በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

ስንት ዓመት መኖር ትችላለህ?

ስንት ዓመት መኖር ትችላለህ?

ሃሪየት በ2006 ስትሞት ዕድሜዋ 175 ዓመት ገደማ ነበር። በእርግጥ፣ ሃሪየት ሰው አይደለችም። በአውስትራሊያ በሚገኝ መካነ አራዊት ትኖር የነበረች የጋላፓጎስ ዔሊ ነች። ሃሪየት ከሰው ልጆች ጋር ስትነጻጸር በጣም ረጅም ዕድሜ ኖራለች። ከሌሎች ሕያዋን ፍጥረታት ዕድሜ አንጻር ግን የሃሪየት ዕድሜ ያን ያህል የሚያስደንቅ አይደለም። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

  • የፊንላንድ ተመራማሪዎች እንደሚናገሩት ጨዋማ ባልሆነ ውኃ ውስጥ የምትኖረው ፐርል መስል የምትባል ፍጥረት 200 ዓመት ልትኖር ትችላለች።

  • በሮዊንግ ክላም (ኦሽን ክዎሆግ) የተባለው የባሕር ፍጥረት ብዙውን ጊዜ ከ100 ዓመት በላይ የሚኖር ሲሆን ከ400 ዓመት በላይ የኖረ የዚህ ፍጥረት ዝርያ እንዳለም ታውቋል።

  • አንዳንድ ዛፎች በሺህዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሊኖሩ ይችላሉ፤ ከእነዚህ መካከል ብሪስልኮን ፓይን፣ ግዙፉ የሴኮያ ዛፍ እንዲሁም ሳይፕረስ እና ስፕሩስ የተባሉት ዛፎች አንዳንድ ዝርያዎች ይገኙበታል።

በምድር ላይ ካሉት ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ላቅ ያለ እንደሆነ የሚታሰበው የሰው ልጅ ግን ረጅም ዕድሜ ለመኖር ምንም ያህል ጥረት ቢያደርግ ከ80 ወይም ከ90 ዓመት በላይ እንኳ መኖር ከቻለ እንደ ትልቅ ነገር ይታያል!

ታዲያ ምን ይመስልሃል? መኖር የምንችለው ለ80 ዓመት ወይም ከዚያ ብዙም ለማይበልጥ ጊዜ ብቻ ነው? ወይስ ከዚህ ለበለጠ ጊዜ መኖር እንችላለን? ብዙ ሰዎች፣ በሳይንስና በሕክምናው ቴክኖሎጂ የሚደረገው ምርምር መፍትሔ እንደሚያስገኝ ይሰማቸዋል።

ሳይንስ መፍትሔ ሊያመጣ ይችላል?

ሳይንስ በጤናና በሕክምና ቴክኖሎጂ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ሳይንቲፊክ አሜሪካን የተባለ መጽሔት እንዲህ ብሏል፦ “በዛሬው ጊዜ [በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ] በተላላፊ በሽታ ወይም ከወሊድ ጋር ተያይዘው በሚመጡ ችግሮች ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከበፊቱ በጣም ዝቅ ብሏል። . . . ከ1960 ወዲህ የሕፃናት ሞት 75 በመቶ ቀንሷል።” ይሁን እንጂ ሳይንስ ዕድሜን በማራዘም ረገድ ያስገኘው ውጤት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። የሳይንቲፊክ አሜሪካን መጽሔት ሌላ እትም “ለበርካታ ዓመታት ምርምር ቢደረግም ስለ እርጅና የታወቀው ነገር በጣም ጥቂት ነው” ብሏል። ይሁን እንጂ “እርጅና የሚመጣው የሴሎቻችንን እድገት የሚቆጣጠረው በጂናችን ላይ የሚገኘው ፕሮግራም በትክክል መሥራቱን ሲያቆም ሊሆን እንደሚችል ማስረጃዎች ያመለክታሉ።” መጽሔቱ በመቀጠል “እርጅና በዋነኝነት የሚከሰተው በጂናችን ላይ በሚፈጠር ሁኔታ ከሆነ አንድ ቀን ይህን ችግር ማስወገድ እንደሚቻል ይገመታል” ብሏል።

“ለበርካታ ዓመታት ምርምር ቢደረግም ስለ እርጅና የታወቀው ነገር በጣም ጥቂት ነው”

አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት፣ ከዕድሜ ጋር የሚመጡ በሽታዎችን ጨምሮ የእርጅና ዋነኛ ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ ኤፒጄኔቲክስ ተብሎ በሚጠራው የጄኔቲክስ ጥናት ዘርፍ ምርምሮችን እያካሄዱ ነው። ለመሆኑ ኤፒጄኔቲክስ ምንድን ነው?

ሕይወት ባላቸው ሴሎች ውስጥ አዳዲስ ሴሎችን ለማምረት የሚያስፈልጉ ጄኔቲካዊ መረጃዎች አሉ። ከእነዚህ መረጃዎች አብዛኞቹ የሚገኙት በጂኖም ውስጥ ነው፤ ጂኖም በአንድ ሴል ውስጥ የሚገኙትን የዲ ኤን ኤ መረጃዎች በሙሉ ያመለክታል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የሳይንስ ሊቃውንት በሴል ውስጥ በሚገኝ ሌላ ዓይነት የአሠራር ሂደት ይኸውም ኤፒጂኖም በተባለ ነገር ላይ ጥልቅ ጥናት እያደረጉ ነው፤ ኤፒጂኖም ቃል በቃል ሲተረጎም “ከጂኖም በላይ” ማለት ነው። አስደናቂ ስለሆነው ስለዚህ የአሠራር ሂደት እና በውስጡ ስላሉት ኬሚካላዊ አጸግብሮቶች የሚደረገው ጥናት ኤፒጄኔቲክስ ተብሎ ይጠራል።

ኤፒጂኖም የተገነባባቸው ሞለኪውሎች ከዲ ኤን ኤ ጋር አይመሳሰሉም። ዲ ኤን ኤ ባለ ሁለት ፈትል አወቃቀር ያለው ሲሆን የተጠማዘዘ መሰላል ይመስላል፤ ኤፒጂኖም ግን ዲ ኤን ኤ ላይ የሚጣበቅ ኬሚካላዊ ምልክት ወይም አርማ ነው። ታዲያ የኤፒጂኖም ተግባር ምንድን ነው? ኤፒጂኖም ልክ እንደ አንድ የኦርኬስትራ ቡድን መሪ ነው፤ በዲ ኤን ኤ ውስጥ የሚገኙት ጄኔቲካዊ መረጃዎች ጥቅም ላይ የሚውሉበትን መንገድ ይቆጣጠራል። በዲ ኤን ኤ ላይ የሚጣበቀው ይህ ሞለኪውል የተወሰኑ ጂኖች ሥራ እንዲጀምሩ ወይም እንዲያቆሙ ያደርጋል፤ ኤፒጂኖም ይህን የሚያደርገው ሴሉ የሚያስፈልገውን ነገር እንዲሁም እንደ አመጋገብ፣ ውጥረትና መርዛማ ነገሮች ያሉ ከሴሉ ውጭ ያሉ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ስለ ኤፒጂኖም የተገኙ የቅርብ ጊዜ ግኝቶች በሥነ ሕይወት ምርምር ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ አስከትለዋል፤ ኤፒጂኖም ለአንዳንድ በሽታዎች አልፎ ተርፎም ለእርጅና ምክንያት ከሚሆኑ ነገሮች ጋር የተያያዘ እንደሆነ ታውቋል።

የኤፒጄኔቲክስ ተመራማሪ የሆኑት ኔሳ ኬሪ እንዲህ ብለዋል፦ “እንደ ስኪትዞፍሬንያ፣ ሩማቶይድ አርትራይተስ፣ ካንሰር እና ምክንያቱ ያልታወቀ ኃይለኛ ሥቃይ (ክሮኒክ ፔይን) ያሉ በሽታዎች [ከኤፒጂኖም] ጋር ተዛማጅነት እንዳላቸው ይገመታል።” በተጨማሪም ይህ ሞለኪውል “ከእርጅና ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የተረጋገጠ ነው።” በመሆኑም በኤፒጀኔቲክስ መስክ የሚደረገው ምርምር ጤንነትን በማሻሻል እንዲሁም ካንሰርን ጨምሮ የተለያዩ በሽታዎችን በመከላከል ረገድ ውጤታማ የሆኑ የሕክምና ዘዴዎችን ለማግኘት ያስችላል፤ ይህ ደግሞ ዕድሜ እንዲረዝም ያደርጋል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ በዚህ መስክ ያን ያህል እመርታ አልታየም። ኬሪ እንዲህ ብለዋል፦ “አሁንም ቢሆን [እርጅናን ለመከላከል] ከዚህ ቀደም እናደርግ እንደነበረው አትክልት አዘውትሮ ከመመገብና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከማድረግ የተሻለ ዘዴ አላገኘንም።”

