በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለብዙዎች አስፈሪ የሆነው የዓለም መጨረሻ

ለብዙዎች አስፈሪ የሆነው የዓለም መጨረሻ

ቀደም ባለው ርዕስ ላይ ከተጠቀሱት ስለ ዓለም መጨረሻ የሚገልጹ ምናብ የፈጠራቸው መላ ምቶች ውጪ በዓለማችን ላይ ስጋት የሚፈጥሩ አሳሳቢ ጉዳዮች አሉ። ብዙ ሰዎች የሕዝብ ብዛት ከመጠን በላይ መጨመርና ይህን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለው የውኃና የምግብ እጥረት ያስጨንቃቸዋል። ሌሎች ደግሞ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ውድቀት የሚያስከትለው መዘዝ ያሳስባቸዋል። ስለ ተፈጥሮ አደጋዎች፣ ወረርሽኞች ወይም የኑክሌር ጦርነትስ ምን ማለት ይችላል? እንዲህ ዓይነቶቹ ክስተቶች ዓለም አቀፍ ጥፋት ሊያስከትሉ ይችሉ ይሆን?

ዓለምን ሊያጠፉ እንደሚችሉ የሚታሰቡ አንዳንድ ክስተቶችን እስቲ በአጭሩ እንመልከት። ከእነዚህ ክስተቶች መካከል የሰውን ዘር ከምድር ገጽ ሊያጠፉ የሚችሉት ሁሉም ባይሆኑም ዛሬ ያለው ሥልጣኔ የመጥፋት አደጋ እንዲጋረጥበት እንደሚያደርጉ ግን አይካድም። ከዚህ ቀጥሎ የተወሰኑትን እንመለከታለን።

ከፍተኛ ኃይል ያላቸው እሳተ ገሞራዎች

በ1991 በፊሊፒንስ፣ ፒናቱቦ ተራራ ላይ የሚገኘው እሳተ ገሞራ ፈንድቶ ከ700 በላይ ሰዎችን የገደለ ሲሆን 100,000 ሰዎችን ያለ ቤት አስቀርቷል። በእሳተ ገሞራው ሳቢያ 30 ኪሎ ሜትር ያህል ወደ ሰማይ የተበተነው አመድ ተመልሶ ወደ ምድር ሲወርድ ሰብሎችን የቀበራቸው ከመሆኑም ሌላ የሕንፃዎች ጣሪያ እንዲደረመስ አድርጓል። ፒናቱቦ ተራራ ላይ እንደፈነዳው ያሉ እሳተ ገሞራዎች ለብዙ ዓመታት የሚዘልቅ የአየር ንብረት ለውጥ ያስከትላሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ በጥንት ዘመናት እንደደረሱት ያሉ ከፍተኛ ኃይል ያላቸው የእሳተ ገሞራ ፍንዳታዎች፣ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ በጣም ከባድና እጅግ መጠነ ሰፊ የሆነ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ። እንዲህ ያሉት እሳተ ገሞራዎች ወዲያው ከሚያደርሱት ከፍተኛ ጥፋት በተጨማሪ ዓለም አቀፍ የሆነ የአየር ንብረት ለውጥ ያስከትላሉ፤ ይህ ደግሞ የሰብል ውድመት በማምጣት የምግብ አቅርቦት እንዲስተጓጎልና ረሃብ እንዲከሰት ያደርጋል።

“እሳተ ገሞራዎች በብዙ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ዕፅዋትንና እንስሳትን ያጠፋሉ፤ ከፍተኛ ኃይል ያላቸው እሳተ ገሞራዎች ደግሞ የመላዋን ፕላኔት የአየር ንብረት በመለወጥ የተለያዩ ፍጥረታትን ዝርያዎች ከምድር ገጽ ሊያጠፉ ይችላሉ።”​—ናሽናል ጂኦግራፊክ

