በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

አርክቲክ

በብሪታንያ የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የውቅያኖስ ፊዚክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ፒተር ዋደምስ “በበጋው ወራት የሚኖረው የበረዶ መጠን ከ30 ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር አንድ አራተኛ ያህል ብቻ ነው” ብለዋል። በምድር ሙቀት መጨመር ምክንያት የተከፈተውን የሰሜን ባሕር መስመር በ2012 ወደ 50 የሚጠጉ መርከቦች ተጠቅመውበታል።

ዓለም

እናቶች ከወለዱ በኋላ ባሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ የጡታቸው ወተት ከ700 በላይ የሆኑ የተለያዩ ዓይነት ባክቴሪያዎችን እንደሚይዝ ታውቋል፤ ይህ አኃዝ ባለሙያዎች ያስቡት ከነበረው በላይ ነው። ተመራማሪዎች እነዚህ ባክቴሪያዎች አዲስ ለተወለደው ሕፃን ሆድ ዕቃና ከልጁ በሽታ የመከላከል አቅም ጋር በተያያዘ የሚያበረክቱትን ባዮሎጂያዊ ጠቀሜታ አሁንም ድረስ አጥንተው አልጨረሱም።

ብሪታንያ

የብሪታንያ ሳይንቲስቶች በምስለ የማሽከርከር ማሠልጠኛ መሣሪያ (ሲሙሌተር) አማካኝነት ባደረጉት ጥናት መሠረት ጉንፋን የያዛቸው አሽከርካሪዎች መኪና የመቆጣጠር ንቃታቸው የአልኮል መጠጥ ጠጥተው ከሚያሽከረክሩ ሰዎች ያነሰ ሆኖ ተገኝቷል።

ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ

በአፍሪካ ውስጥ አንዳንዶች እንደሚሉት “ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ መጠን” በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ዝሆኖች ለጥርሳቸው ሲባል በየዓመቱ ይገደላሉ። በአንድ ወቅት በርካታ ዝሆኖች፣ መሃል አናታቸው ላይ በጥይት ተመትተው ተገኝተዋል፤ ምናልባትም የተተኮሰባቸው ከሄሊኮፕተር ላይ ሳይሆን አይቀርም።

አውስትራሊያ

ታላቁ ባርዬር ሪፍ በሚባለው በጣም የሚያምር የባሕር ጠረፍ አካባቢ፣ ባለፉት 27 ዓመታት ከግማሽ የሚበልጠው ሕይወት ያለው ኮራል ጠፍቷል። ሳይንቲስቶች እንደሚናገሩት ከሆነ ይህ ጉዳት በአብዛኛው ሊደርስ የቻለው በምድር ወገብ አካባቢ በሚከሰት ከባድ አውሎ ነፋስ የተነሳ እንዲሁም ቦታው ክራውን ኦቭ ቶርንስ ስታርፊሽ በሚባለው የዓሣ ዝርያ አለልክ በመጥለቅለቁና በውቅያኖስ ሙቀት መጨመር ሳቢያ ኮራሎቹ በመገርጣታቸው ነው።