ቃለ ምልልስ | ኢሬን ሆፍ ሎራንሶ
የአጥንት ቀዶ ጥገና ባለሙያ ስለምታምንበት ነገር ምን ትላለች?
ዶክተር ኢሬን ሆፍ ሎራንሶ በስዊዘርላንድ የአጥንት ቀዶ ጥገና ሐኪም ናት። ይህች ሐኪም በአንድ ወቅት አምላክ መኖሩን ትጠራጠር ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን አምላክ መኖሩንና ሕይወት ያላቸውን ነገሮች የፈጠረው እሱ መሆኑን አምና ተቀበለች። ንቁ! መጽሔት ስለ ሙያዋ እና ስለ እምነቷ አነጋግሯታል።
ሳይንስን እንድትወጂ ያደረገሽ ምንድን ነው?
ልጅ ሳለሁ ተፈጥሮ በጣም ያስደንቀኝ ነበር። ያደግሁት በስዊዘርላንድ፣ በዙሪክ ሐይቅ ዳርቻ በምትገኝ ሪክቴርስቪል የምትባል ውብ መንደር ነው። ከወላጆቼ እንዲሁም ከታላቅ ወንድሜና እህቴ ጋር በእግራችን ስንንሸራሸር መንገድ ላይ ስለምናያቸው አንዳንድ ፍጥረታትና ዕፅዋት ይነግሩኝ ነበር።
የአጥንት ቀዶ ጥገና የተማርሽው ለምንድን ነው?
አባቴ፣ በአካባቢያችን በሚገኝ ሆስፒታል ቀዶ ጥገና ክፍል ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ ረዳት ሆኖ ሠርቷል። እዚያ የተመለከተው ነገር በጣም ስላስደነቀው ስለ ቀዶ ጥገና በጋለ ስሜት ይናገር ነበር። እሱ ለዚህ ሙያ የነበረው አድናቆት እኔም በቀዶ ሕክምና መስክ እንድሰማራ አነሳሳኝ። ከአጥንት ቀዶ ሕክምና ጋር የተያያዙ አንዳንድ ሥራዎች ስለሚያስደስቱኝ በዚህ የቀዶ ሕክምና መስክ ለመሰማራት ወሰንኩ። የአጥንት ቀዶ ጥገና ሐኪሞች፣ ሰውነታችን ለመንቀሳቀስ የሚያስችሉትን አጥንቶች እንዲሁም ጡንቻዎችና ጅማቶች ለመጠገን እንደ መሐንዲስ ማሰብ ይኖርባቸዋል።
ከሁሉ በላይ ደግሞ የታካሚዎቼ ጤንነት ተሻሽሎ ማየት በጣም ያስደስተኛል። ከሰዎች ጋር የሚያገናኘኝ ሥራ በጣም እወዳለሁ።
አምላክ መኖሩን እንድትጠራጠሪ ያደረገሽ ምን ነበር?
መጠራጠር የጀመርኩት በወጣትነቴ ሲሆን ተጽዕኖ ያሳደሩብኝ ሁለት ነገሮች ነበሩ። አንደኛ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ አንዳንድ የሃይማኖት አስተማሪዎች ጥሩ ሥነ ምግባር እንደሌላቸው አወቅሁ፤ ይህም በጣም ረበሸኝ። ሁለተኛ፣ በትምህርት ቤት አንዳንዶቹ የባዮሎጂ አስተማሪዎቼ በዝግመተ ለውጥ ያምኑ ነበር፤ እኔም ከጊዜ በኋላ በተለይም ዩኒቨርሲቲ ከገባሁ በኋላ ይህን ትምህርት አምኜ ተቀበልኩ።
የዝግመተ ለውጥን ትምህርት የተቀበልሽው ለምን ነበር?
አስተማሪዎቼ የነገሩኝን ነገር ስላመንኩ ነው። በተጨማሪም የአንዳንድ እንስሳት የሰውነት ቅርጽ መመሳሰል፣ ከአንድ ምንጭ እንደተገኙ የሚጠቁም እንደሆነ እንዲሁም በጂኖች ላይ የሚከሰተው ለውጥ (ጄኔቲክ ሚውቴሽን) አዳዲስ ፍጥረታት እንዲገኙ እንዳደረገ የሚገልጸውን ጽንሰ ሐሳብ የሚደግፍ እንደሆነ አስብ ነበር።
ታዲያ ከጊዜ በኋላ አመለካከትሽን የለወጥሽው ለምንድን ነው?
አንድ ወዳጄ በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ እንድገኝ ጋበዘኝ። የጉባኤው አባላት ያደረጉልኝ አቀባበል እንዲሁም በስብሰባው ላይ የቀረቡት እውቀት የሚያስጨብጡ ንግግሮች በጣም አስደነቁኝ። ቆየት ብሎም ከጉባኤው አባላት መካከል አንዲት ደስ የምትል ሴት ቤቴ መጥታ ጠየቀችኝ፤ እኔም “መጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንደሆነ እንዴት እርግጠኛ ልሆን እችላለሁ?” ብዬ ጠየቅኳት።
በዘመናችን እየተፈጸሙ ያሉትን ነገሮች የሚጠቁሙ በርካታ ትንቢቶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳየችኝ። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በመጨረሻው ዘመን በዓለም ዙሪያ ጦርነቶች፣ “ታላላቅ የምድር ነውጦች፣” እንዲሁም “ቸነፈርና የምግብ እጥረት” እንደሚኖሩ ተናግሯል። * በተጨማሪም ማኅበራዊ ቀውስ እንደሚኖር እንዲሁም ክፋትና ስግብግብነት እንደሚስፋፋ የሚገልጹ ትንቢቶችን አሳየችኝ፤ እነዚህ ትንቢቶች በዛሬው ጊዜ እየተፈጸሙ ነው። * ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ማጥናት ጀመርኩ፤ ይህን ሳደርግም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሁልጊዜም በትክክል እንደሚፈጸሙ ተገነዘብኩ። በተጨማሪም ሕይወት ስለተገኘበት መንገድ የነበረኝን አመለካከት መለስ ብዬ መመርመር ጀመርኩ።
በሕክምናው መስክ ያደረግሽው ምርምር ስለ ሕይወት አመጣጥ ያሳወቀሽ ነገር አለ?
