ቃለ ምልልስ | ሰሊን ግራኖሌራስ
የኩላሊት ስፔሻሊስት ስለምታምንበት ነገር ምን ትላለች?
በፈረንሳይ የምትኖረው ዶክተር ሰሊን ግራኖሌራስ የኩላሊት ስፔሻሊስት ናት። ዶክተር ከሆነች ከ20 ዓመት በኋላ፣ ስለ እኛ የሚያስብ ፈጣሪ መኖር አለበት የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሳለች። ንቁ! መጽሔት ስለ ሥራዋና ስለ እምነቷ አነጋግሯታል።
እስቲ ስለ ልጅነት ሕይወትሽ ንገሪን።
የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለሁ ቤተሰቦቼ ከስፔን ወደ ፈረንሳይ ተዛውረው መኖር ጀመሩ። ወላጆቼ ካቶሊኮች የነበሩ ቢሆንም እኔ ግን 16 ዓመት ሲሆነኝ በአምላክ ማመን አቆምኩ። ሃይማኖት ለሕይወቴ ምንም እንደማይጠቅም ሆኖ ይሰማኝ ነበር። አምላክ ካልኖረ ሕይወት ከየት መጣ ብሎ ለሚጠይቀኝ ሰው “በአሁኑ ጊዜ ሳይንቲስቶች ለዚህ ጥያቄ የሚሰጡት ማብራሪያ የለም፤ አንድ ቀን ግን መልሱን ማግኘታቸው አይቀርም” የሚል ምላሽ እሰጥ ነበር።
በኩላሊት ሕመም ላይ ጥናት እንድታደርጊ ያነሳሳሽ ምንድን ነው?
የተማርኩት በፈረንሳይ ውስጥ ሞንትፔሊዬ በሚገኝ የሕክምና ተቋም ነው። በዚያ የሚሠራ አንድ ፕሮፌሰር የኩላሊት ሕክምና ላይ እንድሠራ አነጋገረኝ። ሥራው ምርምር ማድረግንና ሕመምተኞችን መንከባከብን አጣምሮ የያዘ ነበር። እኔም የምፈልገው እንዲህ ያለ ሥራ ነበር። በ1990፣ በአጥንታችን ውስጥ የሚመረተውን ቀይ የደም ሴል ለመቆጣጠር የሚያስችለውን ሪኮምቢናንት ኢሪትሮፖይትን (ኢፖ) ለበሽተኞች በመስጠት ረገድ በሚካሄደው ጥናት ላይ መካፈል ጀመርኩ። በወቅቱ ይህ የምርምር መስክ በአንጻራዊ ሁኔታ አዲስ ነበር።
ስለ አምላክ ማሰብ እንድትጀምሪ ያደረገሽ ምንድን ነው?
ባለቤቴ ፍሎሪዬል በ1979 ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። እኔ ግን ፍላጎት አልነበረኝም። የሃይማኖት ነገር የሰለቸኝ ገና በልጅነቴ ነበር። ባለቤቴና ልጆቼ ግን የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። ብዙም ሳይቆይ ሁሉም ወዳጆቻችን ማለት ይቻላል የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። ከወዳጆቻችን መካከል አንዷ የሆነችው ፓትሪሲያ እንድጸልይ ሐሳብ አቀረበችልኝ። “በሰማይ ላይ ሊሰማሽ የሚችል አካል ባይኖር የምትከስሪው ነገር የለም። ካለ ግን ውጤቱን ታያለሽ” አለችኝ። ከዓመታት
በኋላ የሕይወት ትርጉም ምን እንደሆነ ማሰብ ጀመርኩ፤ በዚህ ጊዜ ፓትሪስያ የተናገረችው ነገር ትዝ አለኝ። ከዚያም ማስተዋል ለማግኘት መጸለይ ጀመርኩ።ስለ ሕይወት ትርጉም እንድታስቢ ያደረገሽ ምንድን ነው?
አሸባሪዎች በኒው ዮርክ የንግድ ማዕከል ላይ ያደረሱት ጥቃት ‘ክፋት ይህን ያህል የበዛው ለምንድን ነው?’ ብዬ እንዳስብ አደረገኝ። ‘ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት የወደፊት ሕይወታችንን ለአደጋ አጋልጦታል። በሌላ በኩል ደግሞ በአካባቢዬ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ሰላማውያን ናቸው። እነሱ ጽንፈኞች አይደሉም። የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ ይከተላሉ። እኔም መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር ሳይኖርብኝ አይቀርም’ ብዬ አሰብኩ። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን በግሌ ማንበብ ጀመርኩ።
ዶክተር እንደ መሆንሽ መጠን በፈጣሪ ማመን ከብዶሽ ነበር?