ንዑሳን ፕላኔቶች

በ1908 አንድ ማለዳ ላይ በቫናቫራ፣ ሳይቤሪያ የሚኖር አንድ ሰው በረንዳ ላይ ቁጭ ብሎ እያለ የተከሰተ አንድ ፍንዳታ ሰውየውን ከወንበሩ አሽቀንጥሮ ጣለው። ፍንዳታው የፈጠረው ሙቀት እጅግ ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ሰውየው ሸሚዙ በእሳት የተያያዘ ያህል ሆኖ ተሰምቶት ነበር። የሚገርመው ይህ ፍንዳታ የተከሰተው 60 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ በሚገኝ ቦታ ላይ ነው። የፍንዳታው መንስኤ 35 ሜትር ስፋት ያለውና 100 ሚሊዮን ኪሎ ግራም ገደማ የሚመዝን ንዑስ ፕላኔት (አስተሮይድ) ነው። ንዑስ ፕላኔቱ የፈነዳው በከፍተኛ ፍጥነት ተወርውሮ ወደ ምድር ከባቢ አየር ዘልቆ ሲገባ በተፈጠረው ኃይለኛ ግፊትና ግለት ሳቢያ ነበር። ይህ ፍንዳታ፣ ሂሮሽማን ያወደመው አቶሚክ ቦምብ ከነበረው 1,000 ጊዜ የሚበልጥ ኃይል በማመንጨቱ 2,000 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት የሚሸፍን የሳይቤሪያ ደን ጠፍቷል። ከዚህ የሚበልጥ መጠን ያለው ንዑስ ፕላኔት ወደ ምድር ቢመጣ ደግሞ የሚያስከትለው ጥፋት እጅግ የከፋ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፤ እንዲህ ያለው ፍንዳታ፣ ከባድ ሰደድ እሳት የሚያስከትል ሲሆን ይህን ተከትሎ የምድር ሙቀት በከፍተኛ መጠን ስለሚያሽቆለቁል በርካታ ሕያዋን ፍጥረታት ከምድር ገጽ ይጠፋሉ።

“ምድር በታሪኳ በሙሉ ከጠፈር በሚመጡ ጅራታም ኮከቦችና ንዑሳን ፕላኔቶች ስትደበደብ ኖራለች። ባለፉት ዘመናት እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች በተደጋጋሚ ይከሰቱ ነበር፤ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ወደፊትም መከሰታቸው አይቀርም።”—ክሪስ ፓልመ፣ በፔንስልቬንያ ዩኒቨርሲቲ የአስትሮኖሚና አስትሮፊዚክስ አንጋፋ መምህር

የአየር ንብረት ለውጥ

የሳይንስ ሊቃውንት የምድር አማካይ ሙቀት መጨመሩ፣ ኃይለኛ ሙቀትና ቅዝቃዜ መከሰቱ፣ በተራሮች አናት ላይ ያለው በረዶና ትላልቅ የበረዶ ግግሮች መቅለጣቸው እንዲሁም ኮራል ሪፍ እና ጠቃሚ የሆኑ ዝርያዎች መጥፋታቸው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ እየተከሰተ መሆኑን የሚያመለክት እንደሆነ ያምናሉ። ለዚህ የአየር ንብረት ለውጥ መንስኤ ስለሆኑት ነገሮች የተለያዩ ጽንሰ ሐሳቦች ቢሰነዘሩም ብዙዎች እንደሚናገሩት መንስኤው መኪኖችና ኢንዱስትሪዎች የከሰል ድንጋይን፣ ነዳጅንና የተፈጥሮ ጋዝን በማቃጠል የሚለቁት ጭስ ነው፤ ምክንያቱም እንዲህ ያሉት ከቅሪተ አካል የሚገኙ የኃይል ምንጮች ከፍተኛ መጠን ያለው ካርቦን ዳይኦክሳይድ ወደ ከባቢ አየር ይለቅቃሉ።

አንዳንድ ባለሙያዎች፣ ካርቦን ዳይኦክሳይድ በብዛት ወደ ከባቢ አየር መለቀቁ ሙቀት ከምድር የሚወጣበት ፍጥነት እንዲቀንስ በማድረግ የምድርን ሙቀት እንደሚጨምረው ያምናሉ። ዕፅዋት ካርቦን ዳይኦክሳይድን ስለሚጠቀሙ መጠነ ሰፊ የሆነ የደን ጭፍጨፋም ቢሆን የአየር ንብረት ለውጥ እንዲከሰት ምክንያት ሊሆን ይችላል።

