በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቃለ ምልልስ | ማሲሞ ቲስታሬሊ

የሮቦት ንድፍ አውጪ ስለሚያምንበት ነገር ምን ይላል?

የሮቦት ንድፍ አውጪ ስለሚያምንበት ነገር ምን ይላል?

ፕሮፌሰር ማሲሞ ቲስታሬሊ ጣሊያን በሚገኘው የሳሳሪ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሳይንስ ሊቅ ነው። ዓለም አቀፋዊ የሆኑ ሦስት ሳይንሳዊ መጽሔቶችን በተባባሪነት የሚያዘጋጅ ከመሆኑም በላይ ከሌሎች ጋር በመሆን ከመቶ የሚበልጡ ሳይንሳዊ ጽሑፎችን አዘጋጅቷል። ሰዎች መልክ መለየት የሚችሉት እንዴት እንደሆነና ኳስ እንደ መቅለብ ያሉ በጣም ቀላል የሚመስሉ ድርጊቶችን እንዴት እንደሚያከናውኑ ያጠናል። ከዚያም የሰው ልጆችን የማየት ችሎታ በመቅዳት የሮቦቶችን “ዓይን” ንድፍ ያወጣል። ንቁ! ስለ እምነቱና ስለ ሙያው አነጋግሮታል።

ቀደም ሲል ሃይማኖትህ ምን ነበር?

ወላጆቼ ቤተ ክርስቲያን አይሄዱም እንጂ ካቶሊኮች ነበሩ። በወጣትነቴ አምላክ የለሽ ወደ መሆን አዘነበልኩ። ሕይወት የተገኘው በዝግመተ ለውጥ እንደሆነ ተምሬ ስለነበረ ይህንን አምኜ ተቀብዬ ነበር። ፈጣሪ እንዳለ ባላምንም ከሰዎች የሚበልጥ ኃይል እንዳለ ግን ይሰማኝ ነበር። ይህ ኃይል ምን እንደሆነ ለማወቅ የቡድሂዝምን፣ የሂንዱይዝምንና የታኦይዝምን እምነቶች መረመርኩ፤ ይሁንና ሁሉም የሚያስተምሩት ትምህርት አላረካኝም።

ወደ ሳይንሱ ልታዘነብል የቻልከው እንዴት ነው?

ከልጅነቴ ጀምሮ ማሽኖች ያስደንቁኝ ነበር። እንዲያውም የኤሌክትሪክ አሻንጉሊቶቼን ፈታትቼ መልሼ የምገጣጥምበት ጊዜ ነበር። አባቴ የቴሌኮሙኒኬሽን መሐንዲስ ስለነበር ሬዲዮና ስልክ እንዴት እንደሚሠሩ ማብቂያ የሌላቸውን ጥያቄዎች እጠይቀው ነበር።

የሳይንስ ሊቅ የሆንከው በምን ሙያ ነው?

በጄኖዋ ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሮኒክ ምሕንድስና የተማርኩ ሲሆን የዶክተሬት ዲግሬዬን ለማግኘት በሮቦቶች ንድፍ ላይ ምርምር አድርጌአለሁ። በተለይ ያጠናሁት ስለ ሰዎች የማየት ችሎታና ይህንን ችሎታ በመኮረጅ የሮቦቶችን ንድፍ ማውጣት ስለሚቻልበት መንገድ ነው።

የሰዎች የማየት ችሎታ ትኩረትህን የሳበው ለምንድን ነው?

የማየት ችሎታችን እጅግ በጣም የረቀቀ ነው። የምናያቸውን ነገሮች ምንነት እንድናውቅ ይረዳናል፤ ፊት ለፊት ከሚታየው የዓይናችን ክፍል በስተ ጀርባ ብዙ ነገሮች ይከናወናሉ። ለምሳሌ ኳስ ስትቀልብ የሚሆነውን ነገር እንመልከት። ኳሱን ለመያዝ በምትሮጥበት ጊዜ የዓይንህ ሌንስ፣ የኳሱ ምስል በሬቲናህ ላይ ተስተካክሎ እንዲቀመጥ ያደርጋል። ከዚያም ይህ ምስል የኳሱንና የዓይንህን እንቅስቃሴ በመከተል በሬቲናህ ላይ ከአንድ አቅጣጫ ወደ ሌላው ይጓዛል። በመሠረቱ ዓይንህ የሚተከለው ኳሱ ላይ ነው። ከዚያ ምስሉ ሬቲናህ ላይ ታትሞ ሲቀር ከኳሱ በስተ ጀርባ ያሉት ነገሮች የሚንቀሳቀሱ ይመስሉሃል።

በዚሁ ቅጽበት ዓይንህ የኳሱን ፍጥነትና የሚሄድበትን አቅጣጫ ያሰላል። በጣም የሚያስደንቀው ይህ ስሌት የሚጀምረው በሬቲናህ ውስጥ ዓይንህ የኳሱን እንቅስቃሴ ከኳሱ በስተ ጀርባ ካሉት ነገሮች አንጻር በሚገምትበት ጊዜ ነው። ከዚያም የዓይንህ ነርቭ ከሬቲና የተላለፈውን መልእክት ወደ አንጎልህ ያደርሳል፤ አንጎልህም የደረሰውን መረጃ ተንትኖ ኳሱን መቅለብ እንድትችል ይመራሃል። ይህ ሂደት ከምንገምተው በላይ ውስብስብ ነው።

በፈጣሪ እንድታምን ያደረገህ ምንድን ነው?