አልከበደኝም። ሰውነታችን ያለው የተራቀቀና የተወሳሰበ ንድፍ በጣም ያስደንቀኝ ነበር። ለምሳሌ፣ ኩላሊታችን በደማችን ውስጥ የሚኖረውን ቀይ ደም ሴል ብዛት የሚቆጣጠርበት መንገድ በጣም አስገራሚ ነው።
እንዲህ ያልሽው ለምንድን ነው?
እንዲህ ያለውን አስደናቂ ንድፍ ሊያወጣ የሚችለው አምላክ ብቻ እንደሆነ ተገነዘብኩ
እንደሚታወቀው ቀይ የደም ሴሎች ኦክስጅን ያጓጉዛሉ። ብዙ ደም ቢፈስሰን ወይም ከፍታ ወዳላቸው ቦታዎች ብንሄድ ሰውነታችን ኦክስጅን ያጥረዋል። ኩላሊታችን በሰውነት ውስጥ ያለውን የኦክስጅን መጠን የሚከታተሉ ጠቋሚዎች አሉት። እነዚህ ጠቋሚዎች በደማችን ውስጥ የኦክስጅን እጥረት እንዳለ ካወቁ ኢፖ በብዛት እንዲመረት ያደርጋሉ፤ በደም ውስጥ ያለው የኢፖ መጠን እስከ ሺህ እጥፍ ሊጨምር ይችላል። ኢፖ ደግሞ በአጥንታችን ውስጥ ያለው መቅኒ ተጨማሪ ቀይ የደም ሴሎችን እንዲያመርት ያደርጋል፤ ይህም ተጨማሪ ኦክስጅን ለማጓጓዝ ያስችላል። ይህ አሠራር በጣም አስደናቂ ነው! የሚገርመው ግን እንዲህ ያለውን አስደናቂ ንድፍ ሊያወጣ የሚችለው አምላክ ብቻ እንደሆነ የተገነዘብኩት ይህን አሠራር ለአሥር ዓመታት ያህል ካጠናሁ በኋላ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ስትጀምሪ ምን ተሰማሽ?
በጣም ብዙ የታሪክ መጻሕፍትንና ታዋቂ ልብ ወለዶችን አንብቤያለሁ፤ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ የተለየ መሆኑን ለማስተዋል ጊዜ አልወሰደብኝም። የሚሰጣቸው ምክሮች ተግባራዊ መሆን ስለሚችሉ ምንጫቸው ከሰው በላይ የሆነ አካል መሆኑን ተረዳሁ። የኢየሱስ ባሕርይ በጣም ነው ትኩረቴን የሳበው። በገሃዱ ዓለም የኖረ ሰው እንደሆነ መገንዘብ ችያለሁ። እንደማንኛውም ሰው ስሜት ነበረው፤ ወዳጆችም ነበሩት። የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጇቸውን ጽሑፎች መጠቀም ስላልፈለግኩ ጥያቄ ሲነሳብኝ በኢንሳይክሎፒዲያዎችና በሌሎች የማመሳከሪያ ጽሑፎች ላይ ምርምር አደርግ ነበር።
በምን ጉዳይ ላይ ምርምር አድርገሻል?
በታሪክ መጻሕፍት ላይ ምርምር አደረግኩ። በመጨረሻም ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ጊዜውን ጠብቆ በትክክል እንደተፈጸመ . . . አረጋገጥኩ
ብዙ ነገሮች ቢኖሩም በተለይ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የሚጠመቅበትን ጊዜ አስመልክቶ የተናገረው ትንቢት ትኩረቴን ስቦት ነበር። ይህ ትንቢት አርጤክስስ ከተባለው የፋርስ ገዥ 20ኛ የግዛት ዓመት አንስቶ ኢየሱስ መሲሕ ሆኖ እስከሚገለጥበት ዓመት ድረስ ምን ያህል ዘመን እንደሚያልፍ በትክክል ይናገራል። * እኔ ደግሞ ምርምር የማድረግ ልማድ አለኝ፤ ምክንያቱም የሥራዬ ክፍል ነው። በመሆኑም የአርጤክስስን የግዛት ዘመንና ኢየሱስ አገልግሎቱን ያከናወነባቸውን ዓመታት ለማወቅ በታሪክ መጻሕፍት ላይ ምርምር አደረግኩ። በመጨረሻም ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ጊዜውን ጠብቆ በትክክል እንደተፈጸመና ይህ የሆነውም መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት በመጻፉ እንደሆነ አረጋገጥኩ።
^ አን.19 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 197-199 ተመልከት።