አዎን። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት በጀመርኩበት ጊዜ በጉልበት ቀዶ ሕክምና ላይ ምርምር እያደረግሁ ነበር። የሳይንስ ሊቃውንት ከ1960ዎቹ ማብቂያ ጀምሮ ጉልበታችን ስለሚሠራበት ውስብስብ የሆነ መንገድ ይበልጥ መረዳት ችለው ነበር። ጉልበታችን የሚታጠፈው እንደ በር ማጠፊያ በአንድ አቅጣጫ ብቻ በመንቀሳቀስ እንዳልሆነ ተገንዝበዋል። ከዚህ ይልቅ እንቅስቃሴው መዞርን እንዲሁም መንሸራተትን ያካትታል። ጉልበታችን የሚሠራበት ይህ አስደናቂ መንገድ እንደ ልብ እንዲንቀሳቀስ ስለሚያስችለው መራመድ፣ መደነስ እንዲሁም ሌሎች ብዙ ነገሮችን ማድረግ እንችላለን።
ተመራማሪዎች ለ40 ዓመት ያህል ሰው ሠራሽ ጉልበት ለመሥራት ሲሞክሩ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ የሰው ጉልበት እጅግ ረቂቅና ውስብስብ በመሆኑ ይህን ማድረግ ከባድ ሆኖባቸዋል። ከዚህም በላይ ሰው ሠራሽ ምርቶች ከጉልበታችን ጋር ሲወዳደሩ ያላቸው ዕድሜ በጣም አጭር ነው። እነዚህ ተመራማሪዎች የተሻለ ጥራት ባላቸው ነገሮች ተጠቅመውም እንኳ የሠሩት ጉልበት 20 ዓመት መቆየት ከቻለ ትልቅ ነገር አድርገው ያዩታል። እርግጥ ጉልበታችን የተሠራው ሕይወት ባላቸው ሴሎች ሲሆን እነዚህ ሴሎች ደግሞ ሁልጊዜ ራሳቸውን ይተካሉ። በእኔ አመለካከት ጉልበት፣ የአምላክ ጥበብ የተንጸባረቀበት እንጂ በዝግመተ ለውጥ በአጋጣሚ የመጣ ነገር ሊሆን አይችልም።
ስለ ሚውቴሽንና በአንዳንድ ዝርያዎች የሰውነት ቅርጽ ላይ ስለሚታየው መመሳሰል ምን ትያለሽ?
መመሳሰላቸው የሁሉንም ንድፍ ያወጣው አንድ አካል እንደሆነ የሚጠቁም ነው። ከዚህም በላይ ሚውቴሽን (በጂን ላይ በአጋጣሚ የሚከሰት ለውጥ) ሕይወት ያላቸውን ፍጥረታት ንድፍ በማሻሻል ከነበሩበት የተሻለ ፍጥረት እንዲሆኑ አያስችልም። ከዚህ ይልቅ ሚውቴሽን በጂኖች ላይ ጉዳት የሚያደርስ ነገር ነው። እርግጥ ነው፣ በአጋጣሚ የተከሰተ ነገር ጠቃሚ ሆኖ የሚገኝበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፤ ለምሳሌ አንድ ባቡር ከድልድይ ጋር ተጋጭቶ ድልድዩ ቢፈርስ ይህ መሆኑ ከተማይቱ በወራሪ ጦር እንዳትያዝ ሊያደርግ ይችላል። ይሁን እንጂ አደጋ መድረሱ ከተማይቱ የተሻለ ሁኔታ እንዲኖራት አያደርግም። በተመሳሳይም ሚውቴሽን ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት እንዲሻሻሉ አያደርግም። ከዚህም ሌላ ሚውቴሽን ሌሎች የሰውነታችንን ክፍሎች ይቅርና አስደናቂ የሆነ ንድፍ ያለውን ጉልበታችንን እንኳ በፍጹም ሊያስገኝ አይችልም።
ሚውቴሽን አስደናቂ የሆነ ንድፍ ያለውን ጉልበታችንን በፍጹም ሊያስገኝ አይችልም
የይሖዋ ምሥክር የሆንሽው ለምንድን ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ ማዋል ስጀምር ሕይወቴ በሚያስደንቅ ሁኔታ ተሻሻለ። በተጨማሪም በ2003 የይሖዋ ምሥክሮች ባደረጉት ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ፤ በዚያ ስብሰባ ላይ የነበሩ የማይተዋወቁ ሰዎች እንኳ እንደ ቤተሰብ ዓይነት አንድነት እንዳላቸው ተመለከትሁ። በመካከላቸው እውነተኛ ፍቅር እንዳለ ግልጽ ነበር፤ እኔም ከእነሱ መካከል መሆን ፈለግሁ።