በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንድፍ አውጪ አለው?

የአጋማ ጅራት

የአጋማ ጅራት

አጋማ የተባለው የእንሽላሊት ዝርያ ከወለል ላይ ተስፈንጥሮ ቀጥ ያለ ግድግዳ ላይ በቀላሉ ማረፍ ይችላል። ወለሉ የሚያዳልጥ ከሆነ ግን እግሩ በደንብ መቆንጠጥ ስለማይችል ሲዘል ሚዛኑን ሊስት ይችላል፤ ያም ሆኖ ግድግዳው ላይ በትክክል ያርፋል። ይህ የሚሆነው እንዴት ነው? ሚስጥሩ ያለው ጅራቱ ላይ ነው።

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ አጋማ ከማያንሸራትት ወለል ላይ ሊዘል ሲል በመጀመሪያ ጅራቱን ወደታች በማድረግ ይመቻቻል። ይህም አቅጣጫውን ሳይስት እንዲዘል ያስችለዋል። ወለሉ የሚያዳልጥ በሚሆንበት ጊዜ ግን ስለሚደነቃቀፍ ትክክለኛውን አቅጣጫ ጠብቆ መዝለል ያቅተዋል። ሆኖም አየር ላይ እንዳለ ጅራቱን ወደ ላይ በማድረግ የሰውነቱን አቅጣጫ ያስተካክላል። ጅራቱን ወደ ላይ የሚያደርገው በዘፈቀደ ሳይሆን አቅጣጫውን ለማስተካከል የሚረዳውን አንግል ጠብቆ ነው። በርክሌይ ከሚገኘው የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የወጣ አንድ ሪፖርት እንደገለጸው ከሆነ “እንሽላሊቶቹ [ከዘለሉ በኋላ] ቀጥ ብለው መንሳፈፍ እንዲችሉ ጅራታቸውን ወደ ላይ የሚያደርጉበትን አንግል ያለማቋረጥ ማስተካከል ይኖርባቸዋል።” ወለሉ ይበልጥ የሚያዳልጥ በሆነ መጠን ጅራታቸውንም ይበልጥ ወደ ላይ ከፍ ያደርጋሉ፤ ይህ ደግሞ በትክክል ለማረፍ ያስችላቸዋል።

የምድር መናወጥ ወይም ሌሎች አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት በሕይወት የተረፉ ሰዎችን ለመፈለግ የሚያስችሉ በሮቦት መልክ የሚዘጋጁ ተሽከርካሪዎችን ንድፍ የሚያወጡ መሐንዲሶች፣ ከበፊቱ ይበልጥ እንደ ልብ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን ንድፍ ለማውጣት የአጋማ ጅራት ሊረዳቸው ይችላል። ቶማስ ሊቢ የተባሉ ተመራማሪ እንዲህ ብለዋል፦ “እንደ ልብ በመንቀሳቀስ ረገድ ሮቦቶች ከእንስሳት ጋር ሲነጻጸሩ ጫፋቸው ጋ እንኳ አይደርሱም። በመሆኑም ሮቦቶች ይበልጥ ተመቻችተው መሄድ ከቻሉ ትልቅ እመርታ ነው።”

ታዲያ ምን ይመስልሃል? የአጋማ ጅራት በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?