በ1990 ወደ ደብሊን፣ አየርላንድ በመሄድ በትሪኒቲ ኮሌጅ ለጥቂት ወራት ምርምር አድርጌ ነበር። ከባለቤቴ ከባርባራ ጋር ወደ አገራችን ስንመለስ ስለ ልጆቻችን የወደፊት ሕይወት ተነጋገርን። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክር የሆነችውን እህቴን ለመጠየቅ ሄድን። እሷም በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ሕይወት—እንዴት ተገኘ? በዝግመተ ለውጥ ወይስ በፍጥረት? (በአማርኛ አይገኝም) የተባለውን መጽሐፍ ሰጠችኝ። ይህን መጽሐፍ ለማዘጋጀት የተደረገው ጥንቃቄ የተሞላበት ምርምር በጣም አስደነቀኝ። መጽሐፉን ሳነብበው የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ የተቀበልኩት አለምንም ማስረጃ እንደሆነ አስተዋልኩ። ለምሳሌ ዝግመተ ለውጥ በቅሪተ አካል ማስረጃዎች በሚገባ የተደገፈ ይመስለኝ ነበር። ነገር ግን አይደለም። እንዲያውም ዝግመተ ለውጥን ይበልጥ እየመረመርኩ ስሄድ ጽንሰ ሐሳቡ በሐቅ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን ባዶ እንደሆነ ተረዳሁ።

ከሮቦት ጋር በተያያዘ ስለማከናውነው ሥራ ቆም ብዬ ሳስብ ‘ማን ያወጣውን ንድፍ ነው ለመኮረጅ የምጥረው?’ በማለት ራሴን ጠየቅኩ።

ከዚያም ከሮቦት ጋር በተያያዘ ስለማከናውነው ሥራ ቆም ብዬ ሳስብ ‘ማን ያወጣውን ንድፍ ነው ለመኮረጅ የምጥረው?’ በማለት ራሴን ጠየቅኩ። ልክ እንደ ሰዎች ኳስ መቅለብ የሚችል ሮቦት ንድፍ ማውጣት ፈጽሞ አልችልም። በእርግጥ አንድ ሮቦት ኳስ መቅለብ እንዲችል ተደርጎ ይሠራ ይሆናል፤ ያም ቢሆን ይህን ማድረግ የሚችለው በታዘዘው መሠረት ብቻ ነው። እንዲያደርግ ከተነገረው ውጪ የሆነ ነገር ቢያጋጥመው ምንም ማድረግ አይችልም። የመማር ችሎታችን ከማንኛውም ሮቦት እጅግ የላቀ ነው፤ ሮቦት እንኳ ሠሪ አለው። አንድ ንድፍ አውጪ መኖር አለበት ብዬ እንዳምን ካደረጉኝ በርካታ ምክንያቶች አንዱ ይህ ነው።

የይሖዋ ምሥክር የሆንከው ለምንድን ነው?

አንደኛው ምክንያት እኔና ባርባራ፣ የይሖዋ ምሥክሮች በጥልቀት ምርምር የሚያደርጉ መሆናቸው ስላስደሰተን ነው። በተለይ ጽሑፎቻቸውን ለማዘጋጀት የሚያደርጉት ምርምር በጣም ያስደንቀኛል። ነገሮችን በዝርዝር መረዳት የሚፈልግ እንደ እኔ ያለ ሰው ጥልቅ ምርምር የተደረገባቸው ጽሑፎች ይማርኩታል። ለምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኙት በርካታ ትንቢቶች የማወቅ ከፍተኛ ጉጉት አደረብኝ። በእነዚህ ትንቢቶች ላይ ያደረግኩት ጥናት መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ ከአምላክ የተገኘ መጽሐፍ እንደሆነ አሳመነኝ። በመሆኑም በ1992 እኔና ባርባራ ተጠምቀን የይሖዋ ምሥክሮች ሆንን።

ሳይንስ እምነትህን አዳክሞታል?

እንዲያውም በተቃራኒው እምነቴን አጠናክሮልኛል። ለምሳሌ የሰውን መልክ እንዴት እንደምንለይ ተመልከት። አንድ ሕፃን በተወለደ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ መልክ መለየት ይችላል። እኔና አንተ አንድ የምናውቀው ሰው ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት መሃል ቢቆምም እንኳ ልንለየው እንችላለን። ሌላው ቀርቶ በምን ዓይነት ስሜት ውስጥ እንዳለም እንኳ ማስተዋል እንችል ይሆናል። ይህን ለማድረግ በጣም ከፍተኛ መጠን ያለው መረጃ በቅጽበት ወደ አእምሯችን እንደሚተላለፍ ግን አንገነዘብ ይሆናል።

የማየት ችሎታችን ከይሖዋ አምላክ ያገኘነው በጣም ውድ ስጦታ እንደሆነ ምንም አልጠራጠርም። መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ ይሖዋ የሰጠን ውድ ስጦታዎች እሱን እንዳመሰግነውና ስለ እሱ ለሰዎች እንድናገር ይገፋፉኛል። ደግሞም ውስጤ እንደሚነግረኝ ለሠራቸው ሥራዎች ምስጋና ሊሰጠው ይገባዋል።