በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አምላክ ለችግረኞች ያስብላቸዋል?

አምላክ ለችግረኞች ያስብላቸዋል?

አምላክ ለችግረኞች ያስብላቸዋል?

“አኗኗራችሁ ከገንዘብ ፍቅር ነፃ ይሁን፤ . . . ምክንያቱም [አምላክ] ‘ፈጽሞ አልተውህም፣ በምንም ዓይነት አልጥልህም’ ብሏል።”​—ዕብራውያን 13:5

አምላክ ለችግረኞች አሳቢነት የሚያሳየው እንዴት ነው?

አንድ የይሖዋ አምላክ አገልጋይ ሲቸገር አምላክ በተለያዩ መንገዶች አሳቢነት ሊያሳየው ይችላል። ከእነዚህ መንገዶች አንዱ የእምነት ባልንጀሮቹ የሚያደርጉለት ፍቅራዊ ድጋፍ ነው። * ያዕቆብ 1:27 እንዲህ ይላል፦ “በአምላካችንና በአባታችን ዓይን ንጹሕና ያልረከሰ አምልኮ ‘ወላጅ የሌላቸውን ልጆችና መበለቶችን በመከራቸው መርዳት’ [ነው]።”

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች እርስ በርስ ይረዳዱ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በይሁዳ ምድር ላይ ከባድ ረሃብ እንደሚመጣ ትንቢት በተነገረ ጊዜ፣ በሶርያ በምትገኘው አንጾኪያ የሚኖሩ ክርስቲያኖች “በይሁዳ ለሚኖሩ ወንድሞች የእርዳታ አገልግሎት ለመስጠት ወሰኑ።” (የሐዋርያት ሥራ 11:28-30) በዚህም ምክንያት የተቸገሩት ክርስቲያኖች የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች ማግኘት ችለዋል። ይህ በፈቃደኝነት የተደረገ እርዳታ ክርስቲያናዊ ፍቅር በተግባር እንዲታይ አድርጓል።—1 ዮሐንስ 3:18

ችግረኞች ያሉበትን ሁኔታ ማሻሻል የሚችሉት እንዴት ነው?

“እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ . . . ነኝ።”​—ኢሳይያስ 48:17, 18

አምላክ ራሳችንን እንድንረዳ ያግዘናል

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል እንደሆነና ተወዳዳሪም እንደሌለው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተገንዝበዋል። ምሳሌ 2:6, 7 እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአንደበቱም ዕውቀትና ማስተዋል ይወጣል። እርሱ ለቅኖች ድልን ያከማቻል [“በጥበቡ ይረዳቸዋል፣” የ1980 ትርጉም ]።” ሰዎች ይህን ጥበብ በመፈለግ ተግባራዊ የሚያደርጉት ከሆነ ራሳቸውን መርዳት ይችላሉ።

ለምሳሌ ያህል፣ በዚህ ጥበብ የሚመሩ ሰዎች ጉዳት ከሚያስከትሉባቸውና ለከፍተኛ ወጪ ከሚዳርጓቸው እንደ ዕፅ ወይም አልኮል ካሉ ሱሶች ይርቃሉ። (2 ቆሮንቶስ 7:1) በተጨማሪም ሐቀኛ፣ ትጉህና ኃላፊነት የሚሰማው ሰው ስለሚሆኑ ሥራ ለማግኘት የተሻለ አጋጣሚ ይኖራቸዋል፤ በተጨማሪም በአሠሪያቸው ዘንድ ተፈላጊ ሠራተኞች ይሆናሉ። ኤፌሶን 4:28 እንዲህ ይላል፦ “የሚሰርቅ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፤ ከዚህ ይልቅ ለተቸገረ ሰው ሊሰጥ የሚችለው ነገር እንዲኖረው . . . በትጋት ይሥራ።”

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥበብ ችግረኞችን እንደሚጠቅማቸው የሚያሳይ ማስረጃ አለ?

የአምላክ “ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በሥራዋ ተረጋግጧል።”​—ማቴዎስ 11:19

የዚህን እውነተኝነት የሚያረጋግጡ ሕያው ምሥክሮች

በጋና የሚኖረው ዊልሰን በሚሠራበት ቦታ ጊዜያዊ ሠራተኛ ሲሆን የቅጥር ጊዜውን ሊጨርስ ተቃርቦ ነበር። ዊልሰን ሥራ በሚለቅበት ቀን የሥራ አስኪያጁን መኪና እያጠበ ሳለ መኪናው ውስጥ ገንዘብ አገኘ። ተቆጣጣሪው ዝም ብሎ ገንዘቡን እንዲወስድ ነገረው። ዊልሰን ግን የይሖዋ ምሥክር ስለሆነ እንዲህ ያለውን ስርቆት ለመፈጸም እምቢ አለ። ከዚህ ይልቅ ገንዘቡን ለባለቤቱ መለሰ። በዚህም ምክንያት ዊልሰን ከሥራ ከመቀነስ ይልቅ ቋሚ ሠራተኛ እንዲሆን ተደረገ፤ ከጊዜ በኋላም የሥራ እድገት አገኘ።

በአውሮፓ የምትኖረው ዣራልዲን፣ አሠሪዋ የይሖዋ ምሥክሮችን ስለምትጠላ ከሥራ አባረረቻት። የአሠሪዋ እናት ግን ልጇን ትልቅ ስህተት እንደሠራች ነገረቻት። “ታማኝ የሆነና ሥራውን በትጋት የሚያከናውን ሠራተኛ የምትፈልጊ ከሆነ ከይሖዋ ምሥክሮች የተሻለ ሰው አታገኚም” አለቻት። ልጇም ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ለማወቅ ጥረት ካደረገች በኋላ ዣራልዲንን ወደ ሥራዋ መለሰቻት።

በደቡብ አፍሪካ የምትኖረውና ልጆቿን ብቻዋን የምታሳድገው ሣራ ችግር በገጠማት ጊዜ ክርስቲያናዊ ፍቅር በተግባር ሲገለጽ ተመልክታለች፤ የጉባኤዋ አባላት ለቤተሰቧ የሚያስፈልገውን ምግብና መጓጓዣ አቅርበውላት ነበር። ከጊዜ በኋላ ልጆቿ “በጉባኤ ውስጥ ብዙ ወላጆች አሉን” በማለት ሊናገሩ ችለዋል።

እንዲህ ያሉ በርካታ ተሞክሮዎችን መጥቀስ እንችላለን። እነዚህ ተሞክሮዎች በምሳሌ 1:33 ላይ የሚገኘውን ይሖዋ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ ያስታውሱናል፦ “የሚያዳምጠኝ ሁሉ ግን በሰላም ይኖራል፤ ክፉን ሳይፈራ ያለ ሥጋት ይቀመጣል።” በእርግጥም ይህ አባባል እውነት መሆኑ ታይቷል!

^ አን.5 በአንዳንድ አገሮች፣ መንግሥት ለችግረኞች ድጎማ ያደርጋል። እንዲህ ዓይነት ዝግጅት በሌለበት አካባቢ ይህ ኃላፊነት በዋነኛነት የሚወድቀው በችግረኛው ዘመዶች ላይ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 5:3, 4, 16