በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ቃለ ምልልስ | ብሬት ሸንክ

አንድ የሥነ ምህዳር ተመራማሪ ስለ እምነቱ ተናገረ

አንድ የሥነ ምህዳር ተመራማሪ ስለ እምነቱ ተናገረ

ብሬት ሸንክ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የተፈጥሮ ንብረት አማካሪ የነበረ አሁን ግን ጡረታ የወጣ ግለሰብ ነው። ዕፅዋት፣ እንስሳትና የመኖሪያ አካባቢ እርስ በርስ ባላቸው ተደጋጋፊነት ላይ ጥናት አካሂዷል። በፈጣሪ መኖር የሚያምነው ለምንድን ነው? ንቁ! እሱ ስለሚያጠናው የሳይንስ መስክና ስለ እምነቱ ጠይቆታል።

አስተዳደግህ ምን ይመስላል?

አባቴ መካኒካል ኢንጂነር ሲሆን ብዙ ጊዜ ስለ ሒሳብና ስለ ሳይንስ በስሜት ይነግረኝ ነበር። ልጅ ሳለሁ በኒው ፓሪስ፣ ኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ መኖሪያችን አካባቢ በሚገኙት ኩሬዎችና ምንጮች በማያቸው ዕፅዋትና እንስሳት በጣም እደነቅ ነበር። ስለሆነም ፐርዱ ዩኒቨርሲቲ ስገባ የሥነ ምህዳር ትምህርት ለመከታተል መረጥኩ።

ለሃይማኖት ፍላጎት ነበረህ?

አዎ፣ ነበረኝ። አባቴ እንከተለው የነበረውን የሉተራን ሃይማኖት ጠንቅቄ እንዳውቅ ያበረታታኝ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈባቸው ቋንቋዎች አንዱ የሆነውን ኮይኔ ተብሎ የሚጠራውን (የተለመደውን) ግሪክኛ አጠናሁ። በመሆኑም ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ የሆነ አድናቆት አዳበርኩ።

ለዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ምን ዓይነት አመለካከት ነበረህ?

ቤተ ክርስቲያኒቱ ይህን ትምህርት ትቀበል ነበር። የሥራ ባልደረቦቼም ያምኑበታል። ስለሆነም ትክክለኛነቱን በተመለከተ ጥርጣሬ አድሮብኝ አያውቅም። ይሁንና በአምላክም አምን ነበር። ሁለቱ እምነቶች እርስ በርሳቸው ይጣጣማሉ የሚል የተምታታ አመለካከት ነበረኝ። ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ አክብሮት ቢኖረኝም ከአምላክ የተገኘ መጽሐፍ እንደሆነ አድርጌ አላስብም ነበር።

ለመጽሐፍ ቅዱስ ያለህን አመለካከት እንድትለውጥ ያደረገህ ምንድን ነው?

ስቲቭ እና ሳንዲ የሚባሉ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች እኔንና ባለቤቴን ዴቢን መጥተው አነጋገሩን። መጽሐፍ ቅዱስ የሳይንስ መማሪያ መጽሐፍ ባይሆንም ስለ ሳይንስ ነክ ጉዳዮች የሚያነሳቸው ነገሮች በሙሉ ትክክል እንደሆኑ አሳዩን። ለምሳሌ፣ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክን በተመለከተ “እርሱ ከምድር ክበብ በላይ በዙፋን ላይ ይቀመጣል” ይላል። (ኢሳይያስ 40:22) በተጨማሪም “ምድርንም እንዲያው በባዶው ላይ አንጠለጠላት” ይላል። (ኢዮብ 26:7) በወቅቱ በሳተላይት ፎቶግራፎች አማካኝነት ሥነ ምህዳራዊ ጥናት አደርግ ስለነበረ እነዚህ ጥቅሶች ልቤን ነኩት። እነዚህ ጥቅሶች የተጻፉት የምድር ክበብ በባዶ ላይ ተንጠልጥሎ የሚያሳይ ፎቶግራፍ የሰው ልጅ ከማንሳቱ ከረጅም ጊዜ በፊት ነው። ስቲቭና ሳንዲ እኔንና ባለቤቴን መጽሐፍ ቅዱስ እያስጠኑን ሲሄዱ ፍጻሜያቸውን ስላገኙ ትንቢቶች ማወቅ ቻልኩ፤ ጠቃሚ  የሆኑ ምክሮችን ተማርኩ፤ እንዲሁም አሳማኝ የሆኑ ማብራሪያዎችን አገኘሁ። ውሎ አድሮ መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የአምላክ ቃል መሆኑን ሙሉ በሙሉ አመንኩ።

