በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የአንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት አባል መሆን ያስፈልግሃል?

የአንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት አባል መሆን ያስፈልግሃል?

የተለያዩ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች የሚያደርጉት ነገር ተስፋ አስቆርጦሃል? ወይም የአንድ ሃይማኖት አባል መሆን እንደማያስፈልግ ይሰማሃል? ከሆነ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ያጋጠመህ አንተ ብቻ አይደለህም። እንዲያውም የየትኛውም ሃይማኖታዊ ድርጅት አባል መሆን የማይፈልጉ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እያሻቀበ ነው።

አንዳንዶች ሃይማኖታዊ ድርጅቶችን ትተው የሚወጡት በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ግብዝነትና አለመቻቻል ተንሰራፍቶ ስለሚገኝ ነው። ሌሎች ደግሞ በርካታ ደንቦች ያሏቸውን የአምልኮ ሥርዓቶች መከተል በጣም ከባድ እንደሆነ ይሰማቸዋል። የተቀሩት ደግሞ ‘አምላክን ለማምለክ አንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት የግድ አያስፈልግም’ የሚል አመለካከት አላቸው። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?

በጥንት ዘመን የነበሩ የአምላክ ወዳጆች

መጽሐፍ ቅዱስ እንደ አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ያሉ በጥንት ዘመን የነበሩ የቤተሰብ ራሶች አምልኳቸውን እንዴት ያካሂዱ እንደነበር የሚገልጽ ሐሳብ ይዟል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ትክክለኛና ቀና የሆነውን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከእርሱ በኋላ ቤተ ሰቦቹን እንዲያዝ [አብርሃምን] መርጬዋለሁ።” (ዘፍጥረት 18:19) የአምላክ ወዳጅ የነበረው አብርሃም በግለሰብ ደረጃ ከፈጣሪ ጋር ወዳጅነት መሥርቶ ነበር። (ያዕቆብ 2:23) ይሁን እንጂ አብርሃም ከቤተሰቡም ጋር በመሆን አምልኮውን ያከናውን ነበር። በተመሳሳይም ታማኝ የአምላክ አገልጋይ የነበሩ ሌሎች የቤተሰብ ራሶች፣ በአብዛኛው ከቅርብ የቤተሰባቸው አባሎችና ከዘመዶቻቸው አልፎ ተርፎም ከአገልጋዮቻቸው ጋር አብረው አምልኳቸውን ያከናውኑ ነበር።

ከጊዜ በኋላ አምላክ፣ የጥንቶቹ እስራኤላውያን በኋላም የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች አንድ ላይ ተሰብስበው እንዲያመልኩት አዝዞ ነበር። (ዘሌዋውያን 23:2, 4፤ ዕብራውያን 10:24, 25) የአምላክ አገልጋዮች አንድ ላይ ሆነው አምልኮ በሚያካሂዱባቸው በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ይዘምሩ፣ ቅዱሳን መጻሕፍትን ያነቡና በኅብረት ይጸልዩ ነበር። (ነህምያ 8:1-8፤ ቆላስይስ 3:16) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በጉባኤው ውስጥ የሚደረገውን የአምልኮ ሥርዓት ብቃት ያላቸው ወንዶች መምራት እንዳለባቸው ይናገራል።—1 ጢሞቴዎስ 3:1-10

አንድ ላይ ሆኖ ማምለክ ያሉት ጥቅሞች

ከእነዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች አንጻር አምላክ በዛሬው ጊዜ ያሉ ወዳጆቹም የአንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት አባል እንዲሆኑ ይጠብቅባቸዋል ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው። ደግሞም አምላክን አንድ ላይ ሆኖ ማምለክ የተለያዩ ጥቅሞችን ያስገኛል።

