን እንዲህ ማድረግ ያስፈልገኝ እንደነበረ ተገነዘብኩ። ከዚያ በኋላ ምን ያህል ቀለል እንዳለኝ ሳስተውል ተገረምኩ።”