ስለ ሕይወት አመጣጥ የነበረህን አመለካከት የለወጥከው መቼ ነው?

በአንድ ወቅት ስቲቭ “እግዚአብሔር አምላክ ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን አበጀው” የሚለውን መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን የማያሻማ ሐሳብ አሳየኝ። (ዘፍጥረት 2:7) የመጀመሪያው ሰው የሕይወት ታሪክ በጽሑፍ ሰፍሯል። ይህ ደግሞ ‘መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንሳዊ ሐቆች ጋር ይስማማል?’ የሚል ጥያቄ በአእምሮዬ ላይ እንዲፈጠር አደረገ። ስቲቭ በዚህ ጉዳይ ላይ ምርምር እንዳደርግ አበረታታኝ፤ እኔም ጉዳዩን መረመርኩ።

ስለ ዝግመተ ለውጥ ምን ነገሮችን ተማርክ?

ብዙ ነገር ተምሬአለሁ። አንዱን ለመጥቀስ ያህል የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ የተለያዩ ዝርያዎች የተገኙበትን መንገድ ለማስረዳት ይሞክራል። ሕይወት ያላቸው ነገሮች እንደ ልብ፣ ሳንባና ዓይን የመሳሰሉ ሥራቸውን በሚገባ የሚያከናውኑ የአካል ክፍሎች አሏቸው። እጅግ በጣም ጥቃቅን ወደሆኑት በዓይን የማይታዩ ሕዋሳት ስንወርድ ደግሞ በሴሎች ውስጥ በጣም አስደናቂ ንድፍ ያላቸው ‘ማሽኖች’ እናገኛለን። የእነዚህ ንድፍ ከየት ተገኘ? የዝግመተ ለውጥ አማኞች የተሻለ አሠራር ያላቸው ሕያዋን ነገሮች በሕይወት የመቀጠል ዕድላቸው ከፍተኛ ስለሚሆን እነዚህ ፍጥረታት እየተመረጡ በሕይወት መቀጠላቸውን ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ ንድፈ ሐሳቡ ‘ይህ አሠራር ከየት ተገኘ?’ ለሚለው ጥያቄ መልስ አይሰጥም። ብዙ የሳይንስ ሊቃውንት የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል የሚል እምነት እንደሌላቸው ማወቅ ቻልኩ። አንድ የሥነ እንስሳ ፕሮፌሰር ከዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳቦች በአንዱም እንደማያምን በሚስጥር ነግሮኛል። ይሁንና ሥራውን እንዳያጣ ስለሚፈራ ይህን አመለካከቱን በይፋ አይናገርም።

ስለ ሥነ ምህዳር ያካበትከው እውቀት እምነትህን አጠናክሮልሃል?