ለምሳሌ ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ አንድን እውነተኛ አምላኪ በጠባብ መንገድ ላይ ከሚጓዝ እንዲሁም ለውድድር ከሚሮጥ ሰው ጋር ያመሳስለዋል። (ማቴዎስ 7:14፤ 1 ቆሮንቶስ 9:24-27) አንድ ሯጭ፣ ወጣ ገባ በሆነ መንገድ ላይ ረጅምና አድካሚ ውድድር በሚያደርግበት ጊዜ በቀላሉ ሊደክም ብሎም ሩጫውን ሊያቋርጥ ይችላል። ይሁንና ከሌሎች የሚያገኘው ማበረታቻ፣ በጣም ደክሞት ሩጫውን ለማቆም በሚያስብበት ጊዜ እንኳ መሮጡን እንዲቀጥል የሚያስችል ብርታት ሊሰጠው ይችላል። በተመሳሳይም አንድ መንፈሳዊ ሰው፣ እንዲዝል የሚያደርጉ መከራዎች ያጋጥሙት ይሆናል፤ በዚህ ወቅት እንደ እሱ አምላክን ከሚያመልኩ ሌሎች ሰዎች የሚያገኘው ማበረታቻ ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና ይዞ እንዲቀጥል ሊረዳው ይችላል።

ይህ ሐሳብ በዕብራውያን 10:24, 25 ላይ ከሚገኘው ነጥብ ጋር ይስማማል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ።” እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች እንደ ወንድማማችና እህትማማች ሆነው አምላክን ማገልገል እንዳለባቸው ቅዱሳን መጻሕፍት ይናገራሉ፤ ይህም እንደ አንድ አካል ስምም እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይህን አካል ወይም ጉባኤ አንድ በሚያደርገው የፍቅርና የሰላም ማሰሪያ እንደተሳሰረ አድርጎ ገልጾታል። ለምሳሌ ያህል፣ ኤፌሶን 4:2, 3 እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች አምልኳቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ማድረግ ያለባቸውን ነገር ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “በፍጹም ትሕትናና ገርነት፣ በትዕግሥት እንዲሁም እርስ በርሳችሁ በፍቅር በመቻቻል ኑሩ፤ አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት አድርጉ።” ታዲያ ከሌሎች የአምላክ አገልጋዮች ተለይተህ አምልኮህን ለብቻህ የምታከናውን ከሆነ ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ትችላለህ?

የአምላክ ፈቃድ፣ መንፈሳዊ የሆኑ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ እንዲያገለግሉት ሳይሆን እውነተኛ አገልጋዮቹ በኅብረት እንዲያመልኩት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች ንግግራቸው አንድ እንዲሆን፣ መከፋፈልን እንዲያስወግዱ እንዲሁም “በአስተሳሰብም ሆነ በዓላማ ፍጹም አንድነት” እንዲኖራቸው ያሳስባል። (1 ቆሮንቶስ 1:10) አምላክ እያንዳንዱ ግለሰብ ለብቻው እንዲያመልከው የሚፈልግ ቢሆን ኖሮ ይህ ሐሳብ ትርጉም አይኖረውም ነበር።

የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች በግልጽ እንደሚያሳዩት አምላክን አንድ ላይ ሆኖ ማምለክ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው። በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተገለጹትን ብቃቶች የሚያሟላና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሃይማኖታዊ ድርጅት፣ መንፈሳዊ ፍላጎቶችህን ማርካት እንድትችል የሚያስፈልግህን ድጋፍ ሁሉ ሊሰጥህ ይችላል።—ማቴዎስ 5:3

እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ግብዞች ከመሆናቸውም በላይ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የጭካኔ ድርጊቶችን ይፈጽማሉ። ሆኖም ይህ ከማንኛውም ሃይማኖታዊ ድርጅት እንድትርቅ ሊያደርግህ አይገባም። የአምላክን የሥነ ምግባር መመሪያዎች ለሌሎች በማስተማር በዓለም ዙሪያ ለሁሉም የሰው ዘሮች ፍቅር የሚያሳይ አንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት መኖር አለበት። እንዲህ ያለው ሃይማኖታዊ ድርጅት እውነተኛ እምነት እንድታዳብር ሊረዳህ ይችላል። በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን ሃይማኖታዊ ድርጅት ለይተህ እንድታውቅ የሚረዱህ መሥፈርቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ።