በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዓለም መጨረሻ—ቀልብ የሚስብ ርዕስ

የዓለም መጨረሻ—ቀልብ የሚስብ ርዕስ

ስለ ወደፊቱ ጊዜ ስታስብ በስጋት ትዋጣለህ? ከሆነ፣ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። ከጥንት ጀምሮ ሰዎች ወደፊት ስለሚመጡት ነገሮች የተለያዩ መላምቶችን ይሰነዝሩ የነበረ ሲሆን ብዙዎች የወደፊቱ ጊዜ ጭልምልም ያለ እንደሚሆን ይሰማቸዋል። የዓለም መጨረሻ ይመጣል የሚለው ሐሳብ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የሰዎችን ቀልብ የሚስብ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተዘጋጁ ያሉትን ልብ ወለድ ታሪኮች እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ዓለም እንዴት እንደሚጠፋ በሚገልጹ ታሪኮች ላይ የሚያጠነጥኑ የካርቱን ሥዕሎችን የያዙ መጽሔቶች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፊልሞችና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ መጻሕፍት በስፋት ይገኛሉ። በእነዚህ ልብ ወለዶች ላይ የተገለጹት የሰውን ዘር ለማጥፋት የተዘጋጁ ኃይሎች ተዘርዝረው የሚያልቁ አይመስልም፤ ከእነዚህም መካከል ገዳይ የሆኑ ሮቦቶችና ማሽኖች፣ የተለያዩ አስፈሪ ፍጥረታት፣ ከሌላ ዓለም የመጡ ፍጥረታት፣ ጣረ ሞቶች፣ ድራጎኖች፣ ዝንጀሮዎች፣ ወፎች፣ አይጦች እንዲሁም ትላልቅ ተርቦች ተጠቃሽ ናቸው። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያሉት ታሪኮች እውነት እንደሆኑ አድርጎ የሚያስብ የለም!

ከላይ ከተዘረዘሩት ነገሮች ይበልጥ አንዳንዶችን የሚያሸብሩ ሌሎች ሐሳቦችና መላ ምቶች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ሳይንሳዊ ድጋፍ እንዳላቸው ይነገራል። አንደኛው መላ ምት እንደሚተነብየው ከሆነ የምድር የላይኛው ክፍል በአንድ ጊዜ ከቦታው በመንቀሳቀሱ የተነሳ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ሱናሚዎች፣ የምድር ነውጦችና እሳተ ገሞራዎች ይከሰታሉ። ሌላው መላ ምት ደግሞ ሁሉም ፕላኔቶች በሕዋ ላይ አንድ መስመር ይዘው የሚደረደሩበት ጊዜ እንደሚመጣና በዚህም ሳቢያ የፀሐይ ነፋስ (ሶላር ዊንድ) ስለሚባባስ በምድር ላይ ጥፋት እንደሚከተል ይገልጻል። የምድር መግነጢሳዊ ዋልታዎች በድንገት ቦታቸውን በመቀያየራቸው የተነሳ ከፀሐይ የሚመጣው ጨረር ሁላችንንም እንደሚያጠፋን የሚገልጽ መላ ምትም አለ። እርግጥ ነው፣ እነዚህ ነገሮች መላ ምት ብቻ ስለሆኑ ሊያሸብሩህ አይገባም። ያም ሆኖ እነዚህ ነገሮች የብዙ ሰዎችን ትኩረት መሳባቸው አልቀረም።

ታኅሣሥ 21, 2012 ዓለም እንደምትጠፋ ስለሚተነብዩት ስፍር ቁጥር የሌላቸው መጻሕፍትና ስለ ዓለም መጨረሻ የሚገልጹ ድረ ገጾችስ ምን ማለት ይቻላል? ኒቢሩ የሚባል ፕላኔት (ወይም ፕላኔት ኤክስ) እንዳለና ይህ ፕላኔት ታኅሣሥ 2012 ከምድር ጋር እንደሚላተም የሚገልጸውን ትንቢት እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ለዚህና በእውነታ ላይ ላልተመሠረቱት ሌሎች ጽንሰ ሐሳቦች መነሻው የጥንቶቹ የማያ ሕዝቦች የቀን መቁጠሪያ ነው፤ አንዳንዶች ይህ የቀን መቁጠሪያ ታኅሣሥ 2012 እንደሚያበቃ ይሰማቸዋል።

አንዳንዶች እንዲህ ያሉት ጥፋት እንደሚመጣ የሚገልጹ ትንበያዎች እውን እንደሚሆኑ ስላመኑ በግቢያቸው ውስጥ መጠለያዎችን አሠርተዋል፤ አሊያም ከመሬት በታች የተሠሩ መጠለያዎች ውስጥ ቦታ ለመያዝ ከፍተኛ ወጪ አውጥተዋል። ሌሎች ደግሞ ተራራማ ወደሆኑ አካባቢዎች ተዛውረው እንደ ውኃና የኤሌክትሪክ ኃይል ያሉ ለማኅበረሰቡ የሚቀርቡ አገልግሎቶችን በማያገኙባቸው ቦታዎች ራሳቸውን ችለው ይኖራሉ።

እርግጥ ነው፣ ይህ ሁሉ ምንም የማያሳስባቸው ሰዎችም አሉ። እነዚህ ሰዎች የዓለም ፍጻሜ ቀርቧል የሚለው ሐሳብ አይዋጥላቸውም። ለምሳሌ ያህል፣ በብሔራዊ የበረራና የሕዋ አስተዳደር (NASA) ውስጥ የሚሠሩ የሳይንስ ሊቃውንት እንደሚከተለው ብለዋል፦ “ምድራችን በ2012 ምንም መጥፎ ነገር አያጋጥማትም። ፕላኔታችን ከ4 ቢሊዮን ለሚበልጡ ዓመታት ምንም እክል ሳያጋጥማት መኖር ችላለች፤ በመላው ዓለም ያሉ ተሰሚነት ያላቸው የሳይንስ ሊቃውንት እንደሚያምኑት በ2012 የሚመጣ አንዳችም የሚያሰጋ ነገር የለም።”

ይሁን እንጂ በሰው ዘር ፊት የተደቀነ ምንም ዓይነት አደጋ እንደሌለ ማሰብ ስህተት ነው፤ ‘የዓለም መጨረሻ ይመጣል’ የሚለው ሐሳብ ከልብ ወለድነት ያለፈ ትርጉም እንዳለው የሚሰማው ሁሉ ሞኝ ነው ብሎ መደምደምም ቢሆን ትክክል አይሆንም። ታዲያ የዓለም መጨረሻ በእርግጥ ይመጣ ይሆን? ከሆነስ እንዴት እና መቼ?