አዎ፣ አጠናክሮልኛል። ሥራዬ ሕይወት ያላቸው ነገሮች አንዳቸው ከሌላው ጋር የሚደጋገፉት እንዴት እንደሆነ ማጥናትን የሚጨምር ነበር። በምድር ላይ ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ የሌሎች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ለምሳሌ፣ አበቦችንና ንቦችን እንውሰድ። የአበቦች ቀለም፣ መዓዛ፣ ቀሰምና ቅርጽ ንቦችን ለመሳብ ከዚያም ከአበቦች የሚያገኙትን ጽጌ ብናኝ ወይም ዱቄት በሌሎች አበቦች ላይ እንዲነሰንሱ ሆኖ የተዘጋጀ ነው። ንቦች የተሠሩት የአበቦች ቀሰም እንዲወስዱና ከአንዱ አበባ የወሰዱትን ጽጌ ብናኝ ከሌላ አበባ ጋር እንዲያዳቅሉ በሚያስችል መንገድ ነው። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው አበቦችና ንቦች አንዳቸው ለሌላው የሚያስፈልገውን ነገር እንዲያሟሉ ተደርገው የተሠሩ ናቸው።

“የምድር ሥነ ምህዳር በአጠቃላይ ዳግመኛ ማንሰራራት የሚችል መሆኑን መመልከቴ ሕይወት አምላክ ባወጣው ንድፍ የተገኘ እንደሆነ በእርግጠኝነት እንዳምን አስችሎኛል”

በአንድ ሥነ ምህዳር ውስጥ ብዙ ነገሮች እርስ በርሳቸው ሲደጋገፉ ይታያል። አንድ ሥነ ምህዳር በሺዎች የሚቆጠሩ ልዩ ልዩ ዓይነት እንስሳትን፣ ዕፅዋትን፣ ባክቴሪያዎችንና ፈንገሶችን አቅፎ ሊይዝ ይችላል። ሁሉም እንስሳት ምግብና ኦክስጅን የሚያገኙት ከዕፅዋት ነው፤ አበባ የሚያወጡ የአብዛኞቹ ዕፅዋት ሕልውና ደግሞ በእንስሳት ላይ የተመካ ነው። ሥነ ምህዳሮች እጅግ ውስብስብ እንዲሁም በውስጣቸው የታቀፉት ሕያዋን ነገሮች በቀላሉ ጉዳት ሊደርስባቸው የሚችሉ ቢሆኑም በሺህ ለሚቆጠሩ ዘመናት በሕይወት መቀጠል ይችላሉ። የአካባቢ መበከል ጉዳት ቢያደርስባቸው እንኳ የብክለቱ ምንጭ ከተወገደ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በጣም ብዙ ሕያዋን ነገሮችን የያዘ ሥነ ምህዳር ዳግመኛ ያንሰራራል። የምድር ሥነ ምህዳር በአጠቃላይ ዳግመኛ ማንሰራራት የሚችል መሆኑን መመልከቴ ሕይወት አምላክ ባወጣው ንድፍ የተገኘ እንደሆነ በእርግጠኝነት እንዳምን አስችሎኛል።

የይሖዋ ምሥክር የሆንከው ለምንድን ነው?

የሰው ልጅ በአካባቢው ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት በእጅጉ ያሳስበኝ ነበር። ሥነ ምህዳሮች ዳግመኛ የማንሰራራት ችሎታ ይኑራቸው እንጂ ሊጠፉ የማይችሉ ነገሮች እንዳልሆኑ አውቃለሁ። ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚሉት አምላክ ‘ምድርን እያጠፉ ያሉትን የሚያጠፋበት’ ጊዜ መኖሩን የይሖዋ ምሥክሮች እንዳውቅ ረዱኝ። (ራእይ 11:18) ይህ ጥቅስ በሕይወቴ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴን እየቀጠልኩ ስሄድ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ተስፋ እውነት እንደሆነ እየተገነዘብኩ መጣሁ።

እምነቴን ለሌሎች ማካፈል ያስደስተኛል፤ ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናኋቸው አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት አሉ። ሰዎች የሕይወትን ፈጣሪና ይህ ፈጣሪ አስደናቂ ለሆነችው ምድራችን ስላለው ዓላማ እንዲያውቁ ለመርዳት የሚያስችለኝን ተጨማሪ ጊዜ ለማግኘት ስል በ55 ዓመቴ ጊዜዬ ሳይደርስ ጡረታ ወጣሁ።