ይሁን እንጂ የሰው ልጆች ዕድሜያቸውን ለማራዘም ይህን ያህል ጥረት የሚያደርጉት ለምንድን ነው? ለዘላለም መኖር የምንፈልገው ለምንድን ነው? ዘ ታይምስ የተባለው የብሪታንያ ጋዜጣ እንዳለው “የሰው ልጅ በአጠቃላይ ያለመሞት ባሕርይ መላበስ፣ ትንሣኤ፣ ከሞት በኋላ ያለ ሕይወት ወይም ሪኢንካርኔሽን እንደሚሉት ያሉ ሐሳቦችን በማምጣት ሞትን ለመሸሽ አጥብቆ የሚመኘው ለምንድን ነው?” የዚህን ጥያቄ መልስ ቀጥለን እንመለከታለን፤ መልሱን ማወቃችን እርጅና የመጣበትን ትክክለኛ ምክንያት ለመረዳት ያስችለናል።

ለዘላለም መኖር የምንፈልገው ለምንድን ነው?

ሰዎች በሺህዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ሲማስኑ ኖረዋል። ለዘላለም መኖር የምንፈልገው ለምን እንደሆነ በትክክል ማወቅ እንችል ይሆን? አካላችን ለዘላለም መኖር እንዲችል ተደርጎ የተፈጠረው ለምን እንደሆነ የሚገልጽ አጥጋቢ ማብራሪያ እናገኝ ይሆን? በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለእነዚህ ጥያቄዎች “አዎ” የሚል መልስ ይሰጣሉ። ለምን? መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆችን አፈጣጠር በተመለከተ የያዘውን አጥጋቢ መልስ ስላወቁ ነው።

የሰው ልጆች ከሌሎች ፍጥረታት ጋር የሚመሳሰሉባቸው ነገሮች ቢኖሩም የተለዩ የሚያደርጋቸው መሠረታዊ ነገር እንዳለም መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፣ በዘፍጥረት 1:27 ላይ አምላክ የሰውን ልጆች በራሱ መልክ እንደፈጠራቸው እናነባለን። ይህ ምን ማለት ነው? አምላክ ፍቅር፣ ፍትሕና ጥበብ የማሳየት ችሎታ ሰጥቶናል። እንዲሁም አምላክ ራሱ ዘላለማዊ እንደ መሆኑ መጠን እኛም ለዘላለም የመኖር ፍላጎት እንዲኖረን አድርጓል። መክብብ 3:11 “በሰዎችም ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ” ይላል።

የሰው ልጆች የተፈጠሩት ከአሁኑ የበለጠ ረጅም ዕድሜ እንዲኖሩ ታስቦ መሆኑን ከሚያሳዩት ማስረጃዎች አንዱ የአንጎላችን አፈጣጠር በተለይ ትምህርት በመቅሰም ረገድ ያለው ችሎታ ነው። ዚ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ዘ ብሬይን ኤንድ ብሬይን ዲስኦርደርስ እንደገለጸው የሰው ልጅ አንጎል መረጃዎችን የማስቀመጥ ችሎታው “ወሰን የለውም ለማለት ይቻላል።” ታዲያ ይህንን ችሎታ የማንጠቀምበት ከሆነ ለምን ተሰጠን? የሰው ልጆች አፈጣጠር አምላክ እነሱን ሲፈጥር የነበረውን ዓላማ ያንጸባርቃል። ታዲያ የምናረጀው፣ ሥቃይ የሚደርስብንና የምንሞተው ለምንድን ነው?

የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው?

የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ፍጹም የሆነ አካል እንዲሁም የመምረጥ ነፃነት ነበራቸው። የሚያሳዝነው ግን የመምረጥ ነፃነታቸውን አግባብ ባልሆነ መንገድ በመጠቀም በፈጣሪያቸው ላይ ዓመፁ። * (ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 3:6-11) ማመፃቸው በሌላ አባባል ኃጢአት መሥራታቸው ከፍተኛ የሆነ የጥፋተኝነትና የኃፍረት ስሜት እንዲሰማቸው አደረገ። በተጨማሪም በሰውነታቸው ላይ ጉዳት አስከትሏል፤ በዚህም ምክንያት ያሉበት ሁኔታ ቀስ በቀስ እያሽቆለቆለ የሄደ ሲሆን ሞት የማይቀር ዕጣቸው ሆነ። አንደኛ ቆሮንቶስ 15:56 “ሞት የሚያስከትለው መንደፊያ ኃጢአት ነው” ይላል።

የአዳምና የሔዋን ዘሮች በሙሉ ከእነሱ ስለተገኙ አለፍጽምናን ወርሰዋል፤ እንዲሁም ኃጢአትን ወይም የተሳሳተ ነገር የማድረግ ዝንባሌን ወርሰዋል። ሮም 5:12 እንዲህ ይላል፦ “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።”

እስካሁን ካየናቸው ነጥቦች አንጻር ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን? የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የሚያስችለው ቁልፍ በቤተ ሙከራዎች ውስጥ በሚደረግ ምርምር ሊገኝ አይችልም። ኃጢአት ያመጣውን ጉዳት ሊያስወግድ የሚችለው አምላክ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ አምላክ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ይህን እንደሚያደርግ ማረጋገጫ ይሰጠናል።

‘ሞትን ለዘላለም ይውጣል’

አምላክ ኃጢአትንና ሞትን ለማስወገድ የሚያስችለውን ትልቅ እርምጃ ወስዷል። ስለ እኛ ሕይወቱን አሳልፎ እንዲሰጥ ኢየሱስ ክርስቶስን ልኮታል። የኢየሱስ ሞት ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ሲወለድ ጀምሮ ፍጹም የነበረ ከመሆኑም በላይ “ምንም ኃጢአት አልሠራም።” (1 ጴጥሮስ 2:22) በመሆኑም ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ ፍጹም ሰው ሆኖ ለዘላለም መኖር ይችል ነበር። ታዲያ ፍጹም የሆነ ሕይወቱን የተጠቀመበት እንዴት ነው? ሕይወቱን ለእኛ በመስጠት ከኃጢአት ነፃ ለመውጣት የሚያስፈልገንን ዋጋ ከፍሎልናል። አዎን፣ ኢየሱስ “በብዙዎች ምትክ ነፍሱን ቤዛ አድርጎ” ሰጥቷል። (ማቴዎስ 20:28) ቤዛው የሚያስገኘውን የተሟላ ጥቅም በቅርቡ እናገኛለን። ይህ ለአንተ ምን ትርጉም ይኖረዋል? የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት፦

  • “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”—ዮሐንስ 3:16

  • “ሞትንም ለዘላለም ይውጣል። ጌታ እግዚአብሔር ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።”—ኢሳይያስ 25:8

  • “የመጨረሻው ጠላት የሆነው ሞት ይደመሰሳል።”1 ቆሮንቶስ 15:26

  • “የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ . . . እሱም እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም።”ራእይ 21:3, 4

ታዲያ ስንት ዓመት ልትኖር ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው መልስ ግልጽ ነው፦ የሰው ልጆች ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው፤ ይህ ተስፋ ፍጻሜውን የሚያገኘው አምላክ ክፋትን በሙሉ ከምድር ላይ ካስወገደ በኋላ ነው። (መዝሙር 37:28, 29) ኢየሱስ አጠገቡ ተሰቅሎ ለነበረ ሰው “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ያለው ይህን አስደሳች ተስፋ በአእምሮው ይዞ ነው።—ሉቃስ 23:43

በእርግጥም፣ የሰው ልጆች ለዘላለም ለመኖር መፈለጋቸው ተፈጥሯዊና ምክንያታዊ ነው። አምላክ የፈጠረንም በዚህ መንገድ ነው! በተጨማሪም ይህን ፍላጎታችንን ያሟላልናል። (መዝሙር 145:16) ይሁን እንጂ እኛም የበኩላችንን ማድረግ ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ በአምላክ ላይ እምነት ሊኖረን ይገባል። ዕብራውያን 11:6 “ያለ እምነት አምላክን በሚገባ ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ወደ አምላክ የሚቀርብ ሰው እሱ መኖሩንና ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን ማመን ይኖርበታል” ይላል። እንዲህ ያለ እምነት የሚገኘው የተባልነውን እንዲሁ በየዋህነት በመቀበል ሳይሆን በትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ላይ የተመሠረተውን ማስረጃ በደንብ በመመርመር ነው። (ዕብራውያን 11:1) አንተም እንዲህ ዓይነት እምነት እንዲኖርህ ከፈለግክ በአካባቢህ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን አነጋግር፤ ወይም www.jw.org/am የተባለውን ድረ ገጽ ተመልከት።

^ አን.21 የአዳምና የሔዋን ዓመፅ ከአምላክ ጋር በተያያዘ ከባድ ጥያቄዎች እንዲነሱ አደርጓል። እነዚህ ጥያቄዎች ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? በተባለው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳ መጽሐፍ ላይ ተብራርተዋል፤ ይህን ማወቃችን አምላክ ክፋት እንዲኖር ለጊዜው የፈቀደበትን ምክንያት ለመረዳት ያስችለናል። ይህን መጽሐፍ www.jw.org/am በተባለው ድረ ገጽ ላይ ማንበብ ትችላለህ።