“ብዙ የሳይንስ ሊቃውንት፣ በአሁኑ ጊዜ ያለው የምድር ሙቀት መጨመር በዚህ ፍጥነት ከቀጠለና የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት ካልተገታ የምድር አማካይ የሙቀት መጠን መጨመሩን እንደሚቀጥልና ይህም ለመተንበይ የሚያስቸግር ከፍተኛ የአየር ንብረት መዋዠቅ ሊያስከትል እንዲሁም የውቅያኖስ ጠለል ከፍ እንዲል ሊያደርግ እንደሚችል ያምናሉ፤ የውቅያኖስ ጠለል ከፍ ማለቱ ደግሞ አብዛኛው የሰው ዘር በሚኖርባቸው ዝቅተኛ ቦታዎች ላይ በሚገኙ የባሕር ዳርቻዎች አካባቢ ስጋት ይፈጥራል።”—ስለ ነገ ማሰብ፦ እውነታው፣ እሴቶችና የወደፊቱ ጊዜ (እንግሊዝኛ)

ወረርሽኝ

በ14ኛው መቶ ዘመን፣ ጥቁር ሞት የተባለው ወረርሽኝ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ የአውሮፓን ሕዝብ ሲሶ ፈጅቶታል። ከ1918 እስከ 1920 ባሉት ዓመታት ደግሞ የኅዳር በሽታ ቢያንስ 50 ሚሊዮን ሰዎችን ገድሏል። በወቅቱ የነበረው የመጓጓዣ ዘዴ ፈጣን አለመሆኑ እነዚህ በሽታዎች በፍጥነት እንዳይዛመቱ አስተዋጽኦ አድርጓል። ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ከተሞች በማደጋቸውና በቀላሉ በዓለም ዙሪያ መጓዝ በመቻሉ እንደነዚህ ያሉ ወረርሽኞች ቢከሰቱ በፍጥነት ወደ ሁሉም አህጉራት ሊዛመቱ ይችላሉ።

እንደዚህ ዓይነቱ ወረርሽኝ ያለ ሰው ጣልቃ ገብነት ሊከሰት ይችላል። ይሁን እንጂ የሰው ልጆች የሚፈጥሯቸው በሽታዎች ማለትም ባዮሎጂያዊ የጦር መሣሪያዎችም ከባድ ስጋት እየፈጠሩ ነው። በመስኩ የተሠማሩ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ስለ እነዚህ መሣሪያዎች እውቀት ያላቸው ጥቂት ሰዎች፣ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በኢንተርኔት አማካኝነት ገዝተው ገዳይ የሆኑ ባዮሎጂያዊ የጦር መሣሪያዎችን ማምረት ይችላሉ።

“በተፈጥሮ የሚመጡት በሽታዎች የሚያስከትሉት አደጋ እንዳለ ሆኖ እነዚህን ወይም ሰው ሠራሽ የሆኑ ሌሎች በሽታ አምጪ ተሕዋስያንን አሊያም ደግሞ [መድኃኒቶችን የመቋቋም ኃይል ያላቸው] በሽታ አምጪ ተሕዋስያንን የሚጠቀሙ ሰዎች ጥቃት በመሰንዘር ከባድ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ።”—ጥምር ፓርቲዎች ያቋቋሙት የጅምላ ጨራሽ የጦር መሣሪያዎች ቁጥጥርና የፀረ ሽብርተኝነት ምርምር ማዕከል

በጣም አስፈላጊ የሆኑ ዝርያዎች ከምድር ገጽ መጥፋት

ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ በዩናይትድ ስቴትስ ያሉ ንብ አርቢዎች ከንቦቻቸው መካከል በየዓመቱ 30 በመቶ የሚያህሉትን አጥተዋል፤ በዓለም ዙሪያ ለሚታየው ለዚህ ክስተት መንስኤው በርካታ የንብ መንጋዎች በማይታወቅ ምክንያት በድንገት ቀፏቸውን ለቀው መሄዳቸው ነው። ንቦች ማር ከመስጠት የበለጠ ጥቅም አላቸው። የወይን፣ የፖም፣ የአኩሪ አተርና የጥጥ ተክሎችን ጨምሮ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ዕፅዋትን ዘሮች ያዳቅላሉ። በእርግጥም ንቦች ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።

በውኃ አካላት ላይ የሚያድጉት ፋይቶፕላንክተን የተባሉት ረቂቅ ዕፅዋትም በእጅጉ ያስፈልጉናል። ፋይቶፕላንክተን ባይኖሩ ኖሮ ዓሣ አናገኝም ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ አፈር አየር እንዲያገኝ የሚያናፍሱት ትሎች ባይኖሩ የምናመርተው ሰብል በጣም ጥቂት ይሆን ነበር። እንደነዚህ ያሉት በጣም አስፈላጊ ዝርያዎች መጥፋታቸው የምግብ እጥረትና ረሃብ እንዲከሰት ስለሚያደርግ ለዓመፅና ለብጥብጥ መንስኤ ይሆናል። ብክለት፣ የሕዝብ ቁጥር ከመጠን በላይ መጨመር፣ የምድር የተፈጥሮ ሀብት መበዝበዝ፣ የእንስሳት የተፈጥሮ መኖሪያ መጥፋት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ የእንስሳት ዝርያዎች ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች ባይኖሩ ኖሮ ከሚጠፉበት 1,000 ጊዜ በሚበልጥ ፍጥነት ከምድር ገጽ እንዲጠፉ ምክንያት እየሆኑ ነው።

“በየዓመቱ ከ18,000 እስከ 55,000 የሚደርሱ ዝርያዎች ከምድር ገጽ ይጠፋሉ። መንስኤው፦ የሰው ልጅ የሚያከናውናቸው ተግባሮች።”—የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም

የኑክሌር ጦርነት

አንድ የኑክሌር ፍንዳታ አንድን ከተማ በቅጽበት ሊደመስስ ይችላል፤ ይህ አሳዛኝ እውነታ ነሐሴ 1945 ከአንድም ሁለት ጊዜ ታይቷል። የኑክሌር ፍንዳታ ከፍተኛ መጠን ያለው ኃይል የሚያመነጭ ሲሆን ፍንዳታው የሚፈጥረው ኃይለኛ ግፊት፣ ነፋስ፣ ሙቀት፣ እሳትና ጨረር ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ይደመስሳሉ። በዚህ ላይ ደግሞ ጨረሩ ምግብንና ውኃን ይበክላል። የኑክሌር ጦርነት በብዙ ቶን የሚገመት አቧራ ወደ አየር ስለሚለቅ የፀሐይን ብርሃን ይጋርዳል፤ ይህም በዓለም ዙሪያ የሙቀት መጠን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ያደርጋል። በዚህም ምክንያት ሰብሎችና ሌሎች ዕፅዋት ይሞታሉ። ምግብ ከሌለ ደግሞ ሰዎችና እንስሳት በረሃብ ያልቃሉ። በዛሬው ጊዜ ዘጠኝ የሚያህሉ አገሮች የኑክሌር ጥቃት ለመሰንዘር የሚያስችል አቅም እንዳላቸው ይነገራል። ሌሎች ጥቂት አገሮች ደግሞ የራሳቸውን የኑክሌር የጦር መሣሪያ በመሥራት ሂደት ላይ ያሉ ይመስላል። አሸባሪዎችም የኑክሌር የጦር መሣሪያዎችን እጃቸው ለማስገባት በጣም እንደሚጓጉ ግልጽ ነው።

“የኑክሌር ጦር መሣሪያዎችን ያህል የሰው ልጆች በቅጽበት የመጥፋት አደጋ እንዲጋረጥባቸው የሚያደርግ ሌላ አሳሳቢ ነገር የለም። . . . አሁንም እንኳ በመላው ዓለም 25,000 የሚያህሉ የኑክሌር ጦር መሣሪያዎች አሉ። . . . ይዋል ይደር እንጂ ይህ ቦምብ በአሸባሪዎች እጅ መግባቱ አይቀርም።”—የዓለም ሁኔታ ያሳሰባቸው ሳይንቲስቶች ኅብረት